- ጣታችንን በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዳንቀስር ኢትዮጵያዊነታችን ያቅበናል
- በሕግ የበላይነት መተዳደር አልቻልንም እያልን ሕግን መጣስ የለብንም
- የድጋፍ ሰልፎቹ፣ ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ቀናዒ እንደኾነ ያመለክታሉ
ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አመራራቸው፤
ከዚህ ቀደም ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ (የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር)፣ አጠር ያለ ደብዳቤ ጽፌላቸው ነበር፡፡ በደብዳቤው ያደረስኋቸው መልእክት፣
“እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲኾኑ፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጉዳይ ላይ ደስ ብሏቸው ነበር፡፡ ይኸውም፣ እርስዎ የመጡበት ክልል፣ ኢትዮጵያዎ ነኝ ወይስ አይደለሁም ከሚል ሐምሌታዊ ጥርጣሬ ነፃ የወጣ በመኾኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ከእርስዎ በፊት ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ኢትዮጵያዊ እንዲኾኑ ጸሎት ስናደርግ እንደነበረ ኹሉ፣ አሁን ደግሞ ለእርስዎ፣ እውነተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኾኑ እየጸለይን ነው፤” የሚል ነበር፡፡
የሚያሳዝነው ግን፣ ኹለቱም የተመኘነውን ሳያሟሉ ቦታቸውን ለቀዋል፡፡ ወደ ወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስንመጣ፣ ኹለቱ የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተናጠል ያጧቸውን ጸጋዎች አሟልተው ተገኝተዋል – ኢትዮጵዊነትንም ጠቅላይ ሚኒስትርነትንም፡፡ በእኔ እይታ፣ አሁን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚስተዋለው የሕዝብ ቅቡልነትና በጎ መንፈስ የመነጨው እኒህን ኹለት ነገሮች አስማምተው በመያዛቸው ነው፡፡
ኹለተኛ ዶ/ር ዐቢይ፣ “ፕራግማቲክ” የኾኑ መሪ ናቸው፡፡ ከፓርቲ ርእዮተ ዓለም ተነሥተው የኢትዮጵያን ችግር ሊፈቱ አልሞከሩም፤ራሳቸውን ከፓርቲ ርእዮተ ዓለም ጫና አላቅቀዋል፡፡ በዋናነት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዙሪያ ያሉ ቀኖናዎች፣ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ይኾናሉ ብለው አያምኑም፡፡ ሙሉ ለሙሉ የአተያይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የመሳሰሉት ለ25 ዓመታት የሠለጠኑትን የርእዮተ ዓለም አተያዮች ጥለው ነው፣ ኹሉንም ነገር እንደ ዘመኑ፣ እንደ ጊዜው፣ እንደ ኹኔታው ለማየት የሞከሩት፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ዶ/ር ዐቢይ፤ ከዚህ ቀደም ከነበሩ የኦሮሞ የፖሊቲካ ድርጅቶች አስተሳሰብ በተቃራኒ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ህልውና እና የፖሊቲካ ጥያቄ፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ማሕቀፍ ውስጥ ነው የሚፈታው ብለው፣ ፊት ለፊት የቆሙ መሪ ናቸው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን እንዲያውም፣ ከዚህ ማሕቀፍ ውጪ አማራጭ የለም፤ ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ለኦሮሞ ነፃነትና መብት መከበር የሚደረገው ትግል፣ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ ካልኾነ ውጤት የለውም፤ የሚል ጽኑ አቋም ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሪ ናቸው፡፡
