(ሳምሶን አስፋው – ቋጠሮ ገጽ)
በህወሃት ተጸንሶና ተወልዶ፤ ለበረከት ስምዖንና ጥቂት ጓደኞቹ በጉዲፈቻ ተሰጥቶ ያደገው ብአዴን ከአሳዳጊ አባቶቹ መካከል ሁለቱን ማባረሩ የሳምንቱ ጮማ ወሬ ሆኖ ሰነበተ።
በረከት እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ አገር ውስጥ ያሉ ማይክራፎኖች ሁሉ ኤታ ማዦር ሹም ነበር። ያለ እሱ ይሁኔታ ማንም ማይክ አይጨብጥም። ሰሞኑን ግን “የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው” እንዲሉ በማይክራፎን ጥማት ተንገብግቦ ያላንኳኳው የሚዲያ በር የለም።
ተጠምቶ አልቀረም።ከፊሉ ውለታ መላሽ ሆኖ፤ ከፊሉም ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ ሲሉ አስተናግደውታል። እሱም ከፊል ባሳደገው ድርጅት መባረሩ በፈጠረበት የቁጭት ስሜት ፤ ከፊል ደግሞ ጻፍኩት ያለውን መጽሃፍ ለማሻሻጥ በማሰብ ይመስላል ያገኘውን እድል ሁሉ ተጠቅሟል።ከ6 ያላነሱ ሚዲያዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።
ጠያቂዎቹም ሆኑ ጥያቄው ይለያይ እንጂ በረከት በቀረበበት ሁሉ ይናገር የነበረው አንድ አይነት ነገር ነበር ። በሃሰት መገፋቱን፤ የሰራው ጥፋት አለመኖሩን፤ የለውጡ ፋና ወጊ እሱ መሆኑን፤ ከሙስና የጸዳ ቤት አልባ ምስኪን መሆኑን ….ባጠቃላይ የዲስኩሩ ጠቅላላ ድምር “መሪና አመራር በኛ ግዜ ቀረ!” አይነት ነገር ነበር ።
ንግግሩ ይሰለቻል። የሚሰለቸው ተመሳሳይ ስለሆነ አይደለም። ይልቁኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ እሱ ያለውን ለዘመናት የተከማቸ ጥላቻ እያወቀ ድርቅ ብሎና አይኑን በጨው አጥቦ መቅረቡ ነው። የድርቅናው አድናቂ ነኝ!!
በዚህ ሳምንት ውስጥ በረከት ያደረጋቸውን ቃለ ምልልሶች በሙሉ አድምጫለሁ። ስለ እሱ የተጻፉ በርካታ ጽሁፎችንም አንብቢያለሁ።ባጠቃለይ የበረከት ጉዳይ በተነሳበት የሶሻል ሚዲያ ገጽ ላይ ሁሉ አንዣብቤ ኮሜንቶችን አንብቢያለሁ። ብታምኑም ባታምኑም አንድም ሰው በረከትን ደግፎ ሲጽፍ አላጋጠመኝም። የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች እንኳ የጣዖታቸውን (የመለስ ዜናዊን) ታማኝ አሽከር ለመደገፍ ብቅ አላሉም። ከዚህ በኋላ በረከትን ሊጠቀሙበት እንደማይችሉ አውቀዋል። የተሰነጠቀ ብርሌ መሆኑ ገብቷቸዋል። የሚገርም ነው። ያልታደለ ሰው።የኔ የሚለው ያጣ ምስኪን አርመኔ…!
እንደ እኔ እምነት በረከት በህዝብ መጠላቱን ከማንም በላይ ያውቀዋል። ይህን ስል ታዲያ መጠላቱን እያወቀ ለምን ይደክማል? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ እገነዘባለሁ።
አዎ! በረከት በህዝብ መጠላቱን እያወቀ እንዳበደ ውሻ የሚንቀዠቀዠው፤ “ እሩጫዬን ጨርሻለሁ” ብሎ ክሩን ከመበጠሱ በፊት የስትነፋሱን የመጨረሻ ትርታ አሰባስቦ በለውጥ አራማጁ ጎራ የቅራኔ እሳት ሊለኩስ አስቦ ነው። ተንኮል እንደሁ የሱ ነች!
