/ያሬድ ኃይለማርያም_የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች/
በዶ/ር አብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል ባጭር ጊዜ ውስጥ በርካታና ከፍተኛ ግምት ሊሰጣቸው የሚችሉ ነገሮችን የከወነ ቢሆንም በበርካታ አደጋዎች እና መሰናክሎች የተከበበ ስለመሆኑ በርካታ ምልክቶችን እያየን ነው። በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከሚታዩት ሥርዓት አልበኝነት፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ዝርፊያ እና ከሕግ ያፈነገጡ ተግባሮች ባሻገር የክልል መንግስታት እርስ በራሳቸው ሲወነጃጀሉ እና አልፎ አልፎም ከማዕከላዊው መንግሥት ጋርም ጭምር ሲገፋፉ ማየት የተለመዱ ዜናዎች ሆነዋል። እንዲህ አይነቶቹ ተግባራት ከወዲሁ የሕግና የፖለቲካ መፍትሔ ካልተበጀላቸው ከእንቅፋትነት አልፈው እንደተራራ በመግዘፍ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የለውጥ ሂደት ባጭሩ ሊገቱት ይችላሉ።
በመጀመሪያ እንዲህ ያሉ የለውጥ እንቅፋት የሆኑ ክስተቶች ሊበራከቱ የሚችሉት ለምንድ ነው የሚለውን መመለስ ተገቢ ይመስለኛል። እንደ እኔ እምነት እነዚህ ችግሮች የለውጡን ሂደት እየተፈታተኑት ያለቱ ለውጡን እያካሄደ ያለው ኃይል ሙሉ የሆነ የፖለቲካ ሥልጣን በእጁ ስላልገባ ነው። አንድ አገርን ለሚመራ ቡድን የሥልጣን ኃይል ምንጮቹ ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው ውስጣዊ ኃይል ነው። ይኽውም ድርጅቱ በራሱ ጥንካሬ ያገኘው ጉልበት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ በድርጅታዊ ጥንካሬው እጅግ ደካማ የሆነ ኃይል ሌሎች ውጫዊ የሆኑ የኃይል ምንጮችን አሰባስቦ በመጠቀም ጉልበት ሊያገኝ እና ጠንክሮ ሊወጣ የሚችልበት ነው። በዶ/ር አብይ የሚመራው የለውጡ ኃይል ምንም እንኳን ድርጅታዊ ምንጩ አገሪቱን ለ27 አመታት ሲመራ የቆየው ኢሕአዴግ ቢሆንም በውስጡ በተፈጠረው ክፍፍል እና አለመግባባቶች የተነሳ የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ሊሆነው አልቻለም። በመሆኑም ይህን ክፍተት ለመሸፈን የግድ ከድርጅቱ ውጭ ያሉትን የተለያዩ ክፍሎች፤ በዋነኝነት ሕዝቡን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ ታዋቂ ሰዎችን እና አለም አቀፍ ማህበረሰቡን ከኋላ ማሰለፍ እና የኃይል ምንጭ ማድረግ ግድ ይለዋል። የዶ/ር አብይ የመደመር እና የጥላቻ ግንቡን እናፍርስ ዘመቻም ካለው ታላቅ አገራዊ ፋይዳ ባልተናነሰ በኢሕአዴግ ውስጥ የታጣውን ድጋፍ ለውጥኑ በሚደግፉ ኃይሎች ለማጥናከር የታለመም ጭምር ነው። የለውጥ ፈላጊው ኃይል ማመዘን ኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን አደናቃፊ ኃይል ይውጠዋል።
የዶ/ር አብይ አስተዳደር ምንም እንኳን የብዙዎቻችንን ቀልብ የሳበ እና ድጋፍም ጭምር የተሸረው ቢሆንም የአገዛዝ ሥርዓቱን ሙሉ ድጋፍ አለማግኘቱ የፖለቲካ አቅሙን የተፈታተነው ይመስላል። አንድ አገርን በማስተዳደር ላይ ያለ የፖለቲካ ኃይል ሙሉ ሥልጣን በእጁ ገብቷል ሊባል የሚችለው ቢያንስ ከዚህ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነገሮች ሲያሟላ ነው።
