በሸኘነው ዓመት ማገባደጃ በሚዲያ ጎልተው ከወጡ ሰዎች መሐል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ አንዱ ናቸው። በጥቂት ፖለቲካዊና በርከት ባሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ጥያቄ፦ 2010 እንዴት ነበር?
አቶ ታምራት: አንደኛው ለረዥም ዓመት የነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብ አዲስ ነገር እንደሚፈልግ፤ ያለፈው ሁኔታ መሞት እንዳለበት ሕዝቡ ራሱ በተለያዩ መንገዶች ያሳየበት ዓመት ነበር። አሮጌ አስተሳሰቦች፣ አሮጌ አስተደደራዊ ዘይቤዎች ማለፍ፣ መሞትና መቅረት አንዳለባቸው የተበሰረበት ነበር።
ሁለተኛ መልካም ጅማሮች የታዩበትና ተስፈ የፈነጠቀበት ዓመት ነበር። ይህን የምለው ሕዝብ አስተያየቱን ያለምንም መደናቀፍ በነጻነት የሚገልጽበት ሁኔታ የተፈጠረበት በመሆኑ ነው። ይሄ ነው አዲሱ ፋና። ገና ጅማሮ ነው። ግን ጥሩ ጅማሮ ነው።
ጥያቄ፦ ከሰጧቸው ቃለምልልሶች በመነሳት የቀድሞው ባልደረቦችዎ ለምሳሌ እንደነ አቶ በረከት ስምኦን እርሶ ላይ የተአማኒነት ጥያቄን አንስተዋል።
አቶ ታምራት: በእኔ በኩልና ቤተሰቤ የነበርንበትን ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ኢህአዴግና ባለሥልጣናቱ፣ በተለይ አቶ በረከትን ጨምሮ፣ ሕዝቡን ሲዋሹና ሲያጭበረብሩ የነበረበትን ሁኔታ እውነቱ ይሄ ነው ብለን ተናግረናል። እሱ ብቻ ሳይሆን እኔ በበኩሌ በሥልጣን በነበርኩባቸው ዓመታት አጠፋሁ ያልኳቸውን ‘አጠፋሁ’ ብዬ፣ ሕዝቡንም በሆነው ነገር ሁሉ ይቅርታ ጠይቄ፣ በኔ በኩል ሒሳቤን ዘግቻለሁ።
ከዚህ በኋላ እንደገና እሰጣገባ ውስጥ የምገባበት ምክንያት የለኝም። ሕዝቡ የትኛው እውነት የትኛው ውሸት እንደሆነ ያውቃል ብዬ አምናለሁ።
አቶ በረከት መግለጫ ሰጡ ከተባለ በኋላ የሕዝቡን ምላሽ እያየሁ ነው። ሕዝቡ ያውቃል። ማን ውሸታም እንደሆነ ያውቃል።
አብረዋቸው ለረጅም ጊዜ የሠሩ ሰዎች ሳይቀር እየወጡ ምን ያህል ዋሾ እንደሆኑ እሳቸውና ሌሎችም ጓደኞቻቸው ምን ያህል በቀለኛ ፣ ምን ያህል ቂመኛ እንደሆኑ እኔ ሳልሆን ሌሎቹ እየተናገሩ ናቸው። እኔ እንኳ እነኚህን ሁሉ ነገሮች ባውቅም ጉዳዩ የመበቀል ሳይሆን አዲሱን ትውልድ የማስተማር ጉዳይ ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ አልገባሁም ነበር።
ሁለተኛው [እዚህ ጉዳይ ውስጥ መመለስ]የማልፈልግበት ምክንያት ይሄ የአቶ በረከትና የመሰሎቻቸው ሐሳቦች የሙታን ሐሳቦች ናቸው፤ ከዚህ በኋላ፥ የሕያዋን ሐሳቦች አይደሉም። እኔ ደግሞ የሕያዋን የሆነ ሐሳብ ይዤ፣ አዲስ ከሚመጣው አስተሳሰብና ኢትዮጵያዊያን ወደ ፊት ሊያራምዳት ይችላል ብዬ ከማስበው ጋር ወደፊት የማስብ እንጂ ወደ ኋላ የማስብ ሰው አይደለሁም።
ጥያቄ፦ በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች የሞቱ ሰዎችን ወቅሰዋል። ለምሳሌ አቶ መለስ እና አቶ ክንፈን። በሕይወት ያሉ ባለሥልጣናትን ስም ግን ከመጥቀስ ይቆጠባሉ። እውነትን ለትውልድ ማስተላለፍ ከፈለጉ ለምን ግማሽ እውነት መናገር መረጡ?
