ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ የተከሰተውን ግጭት አስመልክተው መግለጫ ሰጡ

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ የተከሰተውን ግጭት አስመልክተው መግለጫ ሰጡ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ ትናንትና ዛሬ በሰንደቅ ዓላማ ምክንያት የተነሰውን ግጭት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ “በሀገሪቱ እየሰፈነ ያለው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ባንዲራንም ስለሚያጠቃልል የሌላኛውን አስተሳሰብ መግፋት አይገባም” ሲሉ ገልፀዋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ ብቸኛ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሆነ ከውጭ የሚገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች የማግለል አካሄድን ሊከተሉ አይገባም ብለዋል።በተናጥል በመፎከር አሸናፊ መሆን ስለማይቻል ተነጋግሮ በመግባባት መተባበር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንዲራን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ባንዲራ መቀየር በሌሎች ሀገራትም የተመደ እንደሆነ ጠቅሰው፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ከሆነ ተወዋይቶ፣ ድምፅ ሰጥቶ ሊቀይረው ይችላል፤ በጉልበት ማስቀየር የሚፈልግ ካለ እሱ ጉልበት እንዳለው ሌላውም ጉልበት ስላለው አያዋጣም። ግጭትም ሊያስነሳ ይችላል። ኢትዮጵያንም ያፈርሳል ብለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል በአዲስ አበባ የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ለሸገር ኤፍ ኤም ራዲዮ በሰጡት መግለጫ፤ በሁለቱም ወገን ያሉ ወጣቶች ከጠብ አጫሪነት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።” ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ የኦነግን አመራሮች ቅዳሜ ወደ ሀገር ውስጥ መምጣት ምክንያት በማድረግ ደጋፊዎቹ የፈለጉትን አርማና ሰንደቆች ይዘው እንዲወጡ በአደባባዮችም እንዲያውለበልቡ ፈቅደናል:: ሆኖም አስፓልትና ቋሚ የህዝብን ንብረቶችን ግን ቀለም መቀባት አይቻልም።” በማለት ገልጸዋል።

ተቀጣጣይ ነገሮችን ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወርወርን ጨምሮ ሌሎች ህጋዊ ያልሆኑ ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ዘይኑ፤ መንግስት ህግ የማስከበር ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ወጣቶች ህግ የማስከበሩን ስራ ለፖሊስ እንዲተውና ከኦሮሚያ የመጡ ወጣቶችም ቀለም መቀባት ማቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

LEAVE A REPLY