1ኛ/ የሥልጣን የበላይነት ዋናው እና ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው። ይህም ማለት በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እኩል ተሰሚነት፣ ተቀባይነት እና ሕግ የማስፈሰም ብቃት ሲኖረው ነው። አገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ በቅጡ ያጤንን ከሆነ የተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም የኢትዮ-ሱማሌ ክልል እና የትግራይ ክልል ከዚህ አፈንግጠው ለመቆየታቸው በርካታ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። በተጨማሪም በአንዳንድ ክልሎች የሚስተዋሉት የፉክክር እና የሥልጣን ሽሚያዎች እያንዳንዳቸው እራሳቸውን ችለው የቆሙ አገሮች አስመስሏቸዋል። በቅርቡ በሱማሌ ክልል የተከሰተው ትርምስ እና እልቂት እንዲሁም ከሳምንታት በፊት መቀሌ ኤርፓርት በቁጥጥር ስር የዋሉት የፌደራል መንግስቱ ታጣቂዎች ጉዳይ እና በወንጀል እየተፈለጉ መቀሌ የመሸጉት የቀድሞ ባለስልጣናት ጉዳይ ጥሩ ማሳያውች ናቸው። ዶ/ር አብይም በአደባባይ ሌቦችን መያዝ አልቻልንም። በየክልላቸው መሽገዋል ነበር ያሉት። ይህ ማለት መቀሌ ላይ ስልጣን የለኝም ማለት ነው።
2ኛ/ በሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል ለመደገፍ፣ ለማገዝ እና ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆነ ከፍተኛ የሰው ኃይል ሌላ የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ነው። በዚህ እረገድ ዶ/ር አብይ የተሳካላቸው ይመስለኛል። ምንም እንኳን ወደ ሥልጣን በሕዝብ ምርጫ የመጡ ሰው ባይሆንም በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ይሄን ያህል ህዝብን ያነቃነቀ፣ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተወዳጅነትን ያተረፈ፣ ከህጻን እስከ አዋቂ፣ ከምሁር እስከ ኃይማኖት አባቶች፣ መንግሥትን አጥብቀው ይቃወሙ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ሳይቀሩ ስሙን እየጠሩ ድጋፋቸውን የሰጡት መሪ ያለ አይመስለኝም። ይህን ድጋፍ ዘላቂ የኃይል ምንጭ እንዲሆን አድርጎ መቆየት ከባድ ቢሆንም የዶ/ር አብይን ተጽዕኖ ፈጣሪና የፖለቲካ መሪነት ብቃትም ማሳያም ይሆናል።
3ኛ/ ተጨባጭ፣ አሳማኝ እና አቃፊ የሆነ የፖለቲካ ምህዳር እና አገራዊ ራዕይ መቅርጽ ሌላኛው የኃይል ምንጭ ነው። አገሪቱ ያለችበትን ተጨባች ሁኔታ መሰረት ያደረገ፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈና አግላይ ያልሆነ የፖለቲካ ምህዳር መቅረጽ እና ከፖለቲካ አስተሳሰቦች ልዩነት ባሻገር ሁሉም የፖለቲካ ኃይል ሊስማማበት የሚችል አገራዊ እራዕይ መቅረጽ እና ወደዛ ለመድረስም የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መንደፍ የግድ ይላል። ይህ ተግባር ጊዜ እና የሁሉንም አካላት እርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሊመዘን አይችልም። ይሁንና መሰረቱ እየተጣለ ለመሆኑ ግን ከወዲሁ ማረጋገጫዎችን ማሳየት የግድ ይላል። ለእዚህም የተቃዋሚ ኃይሎች ወደ አገር ውስጥ መግባት እና እርቅ መውረዱ፣ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት እና ከመንግስት ጋር የተጀመሩት መቀራረቦች በጥሩ ጎን ቢጠቀሱም ብዙ ሥራዎች ግን ይቀራሉ። ሳይዘገይም አገራው የምክክር እና የውይይት ጉባኤ መካሔድ አለበት። ጉባዔው በሚሰይመው አካል በኩል የአገሪቱ የዲሞክራሲ ፍኖተ ካርታ ይነደፋል። አሁን ባለው ሁኔታ ከሆነ አብዛኛውን ነገር የለውጡ ኃይል ብቻውን የያዘው ይመስላል። ይህ አካሄድ አደገኛና ሌሎች መዘዞች ስለሚኖሩት ከወዲሁ ይታሰብበት።