አቶ ታምራት፦ እንደኔ አመለካከት የሰዎችን ስም አለመናገር ግማሽ እውነት ሊባል አይችልም። ስም ያላነሳሁበት ምክንያት ቃለ ምልልሴ በዋናነት እውነቱን ለመናገርና ሁኔታውን ለትምህርት ለመተው ነው እንጂ ሰዎችን እያነሱ ለማብልጠል አይደለም።
አቶ በረከት ምስጋና ይግባቸውና በኔም በቤተሰቤም ላይ ሲያሴሩ የኖሩትን ሰዎች እነማን እንደሆኑ እኔ ሳልናገር ራሳቸው ተናግረውልኛል። እነማ እነማ እንደሆኑ፣ እነ እገሌ እነ እገሌ ብለው ራሳቸው ጠቅሰዋቸዋል። አንድ ጊዜ እኔን አንድ ጊዜ አቶ ታደሰን፥ አንድ ጊዜ አቶ ህላዌን አንድ ጊዜ አቶ አዲሱን እያሉ ጠቅሰዋል ሰዎቹ።
የሰዎችን ስም መናገር ለእኔ በጣም ቀላል ነገር ነው። ወደፊትም ደግሞ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በመጽሐፍ መልክም ይሁን በሌላ ስሞችን መግለጽና ማውጣት ይቻላል።
እናንተም ቢሆን ስም ላይ ባተተኩሩ ጥሩ ነው። ዋናው እውነቱ ፤ የተደረገው ነገር ነው። እኔ ይሄን ያደረኩት የሚመጣው መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን እንዳይሠራ ነው እንጂ ወደኋላ ተመልሶ ለመቆዘም አይደለም።
በነገራችን ላይ በዚያ ቃለ መጠይቅ ውስጥ ክስና በቀል እንዳይመስል ብዬ ያላነሳኋቸው ብዙ ሌሎች ጉዳዮች አሉ። አዳዲስና ያልተሰሙ ጉዳዮች። ወደፊት እንደ የሁኔታው በመጽሐፍ ወይም በሌሎች መንገዶች ላነሳቸው የምችል።
ጥያቄ፦ መጽሐፍ እየጻፉ ነው ማለት ነው?
አቶ ታምራት: የመጽሐፍ ሐሳብ አለኝ። በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በእኔም በቤተሰቤም ሕይወት ላይ ያተኮረ እንደ ማስታወሻ ዓይነት ነገሮች የመጻፍ ሐሳብ አለኝ። ደግሞ እንዳልኩት ዋናው ዓላማ ለመበቀል ለመክሰስ ሳይሆን ትምህርቱ ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ነው።
ተስፋ አደርጋለሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሆናል።
ጥያቄ፦ ትዊተር ወይ ፌስቡክ ገጽ አለዎት?
አቶ ታምራት: ትዊተር የለኝም። የፌስቡክ ገጾች ነበሩኝ በተለያየ ጊዜ የኔን የፌስቡክ ገጾች ሌሎች እየወሰዱ እቸገራለሁ። የኔ ያልሆነ መልዕክት እየተላለፈ ተቸግሬያለሁ። አንደኛው ችግርም የኢህአዴግ መሪዎች ናቸው፤ ስልካችንንም እየጠለፉ፣ ፌስቡካችንንም ‘ሀክ’ እያደረጉ ይጠቀሙ የነበሩት እነርሱ ናቸው።
ባለፉት 10 ዓመታት ከተፈታሁም በኋላ እስከዚህ ደረጃ ድረስ የወረደ ክትትል ነበረ፤ አሁንም ፌስቡክ አለኝ፤ ነገር ግን የኔ ያልሆኑ መልእክቶች እየተላለፉ ስላየሁ አልጠቀምበትም።
ጥያቄ፦ የት አገር ነው የሚኖሩት? ለመሆኑ የግል መኖርያ ቤት አለዎት?
