/ያሬድ ኃይለማርያም/
መስከረም 16 ቀን 2018 እኤአ
ቄሮን፣ ፋኖን፣ ዘርማን እና ሌሎች የወጣት ንቅና ቄዎችን እንደፈረስ ለመጋለብ የሚደረገው የፓርቲዎች ሽኩቻ አንድ ሊባልይገባል።
እነዚህ የወጣት ንቅናቄዎች ባለፉት ሦስት አመታት የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል አይደለም። በሺህ የሚቆጠሩ ወንድም እህቶቻቸውን ተነጥቀዋል፣ ብዙዎቹ በየማጎሪያው ተጥለው ለወራትና ለአመታት ስቃይ ሲፈጸምባቸው ቆይተዋል። መሰዋትነታቸውም መና አልቀረም። የተሰውለት አላማ ሙሉ በምሉ ባይባልም ምላሽ እያገኘ ነው። ከመንፈቅ በፊት በመስቀል አደባባይ በወያኔ ታጣቂዎች ተደብድበዋል፣ ደማቸውን አፈሰዋል።
አሁን ደግሞ እነዚህ ወጣቶች በነጻነት በዚሁ ስፍራ ሲሰባሰቡ፣ ሃሳባቸውን ሲገልጹ እና የሚፈልጉትንም ሲደግፉና ሲቃወሙ እያየን ነው። ይህ ትውልድ አገሩን እንደሚወድ፣ ላመነበትም ሆነ ለነጻነቱ መስዋት እስከ ምን ደረጃ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነ እና ጽናቱንም በተግባር አሳይቷል።
በተቃራኒው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ላለፉት አሥርት አመታት ገሚሶቹ ከተኙበት ድንገት ባነው የነቁ በሚመስል መልኩ፤ ለሎቹም እርስ በርስ ሲሻኮቱ፣ ሲወነጃጀሉ እና ሲጠላለፉ በመቆየታቸው ቅርቃር ውስጥ የወደቀውን የአገሪቱ ፖለቲካ ለመታደግ የሚያስችል አቅም መገንባት ሳይችሉ ቆይተዋል። አሁን የተፈጠረው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ያነቃቃቸው ቢሆንም ሰከን ብለው በአገሪቱ ቀጣይ ፍኖተ ዲሞክራሲ ላይ አተኩረው በጋራ ከምስራት ይልቅ ከአገሪቱ አንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ እየተዘዋወሩ ደጋፊ የማሰባሰብ እና የለውጡ ገፊ የሆኑትን ወጣቶች የራሳቸው ለማድረግ ሽሚያ የገቡ ይመስላል። ትዝብቴን በዝርዝር ላቅርብ፤
-
ከላይ እንደጠቀስኩት ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ እና ሌሎች የወጣት እንቅስቃሴዎች የለውጡ ዋና ገፊ ኃይሎች ቢሆኑም ለውጡን ያመጡ ብቸኛ ኃይሎች አይደሉም። አውሬውን ለማምከን የመጨረሻውን ጥይት ነው እንጂ የተኮሱት የወያኔ አገዛዝ ሥርዓት ብቻቸውን አይዸለም ያዳከሙትም፤ የታገሉትም። እነዚህ የወጣት ንቅናቄዎች የተፈጠሩት ሥርዓቱ በብዙ መልኩ በተዳከመብት ወቅት ነው። ስለዚህ እነዚህን የለውጥ ኃይሎች እንደ ፈረስ ለመጋለብ በማሰብ የሚደረጉት ከልክ ያለፈ ሙገሳና ቁለላ ወጣቶቹ በራሳቸው እንዲታበዩ፣ መንገድ እንዲስቱ፣ ገና መሬት ባልረገጠ የለውጥ ድል ባለቤትነት ስሜት እንዲሰክሩ እና ያሻቸውን ማድረግ እንደሚችሉ ሆነው እንዲሰማቸው ያደርጋል።
-
ይህ ለውጥ የአንድ ወይም የተወሰኑ ቡድኖች፣ የአንድ ወይም የተወሰኑ ብሄር፣ የአንድ ፓርት፣ የአንድ የህብረተሰብ ክፍል የትግል ውጤት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። አንዳንድ የፖለቲካ አመራሮች እና ታዋቂ ግለሰቦች እየደጋገሙ ይህ ለውጥ የተወሰኑ ኃይሎች የድካም ውጤት አድርገው መግለጻቸው ሌሎችን ይገፋል። የወያኔ ሥርዓት ሥልጣን ከያዘበት የዛሬ ሃያ ሰባት አመት ጀምሮ ብዙዎች ሥርዓቱን ሲታገሉ አልፈዋል፣ ብዙ ሺዎች ለእስር እና ስቃይ ተዳርገዋል። በ1997ቱ ምርጫ እንኳን ከሁለት መቶ በላይ ወገኖቻችን በአዲስ አበባ እና የተለያዩ ከተሞች ተገድለዋል። ወያኔን በሦስት ዓመት ትግል ነው የጣልነው ብሎ የሚያቅራራ ካለ ግብዝ እና በእነዚህ አመታት ውስጥ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተሰውት ሰማዕታት ደም የሚቀልድ ቁማርተኛ ብቻ ነው።
-
አክራሪ ከሆኑ ፖለቲከኞች እና በአክቲቪስት ስም እኩይ የሆኑ የፖለቲካ አጀንዳዎችን የሚያራምዱ ሰዎች ደጋግመው ሲናገሩ የነበረው ዘር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ፖለቲካም በብዙ ወጣቶች እዕምሮ ውስጥ ምን እንደፈጠረ በእነዚህ ሁለት እና ሦስት ቀናት ውስት በግልጽ እየታየ ነው። ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ድርጊቶች በተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ እና በአንዳን ክልሎች ተስተውሏል። ቄሮን በርቀት ሲመሩ የነበሩት እነ ጃዋር መሃመድ እና ጸጋዮ አራርሳም ዘር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ባለፉት አመታት ያለ ምንም መታከት ሲረጩ ኖረዋል።