በመጨረሻ የስትንፋሱ ትርታ የተሞከረ ተንኮል በመሆኑ አቅም ኖሮት እንደ ከዚህ ቀደሙ ህይወት ሊያስቀጥል አልቻለም።ጭራሹኑ ያን ትልቁን ስልጣን ይዞ አገር ሲንጥ የነበረው ጨካኝ ሰው ለካስ የመንደር አሉባልተኝነትን ባህሪም አዳብሎ የያዘ ነበር እንድንል አስገድዶናል።
ኃይለማሪያም ደሳለኝ ኤርትራ በሄደበት ግዜ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረገው ውይይት ኢሳያስ …… ለምን አትጠራርጓቸውም እንዳለው ሰማሁ በሚል ያቀረበውን አሉባልታ ልብ ይሏል። ይህ አሉባልታ በርግጥም ለሚዲያ የማይመጥን ተራ የመሸታ ቤት አሉባልታ ነው። ነገር ግን በውስጡ መርዝ አርግዟል። በተለይ ነገሩ እውነት ከሆነ የመርዙ መጠን ይጨምራል። አዎ! ነገሩ እውነት ከሆነ የኢሳያስንና የኃይለማሪያምን ውይይት ለበረከት ማን ነገረው ? የሚለው ጥያቄ ለውጥ አራማጁ ጎራ ውስጥ መጠራጠርን ሊፈጥር ይችላል። (በነገራችን ላይ ይህንኑ አሉባልታ ለበረከት የነገረው እግሌ ነው ይባላል በሚል ኢሳት ላይ የቀረበውን የይባላል አስተያየት አልወደድኩትም። ምክንያቱም ይህ አስተያየት በራሱ የበረከትን አሉባልታ እውነት ነው ብሎ ከማመን ስለሚነሳ ነው።) እውነትም ሆነ ውሸት የለውጡ ጎራ ይህን ተንኮል ተረድቶ እንድሚያከሽፈው ግን ጥርጥር የለኝም።
ሌላው የበረከት የሰሞኑ ግርግር ኢላማ “የለውጡን ሃሳብ ያቀረብኩት እኔ ነኝ” የምትለዋን የባለቤትነት ጥያቄ አድምቆ በማሳየት ግርታ መፍጠር ነው።
ይህን የበረከትን የባለቤትነት ጥያቄ ፤ በከፊል ዕውነት ነው ያሉት የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ አባባላቸውን ሲያስረዱ “በረከት ለውጥ እንዲደረግ ሃሳብ አቅርቧል ነገር ግን እሱ ያቀረበው የለውጥ ሃሳብ ፤ የወጣቱን የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ አመጹን ለማብረድ ያለመ እንጂ የዲሞክራሲ እጦቱን ጥያቄ የሚፈታ አልነበረም። ወጣቱ ደግሞ ይጠይቅ የነበረው ነጻነት እንጂ ዳቦ አልነበረምና የበረከትን የለውጥ ሃሳብ አልተቀበልነውም” ብለዋል። አቶ ንጉሱ የበረከትንም የለውጥ አመንጪነት ሃሳብ በከፊል ተቀብለው፤ ነገር ግን በረከት ያሰበው በምርጫ 97 ማግስት ወጣቱን በአነስተኛና ጥቃቅን አደራጅተው ፤ የዕለት ጉርስ በመስጠት አመጹን ያበረዱበትን አይነት ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት እንጂ አሁን የተያዘውን አይነት ለውጥ ለማምጣጥ እንዳልነበረ ያሳዩበት መልስ የበረከትን የባልቤትነት ጥያቄ እርቃኑን አስቀርቶታል። ውዥንብሩንም አጥርቶታል።
ጃዋር መሃመድም ሰሞኑን “ በረከት ለለውጥ እታገል ነበር ያለው እውነቱን ነው። ነገር ግን እሱ ይታገል የነበረው ፌክ ለውጥ ለማምጣት ነበር።” ሲል የተናገረው ለመጀመሪያ ግዜ ተመችቶኛል።