ህወሓት እና ሌሎች የኢሕአዴግ ድርጅቶች፤
ስሙ እንደሚጠቁመው፣ አሕአዴግ ግንባር ነው፡፡ በውስጡ የተለያዩ ድርጅቶችን አቅፎ ይዟል፡፡ እነርሱም፥ ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድ እና ደኢሕዴን ናቸው፡፡ ከግንባሩ ምሥረታ ጀምሮ በመካከላቸው ያለው የኃይል አሰላለፍ በቅርቡ እስከተናደበት ጊዜ ድረስ፣ ህወሓት ፍጹም የበላይነትን ይዞ ቆይቷል፡፡ ይኸውም፣ ህወሓት እንደ ግንባሩ አንቀሳቃሽ (ባዕለ ሕይወት) ሐሳብ አመንጪ ሲኾን፣የተቀሩት ግን ፈጻሚና ተከታይ ኾነው ለረዥም ዓመታት ተጉዘዋል፡፡
የግንባሩ ተቀዳሚ ሐሳብ አፍላቂና አናፂ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲያልፉ፣ አባል ድርጅቶች ከዚህ በኋላ ሐሳቡን በየራሳችን ማዋጣት ይኖርብናል፤ የሚል ዓይነት አዝማሚያ ሲያሳዩ፣የበላይነቱን ተቆጣጥሩ ከቆየው ህወሓት የተሰማው ምላሽ፥ ተረጋጉ፤ ጉዳዩ አያሳስባችሁ፤ ታላቁ መሪያችን፣ ለ40 ዓመት የሚያሠራ የአመለካከትና የሐሳብ ስንቅ ጥልውልን ነው ያለፉት፤ የሚል ነበር፡፡
ህወሓት፣ በብቸኝነት ሐሳብ የማመንጨቱን ሚና የተቀሩት አባል ድርጅቶች እንደወከሉት ሕዝብ በራሳቸው መንገድ አስበው እየተረጎሙ እንዲንቀሳቀሱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- አማራነትም ኾነ ኦሮሞነት በየድርጅቶች እንዲገለጽ የተፈቀደው፣ የህወሓትን ፍጹም የበላይነት በማይገዳደር መልኩ በተፈቀደላቸው ውኃ ልክ ነበር፡፡ ከዚህ ገደብ የማለፍ አዝማሚያ ካሳዩ፣ ትምክህተኛና ጠባብ የሚል ፍረጃና ስያሜ እንዲሸማቀቁ ተደርገዋል፡፡
አሁን ግን፣ አማራውም ኾነ ኦሮሞው፣ የህወሓትን ፍጹም የበላይነት በማስወገድ፣ የድርጅታቸውን እንቅስቃሴ በራሳቸው እየወሰኑ ሲሠሩ እየታየ ነው፡፡ ብአዴንም ኾነ ኦሕዴድ፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ሳይሠቀቁ አመራር እየሰጡ ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ነው፡፡
የህወሓት መሪዎች፣ በቁንጮነት የመሩት ሥርዓት፣ በሥሩ ሰፊውን የሀገሪቱን ሀብት የተቆጣጠሩበት በመኾኑ በውስጡ አጅሎ የያዘውን የሙስና ሕዋስ ለይቶ ራሱን ማጽዳት አለመቻሉና አለመፈለጉ፣ በሒደት ከሕዝብና ከእኅት ድርጅቶቹ ጋራ ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ ኾኗል፡፡
ይኸው፣ ሀብት እያነፈነፈ የሚያድን አግበስባሽና መዝባሪ ኃይል (predatory elite)፣ የፖሊቲካውን ሥልጣን ከተቆጣጠሩት አስቻይ አካላት ጋራ የጥገኛ ግንኙነት መሥርቶ አገሪቱን ከአቅሟ በላይ ዘርፏል፡፡
በተጨማሪም፣ ፍትሐዊ የንዋይ ክፍፍል ላይ ለመድረስ፣ ጤናማ ውድድር፣ በችሎታ ላይ የተመሠረተ እኩል ተጠቃሚነት ቀርቶ፣ በተወሰኑ የወንዝ ልጆች የሀገሪቱ ሀብትና ንብረት እንዲያዝ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም፣ የህወሓት፥ የርእዮት፣ የተግባር፣ የፖሊቲካና የኢኮኖሚ ሞኖፖሊ ይህንም ለማስጠበቅ የተፈጸመው የነጻነት አፈናና የመብት ረገጣ፣ ሕዝቡንም ኾነ አባል ድርጅቶቹን በእጅጉ በማስቆጣት ወደ እንቢተኝነት አድጎ እነኾ ዛሬ የምናየውን የአሰላለፍ ለውጥ ሊያሳየን ችሏል፡፡
በሀገሪቱ እየተካሔደ ያለው ምንድን ነው?
