በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ የመጀመሪያው ሳምንት ከአንዲት የአውሮፓ አገር አምባሳደር ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስንጨዋወት “በዚህ ግዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጫማ ውስጥ መቆም የሚፈልግ ሰው የለም” ብለውኝ ነበር። በርግጥም በወቅቱ ከነበረው ጫፍ እና ጫፍ የተካረረ፣ እንዲሁም ስርዓት አልበኝነት ጠርዝ ላይ የቆመ የተቃውሞ ፖለቲካ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትርነት የወቅቱ የአገሪቱ አስቀያሚ ሥራ ነበር።
ነገር ግን ገና በመጀመሪያው የሥራ ወራታቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ስጋት እንደጤዛ ማርገፍ ተሳክቶላቸው ነበር። ሥልጣነ መንበሩ ላይ ከተቀመጡ በኋላ ብዙ መልካም ንግግሮችን በማድረግ፥ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተስፋ ቀስቅሰዋል። ያልተጠበቁ የፖለቲካ እርቆችን እና የሠላም ስምምነቶችን፣ ባልተጠበቀ ፍጥነት አከናውነዋል። የተቃውሞ ሰልፎችን በሠላማዊ ሰልፎች መተካት ችለዋል። ይሁን እንጂ የመቶ ቀናት የሥራ ምዘናቸውን በድል በተወጡ ጥቂት ቀናቶች ውስጥ አዳዲስ ስጋቶች ተስፋዎችን መልሰው መዋጥ ጀምረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትርነት በወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖከቲካ እውነትም አስቀያሚው የሥራ ዘርፍ ነው የሚያስብል ግዜ ላይ ተመልሰን የቆምን ይመስላል።
ቀውሱ ተረጋጋ ወይስ በአዲስ ተተካ?
ባለፉት ሁለት ወራቶች ብቻ ዜጎችን ማፈናቀል ከምንግዜውም በላይ ከፍቶ ከጉጂ እና ጌድዮ ዞኖች፣ ከሶማሊ እና ኦሮሚያ አጎራባች ወሰኖች፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ከኦሮሚያ ክልል በጥቅሉ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል። እንዲሁም ደግሞ ከጅግጅጋ ተፈናቅለው አዳማ ካምፕ ውስጥ የተጠለሉ ዜጎች በዚህ ሳምንት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ከቀድሞ ቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ ሁሉ ከመጠለያ ካምፓቸውም ዳግም ተፈናቅለዋል፡፡ በወልቂጤ፣ በሐዋሳ፣ በአሶሳ፣ በጣና በለስ፣ በአዊ ዞን፣ በጅግጅጋ፣ በሻሸመኔ እና ሌሎችም ቦታዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ የደቦ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተዳፈኑ ጥያቄዎች እንዳዲስ ተቆስቁሰዋል፤ ደቡብ ክልልን እንዳይቀጥል ሊያረገው የሚችለው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ አንዱ ነው። ወጣቶች የመንግሥት ተቋማትን የፍርድ ሥራ መሥራት እየዳዳቸው ነው፤ ያሻቸውን ሰው በወንጀል ጠርጥረው የፍርድ እርምጃ እስከመውሰድ የደረሰበት አጋጣሚ አለ፡፡ ክልላዊ መንግሥታት እርስበርስ የተኳረፉ ይመስላል፤ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ያላቸውም ኅብረት የመቀዛቀዝ አዝማሚያ እያሳየ ነው።
እነዚህ ክስተቶች መንግሥት የተቃዋሚ ልኂቃንን ማረጋጋት ቢችልም፣ የተቆጡትን ወጣቶች ማረጋጋት እንደከበደው እያጋለጡ ነው፡፡ የመደመር ቅስቀሳው ተቃዋሚዎች ሠላም እንዲያወርዱ ማድረግ ቢችልም፣ የክልል መንግሥታት ግን እርስ በርሳቸው እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እንዳይቃቃሩ ማድረግ አልቻለም፡፡