4ኛ/ ከላይ የተጠቀሱትን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች በአግባቡ እና በጊዜው ለመጠቀም የሚቻለው እያንዳንዱ እርምጃ በእውቀት፣ በጥናት፣ በጥበብ እና በተለያዩ ክህሎቶች ሲደገፍ ብቻ ነው። ማህጸነ ለምለም የሆነችው ኢትዮጵያ በሁሉም የሙያ ዘርፍ የካበተ እውቀት እና ችሎታ ያላቸው፤ ከአገራቸውም አልፈው ለሌላው አለም የሚተርፉ ሰዎች ስላሏት እነዚህን ኃይሎች ማሳተፍ እና በጥንቃቄ መጠቀም የለውጡን ኃይል አቅም ያጎለብተዋል። ለዚህም አንዳንድ በጎ ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው። ምሁራን በአገሪቱ ጉዳይ ሃሳብ እንዲሰጡ እና ውይይቶችን እንዲያደርጉ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ እድሉን እያመቻቹ ነው። ሆኖም ሃሳብ ከመስጠት ባለፈ የተሳታፊነት ድርሻቸው እንዲጎለብት ሰፊ እቅድ ተይዞ ሊሰራበት ግድ ይላል።
5ኛ/ የመንግስት ሕግ የማስከበር፣ ፍትሕ፣ ሰላም እና ሥርዓት የማስፈን አቅም ነው። ጊዜው የሽግግር ወቅት ነው ብለን ብናስብም የዶ/ር አብይ አስተዳደር በዚህ እረገድ ብዙም መሻሻሎችን ያሳየ አይመስለኝም። በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም በሰላም እጦት እየተናጡ ነው። የሳምንቱ ሰባት ቀናት የሚያልቁት በተለያዩ የሁከት እና የብጥብጥ ሰበር ዜናዎች ነው። የገዳዮቹ ማንነት ተቀየረ እንጂ አሁንም ግድያ አልቆመም። ዝርፊያ፣ ዜጎችን ማዋከብ፣ ከቄያቸው ማፈናቀል እና ጥቃት መሰንዘር፣ ንብረቶችን ማውደም፣ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር እና የአገር ሃብትና ገንዘም ማሸሽ የእለት ተእለት ክስተቶች ሆነዋል። ይህ ሕግ እና ሥርዓትን በማስከበር ረገድ እየታየ ያለው ክፍተት እያደር ወደ ለየለት ሥርዓት አልበኝነት እና ነውጥ ሊያመራ ይችላል። እዛ ከደረስን አገሪቱ ለዳግም ትርምስ ትዳረጋለች። ያንን ሊሸከም የሚችል ጫንቃ ያላት አይመስለኝም። የመንግሥትንም የፖለቲካ ኃይል ክፉኛ ያዳክመዋል። ያ ደግሞ ለውጡ ላልተዋጠላቸው ኃይሎች ምቹ እድልን ይፈጥራል።
6ኛ/ ሌላው ወሳኙ የፖለቲካ ኃይል ምንጭ የመንግስት የኢኮኖሚ አቅም ነው። ይህ አንዱ የዶ/ር አብይን አስተዳደር የሚፈታተን ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለ27 አመታት ተንሰራፍቶ በቆየው የወያኔ አገዛዝ በፈጠራቸው ጥቂት ከበርቴዎች እጅ በመውደቁ የለውጡን ሂደት አቅጣጫ ለመወሰኝ የሚያስችል አቅምም ፈጥሮላቸዋል። በተለይም እነዚህ በሙስና እና በዝርፊያ የአገር ሃብት የተቀራመቱ ጥቂት ከበርቴዎች ለሃብታቸው ደህንነት ዋስትና ይሰጣቸው የነበረው ህውኃት ለውጡን የጎሪጥ እያየ ወደ መቀሌ መከተሙ ባለሃብቱ የዘረፉትን ገንዘብ እንዲያሸሹ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። በየቀኑ ሲሸሽ ተያዘ የሚባለው እጅግ ከፍተኛ ግምት ያለው የውጭ ምንዛሪ የእነዚህ አካላት ለመሆኑ ብዙም አያጠራጥርም። እንግዲህ ሳይያዝ አምልጦ ከአገር የወጣውን እና በየቤቱ የተደበቀውን የአገር ሃብትና ገንዘብ መጠን መገመት ከባድ አይሆንም። ይህ ሃብት የማሸሽ መሰሪ አድራጎት ዋነኛ ግቡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሆነ በትር በማሳረፍ የለውጡን ኃይል ከእርምጃው ለመግታት የታለመ ይመስላል። በኢኮኖሚው ላይ የሚደረገው አሻጥር በዚህ ከቀጠለ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን አገሪቷንም ክፉኛ ሊጎዳት እንደሚችል መገመት ይቻላል።
