/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ከሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እየተደረገ ባለው የስራ ማቆም አድማ ምክንያት ከኢትዮጵያ የሚወጡና የሚገቡ አውሮፕላኖችን በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻሉን የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር አስታወቀ።
ማህበሩ ትናንት ባወጣው መግለጫ አየር ላይ ባሉ ሁለት አውሮፕላኖች መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት እንደማይጠበቅ ጠቅሶ ይህም ለከፍተኛ አደጋ እንደሚዳርግ አሳስቧል።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ለጊዜው የተኩት ከውጭ አገርና በጡረታ ተገልለው የነበሩ ባለሙያዎች ቢሆኑም “ከአዲስ አበባና ከናይሮቢ የሚነሱ አውሮፕላኖች ሲተላለፉ አስፈላጊውን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተሰራ አለመሆኑን እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ እየተላኩ ያሉ የበረራ ግመታዎች ሙሉ በሙሉ ስህተት ሲሆኑ የአውሮፕላን ዓይነትና መዳረሻቸውን በተመለከተ የሚሰጠው መረጃ ሳይቀር ስህተት ሆኖ እንደሚገኝ ማህበሩ አስታውቋል።
በጡረታ ተገልለው የነበሩና አሁን የተጠሩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የአየር ክልሉ ግንዛቤ እንደሌላቸው፣ የትብብር መመርያውን እንደማያውቁ፣ ግራ እንደተጋቡና በዘገምተኝነታቸው ምክንያት የሚነገራቸውን ለመስማትና መልዕክት ለማስተላለፍ አዳጋች እንደሆነባቸው የማህበሩ መግለጫ ስጋቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው በበኩላቸው ማህበሩ ያወጣው መግለጫ ሙሉ በሙሉ ስህተት እንደሆነና የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ራሳቸው በአድማ የሚታወቁ ስለሆኑ ለኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው አጋርነትን ለማሳየት ሲሉ ያወጡት መግለጫ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማኅበር በበኩሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድና የትራፊክ ሰራተኞች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት፤ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመፍታት እንዲተባበሩ በማለት ለዓለም አቀፉ የአየር መንገድ ፓይለቶች ማኅበር ፌዴሬሽን፣ ለኬንያ አየር መንገድ ፓይለቶች ማኅበርና ለዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር መግለጫውን ግልባጭ በማድረግ ጥሪ አስተላልፏል።