የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ የዘነጋቸው አራቱ የከፍተኛ ትምህርት ችግሮች

የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ የዘነጋቸው አራቱ የከፍተኛ ትምህርት ችግሮች

(በዚህ ጦማር ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ችግሮች ናቸው ተብለው የተገለፁት ጸሓፊው በ11 ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተሳትፎው በሦስት ዩኒቨርሲቲዎች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እና ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ) በሰራበት ጊዜ ባየው እና ባጋጠመው፣ በትምህርት ዓለም ካፈራቸውና ከ10 በላይ በሚሆኑ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ተበትነው ካሉ የትምህርት ዓለም ወዳጆቹ ጋር ካደረገው ኢ-መደበኛ ውይይት፣ እና በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ በተደረጉ ውይይቶች ከተነሱ ሀሳቦች በመነሳት እንጂ በትምህርት ጉዳዮች ላይ ጥናት እንዳደረገ ባለሙያ እንዳልሆነ አንባቢ እንዲገነዘበው፡፡ በየመሃሉ የገቡት የእንግሊዘኛ ቃላትም በፍኖተ-ካርታው ውስጥ እንደሰፈሩት ሆኖ የአማርኛ ፍቺ በማስቀመጥ ሀሳብ ላለማዛባት የተደረገ ነው፡፡)

ፍኖተ-ካርታው ስለከፍተኛ ትምህርት ምን ይላል?

የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ (ለውይይት የታተመው ጨመቅ (Executive Summary)) ውስጥ ከተካተቱ ዘርፎች መካከል የከፍተኛ ትምህርት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በሚያነሳው ንዑስ-ርዕስ ስር በ8 ጭብጦች ላይ ‘ተግዳሮቶች’፣ ‘ስኬቶች’፣ እና ‘የወደፊት አቅጣጫዎች’ ተገልፀዋል፡፡ ጭብጦቹም የከፍተኛ ትምህርት (1) ተደራሽነት፣ (2) ፍትሐዊነት፣ (3) በብዝሀነት ውስጥ ያለ አንድነት፣ (4) ጥራት፣ (5) ተገቢነት፣ (6) ተወዳዳሪነት፣ (7) ጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት እና (8) በጀት የሚሉ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ፋታ የማይሰጠው፣ በፖሊሲዎች መቀያየር ያልተሻሻለው፣ ምንም እንኳን በፍኖተ-ካርታው ውስጥ ሰፋ ያለ ቦታ ቢይዝም አሁንም ይሻሻላል ብዬ ተስፋ የማላደርግበት ጭብጥ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ነው፡፡

በፍኖተ-ካርታው የከፍተኛ ትምህርት ስኬቶች (በ15 ዓመት) ተብለው የተጠቀሱት:- የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት፣ የቅድመ-ምረቃ ስርዓተ-ትምህርት Harmonization፣ Modular Teaching፣ ተከታታይ ምዘና፣ Peer Learning፣ እና የጥራት ማረጋገጫ መንገዶች መዘርጋት ናቸው፡፡ ስኬቶች ከተባሉት ውስጥ ግማሹ (Harmonization፣ Modular Teaching፣ እና የጥራት ማረጋገጫ መንገዶች መዘርጋት) ለትምህርት ጥራት መውደቅ ዓይነተኛ ሚና የተጫወቱ ድክመቶች እንጂ ስኬቶች እንዳልነበሩ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

Harmonization፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስገዝነት (Autonomy) የደፈጠጠ፣ በሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች አንድ ዓይነት ትምህርት ይስጡ በሚል የትምህርት ብዝሀነትን ያጠፋና የተቋማቱን አቅም፣ የሰው ሀይል አደረጃጀት፣ የሚገኙበት ቦታ እና ያላቸውን ልምድ ያላገናዘበ ነበር፡፡ Modular Teaching፡- “የነቶሎቶሎ ቤት” እንደሚሉት ተገቢው ዝግጅት ሳይደረግበትና በቂ ሀብት ሳይዘጋጅለት በጥድፊያ የተተገበረ፣ ከበፊቱ የማስተማር ዘዴ በአንድ ጊዜ ሲቀየር በቂ ስልጠና ሳይሰጥ የተጫነ እና ‘ግራ የተጋባ’ ፖሊሲ ነበር፡፡ የጥራት ማረጋገጫ መንገዶች መዘርጋት፡- ይህንን “መንገዶቹ ከተዘረጉ ጥራቱ የት ገባ ታዲያ?” በሚል ጥያቄ ልለፈው፡፡ ትልቁ ራስ ምታት እስካሁን የከፍተኛ ትምህርት ችግርን ብልት አግኝቶ ፍቱን መደሃኒት ማስቀመጥ አለመቻሉ ይመስለኛል፡፡