አቶ ታምራት: ብዙ አሉባልታዎች ተብለው ያውቃሉ። ንግድ ውስጥ ተሰማርቷል። አሜሪካ ውስጥ ነዳጅ ማደያ አለው። ኮካ ኮላ ኩባንያ ውስጥ ሼር አለው። ትላልቅ ሕንጻዎች አሉት። ያልተባለ ነገር የለም። የኢህአዴግ መሪዎች ናቸው ሲዋሹ የኖሩት። እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ [እኔና ቤተሰቤ] አገራችን ተመልሰን መኖር እንፈልጋለን። እንደማንኛውም ሰው ቤት እንዲኖረን እፈልጋለሁ። አሁን የምኖረው መንግሥት በሰጠኝ የኪራይ ቤት ነው።
ጥያቄ፦ ኪራይ ቤቱን እንዴት አገኙ?
[ከእስር እንደተፈታሁ] ኪራይ ቤት እፈልጋለሁ፤ ቤት የለኝም አልኩ። እንደሌለኝ ያውቁም ስለነበር ኪራይ ቤት አገኘሁ።
ጥያቄ፦ ሼክ ሙሐመድን አግኝተዋቸው ያውቃሉ?
አቶ ታምራት: አግኝቻቸው አላውቅም
ጥያቄ፦ቢያገኘቸው ሊነግሯቸው የሚፈልጉት ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ታምራት: ምንም የምላቸው ነገር የለም። እግዚአብሔር ይርዳቸው፤ በማንኛውም ነገር። እጸልይላቸዋለሁ፤ እንደማንኛውም ሰው። ድሮ እንደማውቃቸው፣ ልክ ለኢህአዴግ መሪዎች እንደምጸልየው እጸልይላቸዋለሁ። እግዚያአብሔር በኑሯቸውም በሕይወታቸውም እንዲረዳቸው እጸልያለሁ።
ጥያቄ፦ ዶ/ር ዐብይ የእርስዎ እርዳታ ቢያስፈልጋቸው በምን መንገድ ሊያግዟቸው ይችላሉ?
አቶ ታምራት: አሁን ያለው ለውጥ ግንባር ቀደሞች የሆኑት ዶ/ር ዐብይን ጨምሮ እገዛ ያስፈልገኛል በሚሉበትና በሚያምኑበት ሁሉ ለማገዝ እኔ በበኩሌ ዝግጁ ነኝ። በዚህ በዚህ ብዬ አልመርጥም። ዓላማዬ ሁለት ነው። እንደኛ አሁን የተጀመረው ተስፋ በምንም መንገድ መቀልበስ አለበት ብዬ አላምንም። ሁላችንም እንደዛ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን መፍቀድ የለበትም።
ሁለተኛ ለኢትዯጵያ ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ ነጻነትና ፍትህ የሚሰፍንበት ሁኔታ እንዳይ ነው የምመኘው። እነዚህን ጉዳዮች እስካገዘ ድረስ በዚያ ቦታ በዚህ ቦታ፣ በዚህ ሁኔታ በዚያ ሁኔታ ሳልል ምርጫ ሳይኖረኝ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ።
ጥያቄ፦ ከመንፈሳዊ ሕይወት ውጭ ባሉ ሁኔታዎች ምን ያዝናናዎታል?
አቶ ታምራት: አንደኛው በጣም የምወደው ነገር ኳስ ነው። ከልጅነቴም እወድ ስለነበር አሁንም ጊዜ ሲኖረኝ እከታተላለሁ። ሌላው በጣም የሚያዝናናኝ መጽሐፍ ነው። በድካምም ቢሆን በብስጭትም በጉዞም ላይ ቢሆን መጸሕፍት አነባለሁ።
ሌላው እኔም ባለቤቴም በጣም የምንወደው ተፈጥሮን ወደ ምናደንቅበት ቦታ መሄድ ነው። ኮሎራዶ ነው የምንኖረው፤ በጣም ደስ የሚል ተራራማ ቦታ ነው። ወደ ተራሮች እንሄዳለን። አሜሪካዊያን ብዙ ጓደኞች አሉን። ከነርሱ ጋር እናሳልፋለን።
አዘውትሬም ባይሆን አንዳንድ ጊዜ የማደርጋቸው ነገሮች ደግሞ አሉ፤ ከጓደኞቻችን ጋር ቴኒስ መጫወትና ማየት፥ አሳ ማጥመድ ወዘተ።
ጥያቄ፦ ከክለብ የማን ደጋፊ ኖት?
