/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ በኤሌክትሮኒክ የሞባይል አየር ሰዓት መሙላት የሚያስችል ዓለም አቀፍ የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ይፋ አደረገ፡፡ አገልግሎቱ የቅድመ ክፍያና የጥምር (ሃይብሪድ) የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች፣ በውጭ አገር የሚገኙ ዘመድ ወዳጆቻቸው ወደ ሞባይል ቁጥራቸው የአየር ሰዓት እንዲልኩላቸው የሚያስችል እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል፡፡
በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ለተጠቃሚዎች የተዋወቀው ይህ አገልግሎት፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገር ቤት ለሚገኙ ዘመድ ወዳጆቻቸው የሞባይል የአየር ሰዓት በመሙላት፣ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶችን እንዲለዋወጡ የሚያደርግበት ስርዓት እንዳካተተም ተጠቅሷል፡፡
ተጠቃሚዎች በኤሌክትሮኒክ የአየር ሰዓት የመሙላት አገልግሎት ለመጠቀም ከ25 ብር ጀምሮ አገር ቤት ለሚገኙ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ገዝተው መላክ የሚችሉበት አሰራር ነው ተብሏል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአብዛኛው የሞባይልና የኢንተርኔት ታሪፍ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ከውጭ ወደ ሀገር ቤት ለገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ልዩ የቴሌኮም አገልግሎት ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።