ፍኖተ-ካርታው ከስኬቶቹ ቀጥሎ በትምህርት ጥራት ላይ የታዩ ችግሮችን ይዘረዝራል፡፡ እነሱም፡- ኩረጃ፣ የግሬድ ቁለላ (Inflated Grades)፣ ተቀጣሪነትን እና ክህሎትን ያላማከለ ስርዓተ-ትምህርት፣ ITን ለትምህርት የሚያውሉ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት ስልቶች አለመኖራቸው፣ በቂ ያልሆነ University-Industry ትስስር፣ እና ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ እውቀት ሳይኖራቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ናቸው፡፡

ለእነዚህና በየመሐሉ እና በገደምዳሜ ለተጠቀሱ ተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ችግሮች አዳዳዲስ ፖሊሲዎች ተቀምጠዋል፡፡ የዚህ ጦማር ዓላማ የተዘነጉትን ችግሮች ብቻ መጥቀስ ስለሆነ ፖሊሲውን ለመለወጥ የተቀመጡትን መፍትሔዎች ተገቢነታቸው አልተመረመረም፡፡ በትምህርት ጉዳዮች ላይ ጥናት ያደረጉ ቢተነትኗቸው እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

የተዘነጉት አራቱ ችግሮች

በቂ ጥናት ባለመደረጉ ወይም ችግሮቹ ጭራሹኑ በአጥኚዎቹ በመዘንጋታቸው ወይም ደግሞ ቢታወቁም ችላ የተባሉ ነገር ግን የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት እንደ ‘አዚም እስራት’ አንቀው የያዙ፤ ፊት የዞረባቸው ችግሮች አሉ፡፡ አራቱን እኔ እጠቅሳለሁ፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለይም በትምህርት ጉዳዮች ላይ የሚመራመሩ ሰዎች የታዘቧቸውን ተጨማሪ ችግሮች እንዲጠቅሱ እጠይቃለሁ፡፡ እነዚህ ችግሮችም የማስተማሪያ ቋንቋ (Medium of Instruction)፣ ለሀገር-በቀል እውቀት፣ ባህል፣ እና ታሪክ ቦታ ያለው የትምህርት ስርዓት አለመኖሩ፣ የማስተማር ዘዴ (Teaching Method)፣ እና ያልመረጡትን ትምህርት መማር (Misplacement) ናቸው፡፡

ሀ – የማስተማሪያ ቋንቋ

በኢትዮጵያ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ የማስተማሪያ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው፡፡ በፍኖተ-ካርታው እንደተገለፀው 10ኛ ክፍልን የሚያልፉ ተማሪዎች በእንግሊዝኛ በትክክል ማንበብ እና መፃፍ እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ እነዚሁ ተማሪዎች ከሁለት አመት በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ሲገቡ የአንድን የትምህርት ዘርፍ ዕውቀት ተረድቶ በቋንቋው ምልከታቸውን ለመፃፍ/ምርመር ለማድረግ ቀርቶ ራሳቸውን ለማስተዋወቅም እንደሚቸግራቸው ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት መምህራን ይመሰክራሉ፡፡

