“ለኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ይቅርታ አይደርግላቸውም” ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ

“ለኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ይቅርታ አይደርግላቸውም” ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠ/ሚ አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ በጽ/ቤታቸው ሰጥተዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ለጠ/ሚኒስትሩ ከቀረበላቸው ጥያቄዎች መካከል በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የምህረት ወይም የቅርታ አዋጅ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ያካትተዋ ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ህገ-መንግስቱ በቀይ ሽብር ለተሳተፈ ሰው ምህረትን ስለሚከለክል አሁን ባለው ሁኔታ እሳቸውን አያካትትም ብለዋል።

 በመስቀል አደባባይ ባለፈው ሰኔ 16 በደረሰው የቦንብ ፍንዳታና በኢንጂነር ስመኘው ግድያን በተመለከተ መግስታቸውና የመስኩ ባለሙያዎች በትኩረት እየተከታተሉ እንደሆነ እና በቅርቡም መግለጫ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። የኢንጅነሩን ቤተሰቦችም በስልክ ማነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

ባለፈው ወር በመቀሌ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ታግተዋል ስለተባሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የተጠየቁ ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ መቀሌ ለስራ ሄደው እንደነበረና የክልሉ የፀጥታ አባላት ስለሁኔታ እውቅና ስላልነበራቸው ጠይቀዋል እንጂ ታግተዋል የባለው ውሸት ነው ብለዋል። የፖሊስ አባላትም ሰራቸውን ጨርሰው ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለ ህዳሴው ግድብም ጥያቄ የተነሳላቸው ሲሆን በግድቡ ላይ ችግር ወይም መዘግየት እንደነበረ አሁን ሳይሆን ከሦስት ዓመታት በፊት ችግር እንዳለ ብንገመግምም መወሰን ሳንችል ቆይተናል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ለውጥም መስመር እየያዘ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አብዲ መሃመድ ኡመር እጣ ፋንታ በህግ ይፈታል ብዋል። አብዲ መሃመድን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ ወንጀል የፈጸሙ አካላት በህግ ይጠየቃሉ ብለዋል።

  አሁን ላይ ለአዲስ አበባ ከንቲባ እንደተሾመ የሚወራው ስህተት ነው፡፡ ቀጣዩ ምርጫ እስኪደርስ ከተማዋ በባላደራ አስተዳደር ከምትመራ ሶስት ወጣት ፖለቲከኞች ተቀምጠዋል፡፡ ለጊዜው የተቆጠሩ የህዝብ ስራዎችን ይዘው ወደ ስራ ገብተው ውጤት እያሳዩ ነው፡፡ በቀጣዩ ምርጫ የአዲስ አበባ ህዝብ የራሱን ከንቲባ ይሾማልም ብለዋል።

ቋንቋን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “በአለም ላይ ከአንድ በላይ ቋንቋዎች በአንድነት የብዙ አገራት የስራ ቋንቋ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በኢትዮጵያም አፋን ኦሮሞ የስራ ቋንቋ ይሁን የሚል ጥያቄ አለ፤ ሀሉም ወገን ከአንድ በላይ ቋንቋ ለማወቅ ቢጥር መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ አፋን ኦሮሞን የስራ ቋንቋ ለማድረግ የህገ መንግስት ማሻሻያ ስለሚፈልግ አሁኑኑ ይሁን የሚባለው ተገቢ አይደለም፡፡አማርኛን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአንድ ቋንቋ በላይ ለማወቅ መጣር አለበት፡፡ ሁሉም ነገር ህግና አሰራርን ተከትሎ የሚታይ ጉዳይ ነው” ብለዋል። የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት ነፍጣቸውን ጥለው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ነው፡፡ እነሱን የሚደግፍ ተቋምም ይደራጃል ብለዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ እነዚህንና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው መልሰዋል።

LEAVE A REPLY