7ኛ/ የመጨረሻው እና ወሳኝ የሆነው የኃይል ምንጭ ለአገር ሉዐላዊነት፣ ለሕዝብ ደህንነት እና ለሰላም የወገነ የመከላከያ እና የጸጥታ ኃይል መኖር ነው። ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚሰራ የታጠቀ ኃይል ለፖለቲካ መሪዎቹ ትልቅ ጉልበት ነው። ለለውጡም ትልቅ ዋስትና ይሆናል። ይህን በተመለከተ አንዳንድ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ይስተዋላል። በተለይም የጸጥታ ኃይሎች ለዜጎች መብት እና ነጻነት መከበር እና ለሰዎች ደህንነት ዘብ የመቆም የተጣለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ አይሰተዋልም። በቅርቡ በጠራራ ፀሀይ በሻሸመኔ ከተማ አንድ ወንድማችን ላይ አሳፋሪ ተግባር ሲፈጸም በሥፍራው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ያሳዩት ቸልተኝነት እና ዝምታ የድርጊቱ ተባባሪዎች እንደሆኑ በግልጽ ያሳያል።
ከእነዚህ ነጥቦች በመነሳት ዶ/ር አብይ የሚመሩት የለውጥ ኃይል የአገሪቱን ሙሉ የፖለቲካ ሥልጣን በእጅ አስገብቷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ያፈነገጡ ክልሎች እና የገዢው ፓርቲ አባላት ወደ መስመር ካልገቡና ካልተደመሩ፣ የጸጥታና የመከላከያ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ መስራት ካልጀመሩ፣ በየሥፍራው ነውጥን የሚቀሰቅሱ፣ በሰው ሕይወት እና በሕዝብ ንብረት ላይ ውድመት የሚያደርሱ ኃይሎች በሕግ ጥላ ሥር ውለው ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ካልተቻለ ለውጡ ግማሽ ብስል ግማሽ ጥሬ ነው የሚሆነው። ሌላው ወሳኝ ነገር በዶ/ር አብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል እና ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ተጣጥመው ነው ውይ እየሰሩ ያሉት የሚለው ጉዳይ ነው። እንደ እኔ ትዝብት ኢሕአዴግ ገና የተደመረ አይመስለኝም። ኦነግና ግንቦት 7 ሳይቀድሙት አልቀረም። ከሕዝብ ቁጣ ታድገው የሥልጣን እድሜዮን ያራዝሙልኛል ያላቸው ዶ/ር አብይ፣ የአቶ ለማ እና የአቶ ደጉ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር ተውጠው እና በሕዝብ ተፈቅረው ሌላ ደሴት ላይ ያሉ ይመስላል። ሕውኃት ወልዳ እና በባህሪዋ ቀርጻ ያሳደገችው ኢሕአዴግ ደግሞ ሌላ ደሴት ላይ ያለ ይመስላል። ነገሩ እንዲህ ከሆነ የሰሞኑ የዶ/ር አብይም ከሕዝባዊ መድረኮች መሰወር ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
አብዛኛዎቹ የዶ/ር አብይ የአደባባይ ንግግሮች፣ የፖለቲካ አስተሳሰባቸው እና ከሕዝብ ጋር እየፈጠሩት ያለው ግንኙነት በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር የሚታሰቡ አይመስሉም። ኢሕአዴግ የዶ/ር አብይን ራዕይም ሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመሸከም የሚያስችል ቁመና ያለው አይመስለኝም። ስለዚህ ድርጅቱ ለራሱ ህልውና ሲል ዶ/ር አብይ የሚነዱትን አዲስ የለውጥ ባቡር መቆጣጠርና ማስቆም ባይችል እንኳ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ዶ/ር አብይን ማርሽ ቀንስ ማለቱ አይቀርም። ዞሮ ዞሮ ሕዝብ ከዶ/ር አብይ ጎን እስከቆመ እና ሌሎቹንም የኃይል ምንጮች በአግባቡና በጥንቃቄ እስከተጠቀሙባቸው ድረስ ባቡሩ ፍጥነቱ ቢቀንስም ወደፊት መሄዱን ግን ማንም ሊያስቆመው አይችልም።
ቸር እንሰንብት!