/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሁለት ሲኖዶስ ወደ አንድ ሲኖዶስ ከተጠቃለለች በኋላ ሁሉን ስርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል ሲሉ የዋሽንግተንና አካባቢው እንዲሁም የካሊፎርኒያ ሊቀጳጳስ ብጹዕዎ አቡነ ፋኑኤል መናገራቸዉን አድማስ ሬዲዮ ዘገበ፡፡
ሊቀጳጳሱ በዚህ ሰሞን ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ባሰራጩት መመሪያ እንደገለጹት ከሆነ፣ በአንድ ካህንና በአንድ ዲያቆን ብቻ የተከፈቱ ቤተክርስቲያናት ካሉ፣ ታቦታቸውን ይዘው ወደ ሚቀርባቸው ቤተክርስቲያን መጠቃለል ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ከዚያም በላይ በተለይ ዋሽንግተን ፣ አትላንታ፣ ዳላስና ሲያትል እንዲሁም ካሊፎርኒያ ግዛትን በስም በመጠቅስ በቂ አብያተ ክርስቲያናት ስላሉ ከዚህ በኋላ ሊከፈቱ የሚችሉ ቤተክርስትያናት የጠበቅ መስፈርት ማሟላት ይኖርባቸዋል ማለታቸው ተገልጿል።
አዲስ የሚከፈተው ቤተክርስቲያን በአቅራቢያው ካለ ሌላ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቢያንስ የ45 ደቂቃ የመኪና ርቀት ፣ከሁለት ካህናትና 3 ዲያቆናት የሚኖሩትና 50 በላይ ምዕመናን ሊኖሩት ይገባል ተብሏል።
ብጹዕዎ አቡነ ፋኑኤል አያይዘው እንደገለጹት ቤተክርስቲያናት የሚሰይምበት ስምም በከተማው ውስጥ ወይም በተጠቀሰው ርቀት በተመሳሳይ ስም የተሰየመ ቤተክርስቲያን ያልተሰየመበትም ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ላለፉት 26 ዓመታት ለሁለት ተከፍሎ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሐምሌ ወር እርቀ ሰላም በማውረድ አንድ መሆኗን ማወጇ ይታወሳል።