የባርሴሎና ደጋፊ ነኝ። ጫዋታቸው ደስ ስለሚለኝ ነው። [እኔ አንድ ቡድንን] የምደግፈው በሃይማኖተኝነት ወይም በአምልኮ መልክ አይደለም። ጥሩ የሚጫወት አርቲስቲክ የሆነ ቡድንን እደግፋለሁ። በዚህም አሁን የምደግፈው ባርሴሎናን ነው። ድሮ ብራዚልን እደግፍ ነበር።
ጥያቄ፦ከተጫዋዎቾችስ በስም የሚጠቅሷቸው አሉ?
አቶ ታምራት: ሜሲን ነው የምወደው። በጣም እወደዋለሁ፤ አደንቀዋለሁ። ባርሴሎና አጨዋወታቸው ጥበብ የተሞላበት ነው። ራሳቸውን አዝናንተው ሌሎችንም የሚያዝናኑ ስለሆኑ ነው። ኔይማርንም በዚሁ መለኪያ አደንቃለሁ። በእርግጥ ገና በደንብ ማየት አለብኝ እሱን። ሮናልዲንሆንም አደንቃለሁ።
እነዚህ ተጫዋቾች ለራሳቸው ብቻ የሚጫወቱ ሳይሆኑ ሌላውንም የሚያጫውቱ [በተለይ ሜሲ] ያለቀላቸውን ኳሶች በመስጠት ከግለኝነት ውጭ የሆነ ጨዋታን የሚጫወት ነው። በነዚህ መመዘኛዎች ባርሳ እወዳለሁ።
ጥያቄ፦ ከአገር ውስጥ የየትኛው ቡድን ደጋፊ ነዎት?
አቶ ታምራት: ከአገር ውሰጥ አላውቃቸውም። ከኢትዮጵያ ርቄ ስለነበር አላውቃቸውም። የማውቃቸው ቡድኖች የሉም። እከሌ እከሌ ለማለት እቸገራለሁ።
ጥያቄ፦ ቡናን ጊዮርጊስን አያውቁም፤ አቶ ታምራት?
የድሮው ጊዮርጊስን አውቀዋለሁ። ግን ደጋፊ አልነበርኩም። ልጅ ሆኜም ተማሪ ሆኜም አንድ መቻል የሚባል ቡድን ነበር። የመቻል ደጋፊ ነበርኩ። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የአየር መንገድ ደጋፊ ነበርኩ። በአንድ ወቅትም የአየር መንገድ ቡድን ለተወሰነ ጊዜ እጫወት ነበር።
ጥያቄ፦ ጎበዝ ነበሩ ማለት ነው ኳስ ላይ? የት ቦታ ነበር የሚጫወቱት? አጥቂ? ተከላካይ?
አቶ ታምራት: ተማሪ ቤት እያለሁ አማካይ ነበር የምጫወተው። ያን ያህል የምደነቅ ተጫዋች አልነበርኩም።
ጥያቄ፦አውዳመት እንዴት ነው ሊያከብሩ ያሰቡት?
አቶ ታምራት: ከ22 ዓመት በኋላ አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ከቤተብ ጋር ሆኜ አሁን ለመጀመርያ ጊዜ ላከብር ነው (ቃለ ምልልሱ ከአዲስ ዓመት ቀደም ብሎ የተደረገ ነው)። 12 ዓመት በእስር ቤት ስለነበርኩ አክብርው አላውቅም። ብቻዬን ስላሠሩኝ ሻማ አበራለሁ፣ እንደዚህ እንደዚህ አደርጋለሁ እንጂ ከቤተበስ አክብሬ አላውቅም። ከተፈታሁ 10 ዓመት አድርጊያለሁ። 10 ዓመት አሜሪካን አገር በአሉን እያሰብን እንውላለን እንደ ኢትዯጵያ ባይሀንም።
ኢትዯጵያ ውስጥ ግን አክብሬ አላውቅም። አሁን ከባለቤቴ ጋር አብረን ሆነን፣ እናት አለችኝ፣ ከናቴ ጋር አብረን ሆነን፣ ሌሎችም ዘመዶች አሉኝ ከነርሱ ጋር ሆነን ለመጀመርያ ጊዜ ከ22 ዓመት በኋላ ላከብር ነው
ብዙ ጓደኞቼ ‘እኛ ቤት ነው የምትመጡት፣ እኛ ቤት ነው የምትመጡት’ ብለው ቀኖቹን በየተራ አንድ ሳምንት ያህል ከጓደኞቻችን ጋራ ስናሳልፍ ነው የምንቆየው። በተስፋና በአዲስ መንፈስ
ጥያቄ፦ የሚናፍቁት ሰፈር አለ ከአዲስ አበባ?
