የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠው መግለጫ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠው መግለጫ

መንግስት ሕግና ሥርዓት ሊያስከብር እንደሚገባው አብን በአንክሮ ያሳስባል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ማናቸውም አስተሳሰቦች በሰላማዊ መንገድ እስከቀረቡ ድረስ አንዳችም ገደብ ሳይደረግባቸው ሊንፀባረቁ ይገባል የሚል አቋም አለው። አብን እንደድርጅት የአስተሳሰብ ብዝኃነት መብት እንዲከበር በጽናት የሚታገልበትነ የሚታገልለት ዓላማም ነው። አሁን ላይ በአገራችን የሚደመጡና የሚንፀባረቁ አስተሳሰቦችንም በዚህ መልኩ ይረዳቸዋል።

ይሁንና አነሰም በዛም ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች በከፋሉት ከፍተኛ መስዕዋትነት በአንፃራዊነት ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የተጠበቀ ቢሆንም ቅሉ፤ በተገኘው አንፃራዊ ነፃነትና ሰላም ተጠቅመው የሚታገሉለትን የፖለቲካ ዓላማና መርኃግብር እንታገልለታለን ለሚሉት ሕዝብ አቅርበው በማስተዋወቅ ፋንታ አንዳንድ ቡድኖች የአገርንም ሆነ የሕዝብን አብሮነትና አንድነት የሚፈታተኑ ፀብ አጫሪ ድርጊቶችንና ትንኮሳዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለብቻችን ታግለን ያመጣነው ነዉ ከሚል ግብዝነት ከተሞላባቸው ንግግሮችና መግለጫዎች ጨምሮ በሕዝብ ላይ ከፋፋይ፣ አግላይና ነጣይ ድርጊቶችን ታዝበናል። እጅግ በከፋ ሁኔታም የሕዝብ ታሪክና ባሕልና ማንነት መገለጫዎችን የማንቋሸሽና የማውደም ተጨባጭ ሙከራዎችን አስተውለናል።

ስለሆነም የአንዳንድ ቡድኖችና አንጃዎች እንቅስቃሴ እንደአገር የተጀመረውን ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ በጎ ጅምር የሚያስተጓጉል ከመሆኑም በላይ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭትን የሚያነግስ፤ የአገር አንድነትንና መረጋጋትን የሚያናጋ በመሆኑ የኢፌዴሪ መንግስት፦

1) ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነቱን በመወጣት በአገርና ሕዝብ ላይ የተደቀነውን አደጋ ተገንዝቦ የማስተካከያ እርምጃ እንዲዎስድ፣

2) የሕዝብና አገር መለያዎች፣ ቅርሶችና መገለጫዎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ፣

3) ከአዳራሽና አደባባይ ድግስና ፌሽታ ወጥቶ አገርና ሕዝብን ወደ ዘላቂ ሰላም ሊያሸጋግሩ ወደሚችሉና እንደአገር ሁሉንም ህዝቦች አሸናፊ ወደሚያደርጉ ድርድሮችና ውይይቶች እንዲያሸጋግር በአንክሮ እያሳሰብን አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች የሕዝብ ለሕዝብ ታሪካዊና በጎ ግንኙነቶችን በሚጎዳ መልኩና ብጥብጥን ለመፍጠር የሚደረጓቸዉ የጥፋት ሴራዎችንና ሙከራዎችን አምርረን የምናወግዝ መሆኑን እንገልፃለን።

አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ

መስከረም 03/2011 ዓ/ም

አዲስ አበባ፥ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ

LEAVE A REPLY