በረከት ከድርጅቱ መታገዱ አስደንግጦታል። በሚቀጥለው ጉባኤ ደግሞ ይባረራል። የፖለቲካ ህይወቱ ያበቃል። የፖለቲካ ህይወቱን ፍጻሜ ተከትሎ የህግ ተጠያቂነቱ ሂደት መጀመሩን የሚያበስረው ፊሽካ ይነፋል። ላለፉት 27 ዓመታት የሰራቸው ጥፋቶች፤ የፈጸማቸው ወንጀሎችና ግፎች እንደፈንዲሻ ከየአቅጣጫው ፈነዳድተው በአቃቢ ህግ ጠርጴዛ ላይ ሲከመሩ ታይቶታል(በተለይ ካሰቃያቸው ከጋዜጠኞች ) ። እናም መጪው ግዜ አስፈርቶታል። ዘግንኖታል፡ እየተሯሯጠ ያለውም በተቻለው አቅም አስከፊውን የውርደት ቁልቁለት ከድርጅቱ በመባረር ብቻ ለመገደብ ነው። ወደ ደራሲያን ግቢ ለመግባት እያንኳኳ ያለውም ለዚያ ይመስላል፡፤ ቀጣይ ህይወቴን በአነስተኛ ከተማ ውስጥ በማንበብና በመጻፍ ለማሳለፍ እፈልጋለሁ ማለቱን ልብ ይሏል።የፖለቲካውን ሩጫ ጨርሶ የደራሲነት … ሊቀጥል…
የፖለቲካ ህይወቱ ግን በቀላሉ መልቀቂያ የሚሰጠው አይመስልም፡፤ ያልተወራረዱ በርካታ ሂሳቦች ስላሉበት መጀመሪያ በህግ ፊት ሂሳቡን ማወራረድ ግድ ሊል ነው። ሊያስቀር ያሰበውም ይህንኑ ነው። በህግ ተጠያቂነትን። የሚሳካለት ግን አይመስልም። ባይሆን ስንቶቹን ባጎረበት ቃሊቲም ሆነ ዝዋይ ፍርዱን እየተቀበለ ታራሚ-ደራሲ መሆን ይችል ይሆናል፡፡፤ መነበቡን እርግጠኛ ባልሆንም የሚጻፍ ነገር የሚያጣ ግን አይመስለኝም… (ግን እኮ ጎበዝ ሳሞራ የኑስን በሜዳል የሸኙት ዶክተር አቢይ ለኔ ሜዳል ቢያጡ በምስጋና ወረቀት ይሸኙኛል የሚል ተስፋ ቋጥሮ ይሆናል። ይሄ መደመርና የጅምላ ይቅርታ እኮ ከፍትህ ጋር ያለው መስተጋብር ገና በውል አለየም …) ለማንኛውም ወደ በረከት ልመለስ።
እንደኔ እንደኔ የግዜ ጉዳይ እንጂ በረከት አብቅቶለታል። በነገራችን ላይ በረከትን የሚደግፍ ጽሁፍ ወይም አስተያየት አንብቢያለሁ የሚል ቢጠቁመኝ ደስ ይለኛል። እሱን መደገፍ በጣም ስለሚከብድ የሚደግፈውን ሰው ማድነቅ እፈልጋለሁ።
እንደገና በነገራችን ላይ በረከት ከሲሳይ አጌናና ከኤርሚያስ ጋር ቆይታ ለማድረግ ይፈቅድ ይመስላችኋል? ማይክራፎን ተርቧል ብዬ ነው…የተራበ ደግሞ አይመርጥም ….. ለማንኛውም ቢጠየቅ ጥሩ ነው።
በመጨረሻም ጽሁፌን የምቋጨው ለዚሁ ጉደኛ ሰው፤ መልስ የማይሻ የህሊና ጥያቄ በማቅረብ ነው፦
የትናቱ የሚዲያ ኤታ ማዦር ሹም፤ የዛሬው ታጋጅና ተሳዳጅ ፤ የነገው ታራሚ – ደራሲ በረከት ስምዖን ሆይ! ጣዖትህ መለስ ዜናዊ በሰኔ ሞቶ አንተ በክረምቱ መውጫ ነሃሴ ላይ ብቅ ብለህ በኔ ይሁንባችሁ ለእንቁጣጣሽ ይመጣል! በእቅፍ አበባ እንቀበለዋለን! ብለህ የዋሸኽው ህዝብ እንዴት ሊያምነኝ ይችላል ብለህ አሰብክ…?
የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል ሳይውል ሳያድር፤
ይጥልላታል ጠላቷን ከባንዲራው ሥር ፤
የሚለውን የኃይልዬ ታደሰን ድንቅ ትንቢታዊ ሙዚቃ…..ለአንባቢያን ሁሉ ጋብዣለሁ !
ቸር ይግጠመን
—