ይህንን እውነታ ዘንግቶ የከፍተኛ ትምህርት የማስተማሪያ ቋንቋን የተመለከተ ‘አቅጣጫ’ ሳያስቀምጡ ለ12 (15) ዓመታት የሚቆይ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ፍየል ወዲህ፣ ቅዝምዝም ወዲያን ያስተርታል፡፡ ፍኖተ-ካርታው የተዘጋጀው የማሌዥያና ቪዬትናምን የትምህርት ፖሊሲዎች እንደ ምሳሌ ተከትሎ ነው ከተባለ የእነዚህ ሀገራት የከፍተኛ ትምህርት የማስተማሪያ ቋንቋ ፖሊሲ እንደምን ሳይታይ ተዘለለ? በቪዬትናም አብዛኞቹ በተለይ የህዝብ ዩኒቨርሲቲዎች በሀገራቸው ቋንቋ የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ በማሌዢያም ቢሆን (የቪዬትናሙን ያክል ባይሆንም) ከእንግሊዝኛ ይልቅ በራሳቸው ቋንቋ የማስተማር ልምድ አላቸው፡፡

ጥቆማ፡- ችግሩ እንደሌለ አድርጎ ባለማወቅም ይሁን በንዝህላልነት ከማለፍ ይልቅ አሁንም ጥልቀት ያለው ጥናት አድርጎ የከፍተኛ ትምህርት ማስተማሪያ ቋንቋ ችግርን በትክክል የሚያይ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡

ለ – ለሀገር-በቀል እውቀት፣ ባህል፣ እና ታሪክ ቦታ ያለው የትምህርት ስርዓት አለመኖሩ

ይህ ችግር በሀገር-በቀል ቋንቋ ከመማር ጋር ጥብቅ ዝምድና እንዳለው ልብ ይሏል፡፡ ዛሬም ከኢትዮጵያ የተፋታ፣ የራስን ጥሎ የሰውን የሚያንጠለጥል፣ ለምዕራቡ ራሱን አሳልፎ የሰጠ የትምህርት ስርዓት ነው ያለን፡፡

ከፍተኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ‘ሀ’ ብሎ ሲጀመር አፄ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዩኒቨርሲቲ መርቀው ሲከፍቱ ተቋሙ እንደምን ሆኖ እንዲያገልግል የነበራቸውን ህልም እንዲህ ገልፀው ነበር፡-

“ይህ ዛሬ መርቀን የምንከፍተው ዩኒቬርሲቲ በኢትዮጵያ ታርክና ባህል ላይ የተመሰረተና ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ ያጠራቀመችውን የታሪክና የባህል ቅርስ በረቂቅ በመመራመር ወደ ኋላ መለስ ብሎ በማስተዋል ዘመን አመጣሽ የሆነውን አተኩሮ በመመልከት የወደፊቱን የኢትዮጵያ ሕዘብ ታሪክ አቅጣጫውንና የሚይዘውን መልክ ለመምራት የሚቻልበትን ዕውቀት የሚገበዩበት የትምህርት አደባባይ ነው፡፡”

ራሱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ሆነ በ ’አምሳሉ’ የተሰሩት ኋላ የተፈጠሩት ዩኒቨርሲቲዎችም በትምህርት ሚኒስቴር የተሳሳተ ፖሊሲ እየተመሩ፣ ሀገር-በቀል ዕውቀትን ከውጪው ጋር አጣምሮ ስለመስጠት የተናገሩትን ከቁብ ሳይቆጥሩ ዳክረው ዳክረው እዚህ የደረሰው የትምህርት ስርዓት ገና ለመጪዎቹ 12(15) ዓመታት በተሳሳተው መንገድ ሊያዘግም እንደሆነ የፍኖተ-ካርታውን ጨመቅ ያየ ይጠረጥራል፡፡

ይህን እንደምን አድርገን እንቀይረው ቢባል ይህን ለማስረዳት ዶ/ር እጓለን በረጅሙ መጥቀስ ያሻል፡-

“በተፈጥሮ ዘይትነት ያለው ዛፍ አለ፡፡ፍሬ ማፍራት ስለተሳነው ቅርንጫፎቹን ይቆርጡአቸዋል፡፡ በነሱ ፈንታ አውልዓገዳም የምድረበዳ ዛፍ በዘይቱ ግንድ ላይ ተቀጥሎ እንዲያድግ ይተክላሉ፡፡ ተቀፅላው የስሩ ህይወት ተካፋይ ስለሚሆን ዘይትነትንም ያገኛል፡፡ ግን ፈርቶ መኖር አለበት፡፡ በቅርንጫፍነቱ መኩራት አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ሥር ቅርንጫፍን ይሸከማል እንጂ ቅርንጫፍ ሥርን አይሸከምም፡፡ ይህ በጣም ረቂቅና ደግሞም ጉልህ የሆነ ምሳሌ ለጠቀስነው ችግር የታመነ መፍትሔ ነው፡፡

