/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከሶማሌ ክልል 11 ዞኖች ከተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ጋር ተወያዩ። በአዲስ አበባ ዛሬ በተካሄደው ውይይት የሀይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ ማህበራት ተወካዮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች መሳተፋቸው ታውቋል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በሶማሌ ክልል የሚወሰደው እርምጃ ሌሎች የኦሮሞ፣አማራ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉልና አፋር ክልሎች የሚማሩበት እንደሚሆን ተናግረዋል። ጠ/ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የሁሉም ክልሎች ባለስልጣናት ህግንና ሀይማኖትን የማክበር ግዴታ አለባቸው ብለዋል።
በውይይቱ ላይም አዲስ የተሾሙት የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ኡመር እንዲሁም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ተገኝተዋል።
በሌላ በኩል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ዛሬ ባውጣው መግለጫ፤ ለአቶ ሙስጠፋ ኡመር አዲሱ አስተዳደር ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት በየቀኑ እየተሻሻለ መምጣቱንና ጅጅጋ፣ ድሬዳዋና ሐረርን ጨምሮ በምስራቅ ኢትዮጵያ ላልፉት 20 ቀናት ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ መስራት መጀመሩ ታውቋል።