አሁን በሀገሪቱ አብዮት ነው እየተካሔደ ያለው፡፡ “Revolution” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል አመጣጡን ብንመለከት፤ ሰማይ ላይ ያሉትን የፀሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብት እንቅስቃሴ መግለጫ ነበር፡፡ እነዚህ የህዋ ሥነ ፍጥረታት ቦታቸውን ከነበሩበት ወዳልነበሩበት ዑደት ሲያደርጉ፣ “Revolution” ተካሔደ ይባል ነበር። በአጭሩ “Revolution” ማለት የቦታ፣ የምሶሶ፣ የማዕከል ለውጥ ማለት ነው፡፡ የምሰሶ ለውጥ ማለት ነው፡፡ አብዮት ነው እየተካሔደ ያለው የሚለውን ለማስረዳት ስሞክርም፣ ይህን መነሻ አድርጌ ነው፡፡
ማዕከል የነበረው ህወሓት ተገፍቶ አሁን ሌላ ማዕከል እየተፈጠረ ነው፡፡ ለ27 ዓመት ማዕከሉን ይዞ አድራጊ ፈጣሪ የነበረው ህወሓት ቦታውን ለቅቆ ሌላ ማዕከል እየተገነባ ነው፡፡ ይህ ኹነት ደግሞ አብዮት ወይም “Revolution” ለሚለው አገላለጥ የተስማማና በኢሕአዴግ የውስጥ ሥርዐት የተደረገውን የቦታ መቀያየር ሒደት የሚያሳይ ነው፡፡
በውጭስ ምን ተካሔደ ብንል፣ ሕዝቡ በብአዴን እና በኦሕዴድ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ ነው የጀመረው፡፡ ሕዝቡ መጠየቅ ጀመረ፡፡ በተለይ ግፊቱ ያየለው ደግሞ በአማራ እና በኦሮሚያ አካባቢ ነው፡፡ ህወሓት በድሮው የተቆጣጣሪነት መንገድ መሔድ አልቻለም፡፡ ቺንዋ አቼቤ፤ “Things Fall Apart“ እንዳለው መጽሐፉ፣ ነገሮች እንዳልኾኑ ኾኑ፤ ህወሓትም እንደ ፊቱ መቀጠል አልቻለም፤ ነገሮች ተሰበሩ፤ እንዳልኾኑ ኾኑ፤ በሀገሪቱ የኾነው ይኸው ነው፡፡ አሁን ሕዝቡ የግፊቱ ጫፍ ላይ ደርሷል፤ መሃሉን ይዞ የነበረው አካል ወደ ዳር ተገፍትሮ፣ በሌላ ኃይል እየተተካ ነው፡፡ ድምፅ የሌለው አብዮት ማለት ይኼ ነው፡፡
ፓርቲንና ሕዝብን እንለይ፤
“የትግራይ ሕዝብ ማለት ህወሓት ነው፤ ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው፤” የሚለው አካሔድ ተቀባይነት የለውም፡፡ በመጀመሪያ ህወሓት ማለት የትግራይ ተወላጆች የፈጠሩት ድርጅት እንጅ መላው ትግራይ ማለት አይደለም፡፡
እንደ ሌላው ሁሉ፣ በትግራይ ሕዝብና በዴሞክራሲ እንዲሁም በሕግ የበላይነት ወይም በኢትዮጵያዊነት መካከል ምንም ተቃርኖ የለም። የትግራይ ሕዝብ፣ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ነፃነቱንና መብቱን የሚሻና የሚያስከብር ለመኾኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ፣ የህወሓት የበላይነት ተሻረ ብሎ ቅር የሚለው ሕዝብ አይደለም፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው፣ ከህወሓት ጋራ የተቆራኘ መዝባሪ ኃይል ስለመኖሩ መናገር፣ የትግራይ ሕዝብ በጠቅላላ የዚህ ክፍል አካል ነው ማለት ፈጽሞ አይደለም፡፡ ትላንትና የህወሓት መሪዎች፣ በተወሰነ ብሔር ላይ ጣታቸውን ስለ ቀሰሩ አሁን ደግሞ በሌላው ብሔር በኩል፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጣትን መቀሰር እንደማይገባ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያቅበናል፡፡
አንዳንድ ወገኖች አሁን የተነሣውን አብዮታዊ አካሔድ ህወሓት ሙሉ በሙሉ የማይቀበለው ስለኾነ፣ ኢሕአዴግ እንደ ግንባር መቀጠሉ አሳሳቢ ነው የሚሉ አሉ፡፡ የህወሓት የቀድሞ መሥራች አመራሮች አሁንም በበላይነት እስካሉ ድረስ የተባለው ነገር ሊደርስ ይችላል፡፡ ኾኖም ድርጅቱ ወጣት ተተኪዎችን ወደ አመራርነት ማምጣት ከጀመረ፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋራ በእኩልነት አብሮ የመሥራት ፈቃደኝነት ይኖረዋል፡፡