“ለኛ የተፈጥሮ ዘይትነት ያለው ዛፍ የሀገራችን ስልጣኔ ነው፤ ተቀፅላው በሱ ላይ ተጣብቆ የሥሩ የዘይቱ ተካፋይ መሆን አለበት፡፡ ብቻውን ቢቆም አውልዓ ገዳም፤ ወፍ አባቱ፤ የምድረ በዳ ቅጠል ሆኖ ይቀራል፡፡ ከኢትዮጵያ ሊቃውንት ‹‹እለ እምፍጥረቶሙ ዘይት›› ከሚገኘው ዕውቀት ጋር አዲሱ ከምዕራብ የሚመጣው የሐሳብ ዘዴ ሲፃመር ሲዋሐድ፤ የዕውቀት ዛፍ ይለመልማል ሲያዩት እንኳ ለዓይን ያስደስታል፡፡”

በፍኖተ-ካርታው ከኢትዮጵያ ስርዓተ-ትምህርት ላይ የባዕድን እጅ ለማንሳት የተተለመ አንድም እቅድ እልተቀመጠም፤ ይባስ ብሎ በባዕዳን ስርዓት ላይ ጥገኝነት የሚፈጥር እና ውጪን የሚያማትር ዕቅድ አዚህም እዚያም ተቀምጧል፡፡ ይሄን ሳይፈቱ ለ12 (15) ዓመት መቀመጥ በትውልድ ዓይን ያሳጣል፤ አላዋቂነትም ነው፡፡ የትምህርት ስርዓትን ሀገር-በቀል ስለማድረግ ወይም ከምዕራቡ ጋር አዛምዶ መስጠት ስላለው አስፈላጊነት ያጠኑ እና የፃፉ ኢትዮጵያውያን በዚህ ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ወቅት እንዲሳተፉ አለመደረጉ ይህ ችግር ቸል እንዲባል አስተዋፅኦ ያለው ይመስለኛል፡፡

ጥቆማ፡- ለጥንት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ጆሮ ያለው እና ከባዕድ ወደ ኢትዮጵያ “ዕውቀትን” ከማሸጋገሪያነት ይልቅ የኢትዮጵያ የሆነን ከባዕድ “ጠቃሚ ዕውቀት” ጋር የማጣመሪያ ዘዴን የተከተለ የትምህርት ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ፍኖተ-ካርታውን ለማሻሻል በሚደረጉ ውይይቶች ላይም ትምህርትን ሀገር-በቀል ስለማድረግ ያገባኛል ባይ ኢትዮጵያውያን ምክር ቢሰበሰብ ብናተርፍ እንጂ አንከስርም፡፡

ሐ – የማስተማር ዘዴ

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎችን የግል ችሎታና ክህሎት የሚያበለፅጉ፤ አንድን ዕውቀት ወደራሳቸውና ሀገራቸው አውድ ገልብጠው በራሳቸው ፈጠራ እንዲመራመሩ፣ እንዲጠይቁ፣ እና እንዲራቀቁ የሚያደርጉ የማስተማር ዘዴዎች የሉም! የመምህራኑ የትምህርት ስነ-ዘዴ ዝግጅት ማነስ፣ በቂ የትምህርት ቁሳቁሶች እና መጽሓፍት አለመኖራቸው እና የማስተማር ዘዴን ከቁብ የሚቆጥር ፖሊሲ አለመኖሩ ይህ አይነቱ የማስተማር ዘዴ እንዳይኖር አስተዋፅዖ አላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት በተማሪዎች ጭንቅላት ውስጥ “ዕውቀት” ከማጨቅ ባለፈ ጭንቅላታቸውን ተጠቅመው ዕውቀቱን እንዲመረምሩ እና እንዲጠቀሙበት አልሆነም፡፡