አቶ ታምራት: በጣም የምወደው ሰፈር ቦሌ አካባቢን ነው፤ ተወልጄ ያደኩትም እዚያው ስለሆነ። ከመስቀል አደባባይ ጀምረህ ስታዲየም አካባቢ እነ መሿለኪያ፣ እነ ኦሎምፒያ፣ ወሎ ሰፈር፣ ኡራኤል እነዚህ ያደኩከባቸው ሰፈሮች ናቸው። በኳስ በትምህርት ቤት፥ በጓደኝነት ወዘተ። ከእነዚህ ሰፈሮች ጋር ልዩ ስሜት አለኝ።
ጥያቄ፦ የት ሰፈር ነው የተወለዱት?
አቶ ታምራት: የተወለድኩት ኦሎምፒያ አካባቢ ነው። ያደኩትም እዚያው አካባቢ ነው።
ሌለሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የምወዳቸው ሰፈሮች አሉ። የፊት በር አካባቢ፣ ከዚያም በላይ ግን የንፋስ ስልክ ሳሪስ አካባቢን በጣም እወደዋለሁ። ከምወዳቸው ጓደኞች ጋር ብዙ ያሳለፍንብት ሰፈር ነው። ጉለሌ አካባቢ ላይ ከኢህአፓ ጋር በተያያዘ ብዙ ሠርቼበታለሁ እና እወደዋለሁ። አሁን ሰፈሮች ተለዋውጠዋል። መግቢያ መውጫቸው ተለዋውጧል። ብሄድ ልጠፋም እችላለሁ።
ጥያቄ፦ ባለሥልጣን እያሉ የት ነው የኖሩት?
አቶ ታምራት: ቦሌ አካባቢ አብዛኛው ባለሥልጣናት የሚኖርበት ሰፈር ነው የኖርኩት።
ጥያቄ፦ አሁን መንገድ ላይ ሰዎች ሲያገኝዎት ምን ይልዎታል?
አቶ ታምራት: ሰው መንገድ ላይ ሲያየኝ ሰላምታ ይሰጠኛል፤ ያቅፉኛል በተለይ ወጣቶች። ካፌ ሬስቶራንት እገባለሁ፤ ተከፍሏል ይሉኛል። በጣም በጎ መንፈስ ነው ያለው።
ጥያቄ፦ የምግብ ምርጫዎ ምንድነው?
አቶ ታምራት: የምግብ ምርጫ የለኝም። ያገኘሁትን እበላለሁ። በጣም ጤነኛ ስለሆንኩ የፈለኩትን እበላለሁ። በጤና ምክንያትም የምመርጠው የለኝም። የኢትዮጰያ ምግብ በአጠቃላይ ይስማማኛል።
ጥያቄ፦ ይህ ነገር ቁርጥን ይጨምራል?
አቶ ታምራት: ቁርጥ እንኳን በልቼም አላውቅም። አንድ ጊዜ መብላቴን አስታውሳለሁ፤ አንድ ዘመድ አምጥቶልኝ በልቻለሁ። ቦታው ላይ ሄጄ ሳይሆን ቤት አምጥቶልኝ በልቻለሁ። ቁርጥ ብዙም አልበላም። አልወድም ማለቴ ሳይሆን አላዘወትርም ማለቴ ነው።
ጥያቄ፦ በ12 ዓመታት የእስር ጊዜ ምን አነበቡ? ከመንፈሳዊ መጻሕፍት ውጭ የትኞቹን ወደዷቸው?
አቶ ታምራት: ዘውዴ ረታን በጣም አደንቃቸዋለሁ። የበዓሉ ግርማን ብዙዎቹን ሜዳ እያለሁ ያነበብኳቸው ቢሆንም በድጋሚ አንብቤአቸዋለሁ። የነ ገብረክርስቶስና የነጸጋዬን ግጥሞችም እንደገና አንብቢያቸዋለሁ።
ጥያቄ፦ ዛሬም ኢህአዴግ ውስጥ በሥልጣን ያለ፣ የኔ የሚሉት ጓደኛ አለዎት?
አቶ ታምራት: አብረን ከነበርናቸው እና ከቆዩት መሐከል ጓደኛዬ የምለው የምቀርበውም የለኝም። ለሁሉም ግን እጸልያለሁ። ለሁሉም መልካምን እመኛለሁ። ምንም ዓይነት ቂም በቀል የለኝም።