የድርጅቱ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በዚህ ኾኖ፣ በተጨማሪም፣ የትግራይ ክልል እንደ ሌሎቹ ክልሎች፣ ከህወሓት የሐሳብ አፈና ሊላቀቅና የሰፋ ምኅዳር ሊዘረጋለት ይገባል፡፡ ከኅትመት ውጤቶች ጀምሮ የብዙኃን መገናኛዎች ይዘትና ሥርጭት፣ አማራጭ ሐሳብ በነፃነት የሚስተናገድባቸው እንዲኾኑ ያስፈልጋል፡፡ ፖሊቲካዊ መግባባት ላይ የሚደረሰው፣ በውይይት፣ በንግግርና በመሰብሰብ ነፃነት ላይ ተመሥርቶ በሚንሸራሸር ሐሳብ እንደመኾኑ፣ ህወሓት የለመደውን የሐሳብና አሠራር እመቃ መለወጥ የግድ ይለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና የዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብ
የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጅማሮ ፅንሰ ሐሳብ አንዱ ችግር፤ ዴሞክራሲው በሊበራሊዝም የታጀበ አለመኾኑ ነው፡፡ የዴሞክራሲ እና የሊበራሊዝም ፖለቲካዊ መርሕ ከፍልስፍና አንጻር ሲታይ፣ አንድነትም ልዩነትም አላቸው፡፡ የሰው ልጅ ሙሉ የኾነ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ፍትሐዊ ነፃነት ይኖረው ዘንድ የዴሞክራሲና የሊበራሊዝም መስተጋብር ግድ ይላል፡፡ ዲሞክራሲ ሕዝብን ከዓምባገነን ጦር የሚከላከል ጋሻ ሲኾን፣ ሊበራሊዝም ደግሞ የሕዝብ ሉዓላዊነት ነው፡፡
የእኛ ሀገር አንደኛው ችግር፤ የዴሞክራሲና የሊበራሊዝም መስተጋብር አለመኖር ነው። ሌጣውን ያለሊበራሊዝም ዴሞክራሲውን እንጀምር ማለታችን ነው ችግራችን፡፡ ደርግ በአንድ ሥርዓት ውስጥ ያለውን አፋኝ ተቋም ማለትም ወታደሩን፣ ፖሊሱን ደኅንነቱን ፊት ለፊት በግልጽ አውጥቶ ነበር የተጠቀመበት፡፡ ምንም ርእዮተ ዓለማዊ ሽፋን አልነበረውም፡፡ ኢሕአዴግ ግን ለሰው ልጅ ነፃነት ያገለግላሉ ተብለው የተቀመጡትን እንደ ፕሬስ ነፃነት፣ ምርጫ፣ የሲቪክ ተቋማት ፈቅደናል ብሎ ነገር ግን ወደ ራሱ አላምዶ ነው ለጭቆና መሣርያነት የተጠቀመባቸው፡፡ በደርግ እና በኢሕአዴግ መካከል ያለው ልዩነት ይኸው ነው፡፡
አሁን አመራርን የማጠናከርና የማደላደል ኹኔታ ነው ያለው፡፡ በመጀመሪያ ቃል ነበር ይላል መጽሐፉ፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ይኼ ቃል ወይም ሐሳብ ተሸካሚ ተቋማት ያስፈልጉታል፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ወሳኝ የኾኑ ቦታዎችን በአዲሱ አመራር መተካት ነው፡፡ ይኼ አስፈላጊ ነው፡፡
ዴሞክራሲ ሦስት ነገሮች ያስፈልጉታል፡፡ አንደኛው፥ በጎ ፈቃድ ነው፤ ኹለተኛው፥ ባህል ነው፤ ሦስተኛው፥ ተቋም ነው፡፡ አሁን የበላይ አመራሩ በጎ ፈቃድ አለ እየተባልን ነው፡፡ ባህሉ ደግሞ እየወደቅንም እየተነሣንም የምንፈጥረው ጉዳይ ነው የሚኾነው፡፡ ወሳኙ ተቋማቱ ናቸው፡፡ ተቋማቱ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ዝም ብለን በአመራሩ በጎ ፈቃድ ውስጥ ብቻ እንዳንወድቅ፣ ሐሳቡ እንደ ምሶሶ ተሸካሚ ተቋማትን ማግኘት አለበት፡፡ ይኼ እስኪኾን ድረስ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት ትልቅ መዋቅር ዘርግተው፣ ሀብት የሰበሰቡና ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ወገኖች አሉ፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ እንጂ በአንድ ጊዜ ኹሉንም ነገር ለመገለባበጥ መሞከር ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በተደጋጋሚ የለውጥ ጅማሮዎች ሲቀለበሱ የምናስተውለው፣ በአንድ ጊዜ ኹሉንም ነገር መገለባበጥ በሚለው እሳቤ የተነሣ ነው፡፡
