የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት አዲስ አበባ አቀባበል ደማቅ መሆኑ ተገለፀ

የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት አዲስ አበባ አቀባበል ደማቅ መሆኑ ተገለፀ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የልዑካን ቡድን ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ገብተዋል። የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ ዋና ፀሀፊው አቶ አዳርጋቸው ፅጌ፣ አቶ ነዓምን ዘለቀን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቱ መሪዎች ከአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ኖርዌይ፣ አውስትራሊያ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎች ሀገራት የተውጣጡ መሆናቸው ተገልጿል።

የአርበኞች ግንቦት 7 የልዑካን ቡድን ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ከፍተኛ የመንግስት ባልስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ከቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በውጣት ደማቅ አቀባበል እያደረጉ ነው።ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ መስቀል አደባባይ ያለው አፍሪካ ጎዳና ለትራፊክ ዝግም ነበር።

ለፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ለጋዜጠኞች መግለጫም ሰጥተዋል። ፕሮፌሰሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የንቅናቃቸው ቀዳሚ ተግባር ሀገርን ማረጋጋት ነው ብለዋል። አርበኞች ግንቦት 7 ከህዝብ፣ መንግስት፣ በየትኛውም መንገድ ከተደራጁ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ውይይት እንደሚያደርግም ተጠቅሷል።

ሀገር ውስጥ ከሚገኘው የአርበኞች ግንቦት 7 የአቀባበል ኮሚቴ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ድርጅቱ  ከመስከረም 5/2011 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያካሂድ ታውቋል። አዲስ አበባ፣ አዳማና መቀሌን ጨምሮ በሎች 32 ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ እቅድ መውጣቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ባህር ዳርና ጎንደር ከተማ መስከረም 6 እና 7 እንዲሁም አዳማ ከተማ ደግሞ መስከረም 12 የንቅናቄው አመራሮች በተገኙበት ህዝባዊ ትዕይት ከተካሄደ በኋላ በተከታታይ ቀናት በመቀሌ፣ ወልዲያ፣ ደሴና አምቦ ተመሳሳይ ፕሮግራም እንደሚኖር ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል  የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ክንፍ የሆነው ኦነግ ሽኔ አመራሮችና አባላት መስከረም አምስት 2011 ዓ.ም ከኤርትራ ወደ ሀገራቸው ሊገቡ መሆኑ ታውቋል። 1300 የግንባሩ ታጣቂዎችም ከመሪያቸው ዳውድ ኢብሳ ጋር ትጥቃቸውን በመፍታት ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ ተብሏል፡፡በአዲስ አበባ ከተማም አቀባበል እንደሚደረግላቸው ትናንት ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

LEAVE A REPLY