/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰላምን አስተማማኝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለፁ፡፡ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አመራሮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰላሙን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውንና ከመግባባት ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሰው ህይወትና ንብረት መጥፋቱ አሳዛኝ ድርጊት ነውም ብለዋል።
የሶማሌ ክልል የመገንጠል ጥያቄ አንስቷል ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “የኢትዮጵያ አንድ አካል የአንድ ዛፍ አንድ ቅጠል አይደለም! እንደው ዝም ብሎ የሚረግፍ ሀገር አይደለም፡፡ እኛ ስፈለግን የምንጠብቀው፤ ሰላልፈለግን የሚፈርስ ሀገር አይደለም፡፡ እንደው በዋዛ እንበታናለን ብሎ መጠበቅ ከንቱ ህልም ነው፡፡ ሀገራችንን መጠበቅ፣ መስፋት፣ ማሳደግ የሁሉም ዜጎች ኋላፊነት ነው፡፡” ሲሉ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ከ26 ዓመታት የስደት ህይወት በሗላ በቅርቡ ወደ ሀገራቸው የተመለሱትን ብፁዕዎ ቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን መጎብኘታቸው ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሰዓት በሗላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 4ኛ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን መጎብኘታቸውን እንዲሁም ስለ “ይቅርታና ፍቅር” መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፁ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በመንበረ ፓትረያርክ በመገኘት ብፁዕዎ ቅዱስ አቡነ ማርቆርዮስን ሲጎበኙ የትግራይ ክልል ም/ር/መስተዳድር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልም መገኘታቸው ተገልጿል።