እኔ፣ ለውጡ ወደ ኋላ አይመለስም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ተስፋ እንዳደርግ ያገዘኝ ደግሞ፣ ሕዝቡ ለውጡን ደግፎ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊ ሰልፎች መመልከቴና ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሐሳብ ጽንፎች ያሉ ኃይሎች ተቀራርበው ለመሥራት ሲፈቃቀዱ በማየቴ ነው። ሰልፎቹ፣ ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ቀናዒ እንደኾኑ አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ታንክ ተጠቅሜ መንግሥት እገለብጣለሁ ለሚሉትም መልእክት ያስተላለፉ ናቸው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ግን ጥንቃቄ ሊለየን አይገባም፡፡
በሌላ በኩል፣ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የዴሞክራሲ አተያዮች ሊስተካከሉ ይገባል። እኛ ተበድለናል፤ በሕግ የበላይነት መተዳደር አልቻልንም፤ እያልን ሕግን መጣስ የለብንም፡፡ የዴሞክራሲ ባህል ይኼን አይፈቅድም፡፡
ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ
ይሄ ኹለት ዓመት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ እየተነሣ ያለ የሽግግር መንግሥት ጉዳይ አለ፡፡ ይኼ በእኔ አመለካከት ለወቅቱ የሚገባ ጥያቄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ኹልጊዜ በሽግግር መንግሥት ሥር ማለፍ የለባትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ እኔ አሸጋግችኋለሁ ብለው ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ፓርቲዎች በቀጥታ መዘጋጀት ያለባቸው ለምርጫ ነው፡፡ በነፃነት ጎሕ ላይ ነን፡፡ ዕድሉ እንዳያመልጠን ዜጎች ኹሉ በንቃት ሒደቱን መጠበቅና መሳተፍ አለባቸው። በጥንቃቄ ወደፊት ማሻገር ያስፈልጋል፡፡ አንዱ የመሸጋገሪያ ድልድይ፣ መጪውን ምርጫ፥ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተኣማኒ በማድረግ ነው፡፡ ይህም በቀዳሚነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሓላፊነት ነው፡፡ አሁን ሁሉም ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ ማኦ ሴቱንግ በአንድ ወቅት፣ “Let hundred flowers blossom” እንዳለው፣ አበቦቹም ያብቡ፤ ሁሉም ይውጣና ይታይ፤ ሐሳብ ያቅርብ፤ ይወዳደር፤ በመድረኩ ይለይለት። ዴሞክራሲ ማለት፣ ለኹሉም ተፎካካሪዎች እኩል መጫወቻ ሜዳ ማዘጋጀት ማለት ነው፡፡ አሁን እየገቡ ያሉ ፓርቲዎችም በመጨረሻ እየተሰባሰቡ ጥምረቶችን ይፈጥራሉ የሚል እምነት አለኝ። ኢሕአዴግም እንደ አንድ ድርጅት፣ በዶ/ር ዐቢይ አመራር በቀጣዩ ምርጫ ከባድ ተፎካካሪ እንደሚኾን ተስፋ አደርጋለኹ፡፡
(ምንጭ፦አዲስ አድማስ)