አምና የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ይገባል የሚል ቅሬታ ነበር፥ ዘንድሮ ግን ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ የበለጠ ነጻ መንግሥታት የሆኑ ይመስላል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተለመደ ሁኔታ ልዩነታቸው ጎልቶ እየታየ ነው። በየክልሉ መንግሥታት ብዙኃን መገናኛዎች እርስ በርስ እስከ መወነጃጀልም የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። በተለይም ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሊ እና ትግራይ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ የበለጡ ነጻ መንግሥታት መስለዋል።
የችግሮቹ መንስዔዎች
ከአፈና ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የሚደረገው የሙከራ ግዜ ችግሮች ዋነኛ መንስዔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በቅጡ ያልተደራጁ የየአካባቢው ወጣቶች የአፈና ፈሊጥ የተጠናወተውን አስተዳደር በትግላቸው ተፅዕኖ ካሸነፉ በኋላ፣ በሠላማዊ የዜጎች ተሳትፎ እንዲቀጥሉ ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ወጣቶቹ አሁንም የለውጥ ሒደቱ የተጠናቀቀ አልመሰላቸውም፡፡ በዚያ ላይ ቀድሞ በገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎቹ መካከል ያለው ጫፍ የረገጠ መወነጃጀል የተጋጋለው ስሜታቸው በአዲስ ትርክት ተባብሶ ተቀጣጥሏል – “ለውጥ ፈላጊዎች” እና “አደናቃፊዎች” አሉ በሚል፡፡ እነዚህ በአመፃቸው አስተዳደሩን እንዲለውጥ ያስገደዱ ወጣቶች፣ “ለውጥ አደናቃፊዎቹንም” መቅጣት ያምራቸዋል፡፡ የደቦ ጥቃቶቹ መነሻ ይኸው ነው፡፡ ወጣቶቹን ለተቃውሞ ያነሳሱት የዳያስፖራ መገናኛ ብዙሀን ወጣቶቹን የማረጋጋትም ይሁን፣ ቀጣይ ድርሻቸው ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ምንም ሥራ አልሠሩም፡፡ የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎችም የለውጥ አደናቃፊዎች የመኖራቸውን ዜና እያጋነኑ በማራገብ የወጣቶቹ ያልሰከነ እርምጃ ላይ የስሜት ነዳጅ አርከፍክፈዋል፡፡
ከዚያም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ የደቦ ጥቃቶች በሚፈፀሙባቸው አጋጣሚዎች መንግሥት ሕጋዊ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ ማሳየት አለመቻሉ ደግሞ ወጣቶቹንም እንዳይረጋጉ፣ ቀሪ ዜጎችም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን እንዲፈሩ እያደረገ ነው፡፡
በሌላ በኩል በገዢው ፓርቲ ውስጥ የለውጥ አካል ነኝ የሚለው ቡድን ተቃዋሚዎቹን ማሳመን የቻለውን ያክል በፓርቲው ውስጥ የተለየ አቋም የሚያራምዱትን ማሳመን አልተቻለውም፡፡ ይህም በክልላዊ መንግሥታት መካከል የመጎሻሸም መንስዔ ሆኗል፡፡ የክልሎቹ መጎሻሸም በሚያስተዳድሯቸው ክልላዊ ብዙኃን መገናኛዎች ስለሚንፀባረቅ የየክልሉ ሕዝቦች መካከልም ቅያሜን እያበረከተ ነው፡፡ በየአካባቢው የሚነሱት ግጭቶች ዋነኛ መንስዔም በክልላዊ መንግሥታቱ መካከል ያለው ሽኩቻ ነው፡፡
እነዚህን ተቃርኖዎች ለማስታረቅ መንግሥት እና መገናኛ ብዙኃን የለውጡን ሒደት የሚገልጹበትን ትርክት ማስተካከል አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ችግሮቹ እየተባባሱ የመሔድ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