በተቋሙ ወይም በመምህራኑ በሚሰጧቸው ቅንጭብ ጽሑፎች ተገድበው፣ የተሰጣቸውን ብቻ እንዲያመነዥኩ እየተደረገ፣ ተገቢነታቸው እና በቂነታቸው ያልተገመገሙ መልመጃዎች እየሰሩ፣ በፈተናዎችም የተማሩትን ብቻ ቃል በቃል እንዲመልሱ እየተደረገ፣ ለራስ፥ ለቤተሰብ እና ለሀገር ረብ ያለው ስራ የሚሰሩ፣ ለኢትዮጵያ እና ለዓለም የሚበጅ ሀሳብ የሚያፈልቁ፣ እና የኢትዮጵያውያንን አዕምሮ የሚያረሰርስ እውቀት የሚያበለፅጉ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃንን ማግኘት የማይታለም ነው፡፡

ጥቆማ፡- አሁንም በማሌዥያ እና በቪዬትናም ሳይገደቡ፣ ከለብለብ ጥናት ይልቅ ጥልቀት ያለው፣ በጥቂት ናሙናዎች ያልተገደበና መምህሩንም ተማሪውንም ያካተተ ጥናት ሰርቶ የከፍተኛ ትምህርት የማስተማር ስነ-ዘዴን መከለስ ያስፈልጋል፡፡

መ – ያልመረጡትን ትምህርት መማር

ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲመደቡ በመጀመሪያ ወደ ኮሌጆች ወይም ሁለት እና ሶስት ኮሌጆችን ወደሚይዙ ምድቦች ነው፡፡ ቀጥሎ በምድቡ ወይም ኮሌጁ ስር ያሉ ትምህርት ክፍሎችን ይመርጣሉ (አንዳንድ ጊዜ እስከ 20 የሚደርሱ ትምህርት ክፍሎች ለምርጫ ይቀርቡላቸዋል) ፡፡ ምደባው ከፍላጎት ይልቅ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤታቸውን መሰረት ያደረገ ይሆናል፡፡

በዚህ መሠረት በሚደረግ ምደባ በየዓመቱ ከ85-90 በመቶ የሚሆኑት (በግል ልምዴ ባየሁት) ባልመረጡት የትምህርት ክፍል ይመደባሉ፡፡ ይህም የከፍተኛ ትምህርትን የሀገር ሀብት ብክነት ከማድረግ እና የትውልድን እድገት ከማምከን የተለየ ትርጉም የለውም፡፡

ጥቆማ፡- ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተማሪ ዛሬውኑ የመረጠውን ብቻ አንዲማር የሚያደርግ ስልት ማምጣት አለበት አይባልም፡፡ ነገርግን አብዛኛው ተማሪ የመረጠውን ቢማር የበለጠ ብቁ፣ የበለጠ አዋቂ፣ የበለጠ ተመራማሪ እንደሚሆን አስረጂ መጥቀስ አያሻም፡፡ ይህንን የተማሪ ምደባ ችግር የሚቀርፍ ሁነኛ መፍትሔ ማስቀመጥ የፍኖተ-ካርታው አንድ ተግባር መሆን አለበት፡፡

መደምደሚያ

የማይፈልገውን የትምህርት አይነት በቅጡ በማያውቀው ቋንቋ እየተማረ፤ የግል ክህሎቱንና የፈጠራ ችሎታውን ያላገናዘበ የ‘ዕውቀት ማጨቅ’ የማስተማር ዘዴ ባለበት፤ ከሀገሩ መንፈስ የራቀን ትምህርት የሚማርን ተማሪ እስከመቼ ያስመርቋል? በዚህ መንገድስ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን እንደምን ይቀርፏል? በዚህ ዓይነቱ የትምህርት ስርዓት ሀገርን እስከመቼ ይበድሏል? እንደምንስ ለኢትዮጵያ ስልጣኔን መሰረት የሚጥል ወይም ለስልጣኔው መበልፀግ ጉልህ ድርሻ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ስርዓት አይኖረንም?

(ምንጭ፦ጎበና ስትሬት)

LEAVE A REPLY