/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ንጉሱ ጥላሁን የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ በማምራት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ(አዴሃን) እንዲሁም ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።
የልዑካን ቡድኑ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ ከአቶ የማነ ገብረአብ ጋር በተወያዩበት ወቅት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ መምከራቸውን የአማራ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በዚህም መሠረትም በቅርቡ በአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ እንደሚያቀና እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንዲሚመጣ ከስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታውቀዋል።
አቶ ንጉሱ ጨምረው እንደገለጹት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ(አዴሃን) ጋር ሰፊ ምክክር እንዳረጉ እና ወደ ሀገር ቤት ገብቶ በሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል።