የአቶ በረከት ክስ እና የአቶ ንጉሱ ጥላሁን መለሽ

የአቶ በረከት ክስ እና የአቶ ንጉሱ ጥላሁን መለሽ

በቅርቡ ከብአዴን ማዕካላዊ ኮሚቴ የተባረሩት አቶ በረከት ስምዖን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ቀርበው በብአዴን መሪዎች ላይ ክስ እያቀረቡ ይገኛሉ።የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ንጉሱ ጥላሁን የአቶ በረከትን ውንጀላ በተመለከተ አጭር ምላሽ ሰጥቷል።

   ——————

ሰሞኑን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ በርከትን እና አቶ ታደሰን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ማገዱን ተከትሎ አቶ በረከት ለተለያዩ ሚዲያዎች ውሳኔው:-

=> በስብሰባው ለመታደም ዋስትና ስላልተሰጠኝ መገኘት አልቻልኩም፣

=> ውሳኔው መሰረተ ቢስ ነው፣

=> የኤርትራ መንግስት እጅ እና ፍላጎት ስለላበት በኤርትራ መንግስት ትዕዛዝ የተፈፀመ ነው፤ እኔ እርምጃ የተወሰደብኝ ኤርትራዊ ዘር ስላለኝ ነው፣

=> አቶ ደመቀ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳይሆን ስለታገልኩት በቂም ነው፣

=> እኔ ከኦሮሞ አንድ አመራር ወደ ሀላፊነት(ጠቅላይ ሚንስትርነት)እንዲመጣ ፍላጎት ነበረኝ ታግያለሁም፣

=> የአማራ አመራር አቅም የሌለው በመሆኑ የወጣቱን ጥያቄ ስላልመለሰ አቅጣጫ ለማሳት ከሱዳን፣ ከትግራይ እና ከአፋር እያጋጨ ነው፣ ሲሉ ብአዴንን በመክሰስ እና ማንንም ሊያሳምንልኝ ይችላል ያሉትን ሁሉ ጠጠር በመወርወር ላይ ናቸው ፡ ፡

===

ይህንን ሰምተን እና እዳምጠን አቶ በረከትን በዕድሜያቸው አክብረን እውነትን ሲያዛቡ እና በተንኮል መንገዳቸው ሲነጉዱ ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ ጥቂት ነገር ማለት ፈለግን ::

===

አቶ በረከት የጠየቁት ዋስትና የአማራ ወጣቶች እንዳያጠቋቸው በመፍራት እንደሆነ ገልፀዋል :: እሳቸውን የመሰለ አድራጊ ፈጣሪ፣ የፈለጉትን አንጋሽ እና አውራጅ ሰው ወደ ዋስትና ጠያቂነት ሲለወጥ ዋስትናውን ከመጠየቅ ለምን ወጣቱ ይህንን አለ፤ ምንስ አጠፋሁ ? ብሎ ራስን መመርመር የሚበጅ ስለመሆኑ እሳቸውን መምከር “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች ” ስለሚሆን እንተወው:: ግን ግን በየወረዳው መድረክ ፈጥረን ባወያየንባቸው መድረኮች ሁሉ ወጣቱ ” በረከት የአማራን መብት አስረግጧል፣ ህዝቡን አስቀጥቅጧል፣ አማራን አንገቱን እንዲደፋ አድርጏል … ወዘተ “ብሎ ሲሞግተን እኛም ወጣቱን ስንመክር የሚወርድብንን ትችት ቢያዩት አቶ በረከት አመራሩን ባልኮነኑ እንላለን::

===

ውሳኔውን በተመለከተ አቶ በረከት መሰረተ ቢስ ነው አሉት እንጂ እኛ ደግሞ ብአዴንም ሆነ አመራሩ መወቀስ ካለበት ውሳኔውን በማዘግየቱ ን እና ከልክ ያለፈ ትዕግስት ማሳየቱ ነው:: አቶ በረከት ማዕከላዊ ኮሚቴው ስለ ክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት እንዳይወያይ በማድረግ የንትርክ እና የጭቅጭቅ ኮሚቴ ካደረጉት እኮ ከአምስት አመታት በላይ ሆኗቸዋል:: በብአዴን ውስጥ ብቃት ያለው አመራር እንዳይወጣ እና የአማራ ህዝብ ጥያቄ በአግባቡ እንዳይነስ ትንሽ ሀሳብ ብልጭ ያደረገን ሰው ከሌሎች ጋር ሆነው “ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ” በማለት አጎብዳጅ እና ተላላኪ ሆነን እንድንኖር ታግለዋል:: እሳቸውውን የታገሉትን ህይወታቸው እንዲመሰቃቀልም ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል:: ጥረትንም የተጨመላለቀ የቤተሰብ እና የጏደኛ ጎጆ መውጫ አድርገውታል ተብሎ መገምገሙን በሶስትና አራት ወራት አይረሱትም:: ስለሆነም ውሳኔው የዘገየ ከበቂ በላይ ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ነው እንላለን:: በህግ የመጠይቅን ጉዳይ በተመለከተ ህግ ይየውም እንላለን::

===

” ውሳኔው የኤርትራ መንግስት እጅ አለበት፤ እኔም ኤርትራዊ ስለሆንኩ ነው ” ያሉት ነገር እርስ በእርሱ የሚጣፋ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አቶ በረከት ብአዴን በሌላ ውጫዊ አካል የሚታዘዝ ድርጅት ነው እያሉንም ስለሆነ “እሱ አክትሟል፤ እንኳን ከሌላ አገር በብእእዴንም ውስጥ ባዕድ ሀሳብ ሊጭን ይእሚችል ሀይል የሚሸከም ትከሻ የለም ” ልንላቸው እንወዳለን:: እኛም ወደ ኤርትራ የሄድንበትን ምክንያት ህዝብ ስለሚያውቀው ውሀ እንደማይቋጥር እሳቸውም አይጠፋቸውም :: በነገራችን ላይ የአማራ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት ልዑክ መስከረም 3 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ኤርትራ ይጏዛል::

===

አቶ ደመቀን በተመለከተ “ጠቅላይ ሚንስትር እንዳይሆን ስለታገልኩት ነው ” ላሉት ደግሞ ምክንያታቸው ደካማው ነው:: ምክንያቱም አቶ ደመቀ በእጩነትም እንዳይያዙ ለምክር ቤት አቅርበው እንደነበረ እና ምክንያታቸውም አዲስ አመራር እንዲመጣ ፍላጎት ስላላቸው መሆኑ ያደባባይ ሚስጥር ከመሆኑም በላይ የአቶ ደመቀን ትልቅነትና አስተዋይነት ያሳየ የወራት ትውስታ ስለሆነ ይህም ውሀ አይቋጥርም:: ለነገሩ አቶ በረከት በብአዴን መድረክ የአመራር ሽግሽግ አጀንዳ በማቀንቀን እሳቸው የሚያዙት አሻንጉሊት ሊቀመንበር ለማስቀመጥ አምርረው ታግለዋል፣ ጉዳዩንም እስክ ደምፀ ውሴኔ አድርሰዋል:: ሀሳባቸውም ውድቅ ተደርጏል:: አቶ በረከት ኦሮሞ ወደ ስልጣን ይምጣ ብለው እንደሞገቱ እና እንደታገሉ ገልፀዋል :: ነገር ግን ዶክተር አብይ ሊቀመንበር ሆነው እንዲመረጡ ብአዴን ሲታገል ” አብይ ኢትዮጵያንም ኢህአዴግንም አይመጥንም ” ብለው የታገሉት አብይ የየትኛው ብሄር እና ድርጅት መሪ መስለዋቸው ይሆን? ምን አልባት በአልባት በሁለቱ ህዝቦችና ድርጅቶች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር ታስቦ ከሆነ ይሄ አልፎበታል:: ለነገሩ ባለፈው አመት በባህር ዳር የኦሮሞ እና አማራ ህዝብ የጋራ መድረክ ስንፈጥር አቶ በረከት እና መሰሎቻቸው ” መርህ አልባ ግንኙነት ነው” ብለው መድረኩ እንዳይካሄድ እስከ ዋዜማው ጥረት ማድረጋቸው እና ትምክህትና ጥበት ያልተቀደሰ ጋብቻ መሰረቱ ብለው እንደወረዱብን ለምናስታውስ ጉዳዩ የቆየ እና ባህሪያዊ ስለሆነ እንደተለመደው እናልፈዋለን::

===

በመጨረሻም የአሁኑ የአማራ ክልል አመራር ደካማ ነው ሲሉ አመራሩን አጣጥለዋል :: ለመሆኑ ይሄ አመራር ደካማ ቢሆን ኖሮ እንዴት እሳቸውን ያህል ጉምቱ ፖለቲከኛ እና የተቀናቀኑትን መቀመቅ የሚያወርዱ ሰው ተቋቋመ? እንዴትስ ለእርሶ አላጎበድድም አለ? እንዴትስ ያልተደፈሩትን የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ደፍሮ ተሟገተባቸው? ባለፉ ጥቂት ወራት በነበሩን ስብሰባዎችስ ብአዴን ላይ ተስፋ አለኝ አላሉምን ? አሁን ያለው አመራር የወጣቱን የስራ ዕድል ይፈጠርልኝ ጥያቄ አይመልስም ሲሉ ለመሆኑ ይህ አመራር ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ምን እየሰራ እንደሆነስ ያውቁ የለም ? የአማራ ወጣት ጥያቄ ስራ እና ዳቦ ብቻ ነው እንዴ ? ጥያቄው እኮ ከዳቦ በላይ ነው:: ጥያቄው ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ ማንነት ነው:: ለነገሩ እነዚህ ጥያቄዎች አማራ ሲያነሳቸው ለእርስዎ ትምክህት ናቸው:: እነዚህን ያነሱ የብአዴን አመራሮችን አሳደው መምታትዎትን መናገር እርስዎን መድፈር ስላልሆነ እንናገረዋለን:: አመራሩስ ደካማ ቢሆን ማን መራው፣ ማን አሰለጠነው፣ ማን ገመገመው ቢባል ቀዳሚው ሰው አቶ በረከት መሆንዎ አይቀርምና የአመራር አያያዜ ምን ይመስል ነበር ብሎ ራስን መፈትሽ ከእውነት ያስታርቃል::

ታዲያ ይህንን ስል የትንታኔ ብቃቶትን፣ የትግል ድፍረቶትን እና እድሜዎትን በመድፈር አይደለም :: ቢያድልዎት ኖሮ ልክ እንደ አንዳንዶቹ የድርጅታችን መስራቾች “ቦታውን የያዘው አመራር በራሱ መንገድ ይምራ፣ እኛ ገብተን አንፍትፍት ” ብለው መድረኩን ለባለመድረክ ቢልቁ መልካም ነበር እንላለን:: እርሶን ያህል የኢትዮጵያን ሚዲያዎች ያሾር የነበረ ሰው አንድ ድብቅ አላማ ያነገብ እውደድ ባይ ግለሰብ የሚዘውራት እዚህ ግባ ማትባል ቦታ መገኘትዎትም እርስዎን አይመጥንም እና ይቅርብዎት እንልዎታለን::

LEAVE A REPLY