-
አቶ ጃዋር ቄሮን ሁለተኛ መንግስት ነው፣ ያሻውን የማድረግ አቅም አለው እያሉ ወጣቶቹን ሲያነሳሱ ቆይተዋል። ጸጋዮ አራርሳም በግልጽ በሚዲያ ላይ እየወጣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ውጭ ያለውን የአዲስ አበባ እና በሌሎች የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ “መጤ ነው” እያለ ወጣቶቹ አይምሮ ውስጥ ጥላቻ እንዲሰርጽ በማድረግ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። በተመሳሳይ በአማራ ክልልም አንዳንድ ወጣቶች ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በክልሉ ውስጥ ተንቀሳቅሰው ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ በማህበረ ድረ ገጾች ቅስቃሳ ሲያደርጉ ብግልጽ እየታየ ነው። እነዚህ እኩይ የሆኑ አስተሳሰቦችና እርምጃዎች የዜጎችን መብትና ነጻነት ከመገደቡም በላይ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ እና የሰው ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል።
-
ሌላው እኩይ ኃይል መቀሌ የከተመው ሦስተኛው መንግስት፤ ህውሃት ነው። የሕውሃት አመራሮች ትላት የኦሮሞን ወጣቶች ኦነግ ናችሁ እያለ ሲያስር፣ ሲያሰቃይ እና ከአገር ሲያሰድድ እንዳልቆየ ዛሬ በአዲስ አበባ እና ዙሪያው አካባቢ በወጣቶች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ሊያተርፍበት በአክቲቪስት ስም ባደራጃቸው ሰዎች በኩል እያደረገ ያለው ጥረት እጅግ አሳፋሪ እና የሚያስጠይቅ ነው። በተጨማሪም ሕውሃት የለውጡ እንቅፋት መሆኑን የሚያመላክቱ በርካት ነገሮች በየቀኑ መታየታቸው እና በመንግስት አካልት ጭምር ተደጋግመው መገለጻቸው ሕዝቡ በለውጡ ላይ እምነት እንዲያጣ ወይም ስጋት እንዲገባው እያደረገ ነው። የመቀሌው ጉዳይ አፋጣኝ እልባት ይፈልጋል።
-
ሌላው መዘንጋት የሌለበት ቄሮም፣ ፋኖም፣ ዘርማም ሆነ ሌሎች የወጣት ንቅናቄዎች ህውሃት የሚመራውን የወያኔን አስተዳደር ሊያሸንፉ የቻሉት የየክልሉ መንግስታት በተለይም ኦህዴድ እና ብአዴን አውሬውን በማዳከም እረገድ ትልቁን ድርሻ በመወጣታቸው ነው። እነዚህ ድርጅቶች የህውሃት ፈረስ ሆነው የገዛ ወገኖቻቸውን በመጨፍጨፉ ወንጀል ላይ ተባባሪ ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ የዛሬዋ ነጻነት ወይ ህልም ሆና ትቀራለች፤ አለያም አመታትን ያስቆጥር ነበር። በሰው እና በንብረት ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውም ጉዳት በብዙ እጥፍ ይሆን ነበር። እነዚህ የወጣት ለውጥ ገፊ ኃይሎች በመንገድ ላይ የጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴ ተቀብለውይ ወደ ሰከነ የሥርዓት እንዲያመራ ያደረጉት እነዚህ ድርጅቶች ናቸው።
ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ያለኝ ማሳሰቢያ፤
-
ወጣት ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም በለውጡ ላይ ትልቅ ተሳትፎ እና ድርሻ የነበራችው ሁሉ የፖለቲካ ኃይሎቹ በገቡበት የቁርሾና የመጠላለፍ ባህል ተጠልፋችው እራሳችውን ያረጀ እና ለአገርም ያልበጀ የፖለቲካ ጋሪ ጎታች ፈረስ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ። ተደጋግሞ እንደተገለጸው የአገራችን ፖለቲካ በተንኮል የተሞላ ነው። ወጣቱ ከዚህ አዙሪት ውስጥ እራሱን ማውጣት እና ማራቅ አለበት። ጥላቻ እና ጸብ የዘመናዊ ሰው መገለጫዎች አይደሉም። በእርስ በርስ ግጭት አሸናፊ መሆን እና አገርን መለወጥ የሚቻል ቢሆን ኖሮ ዛሬ ያየናትን ትንሽ ነጻነት ለማግኘት ከአርባ አመታት በላይ ባልፈጀብን ነበር።
-
ወደ አገር ውስጥ የገባችሁም ይሁን አገር ውስጥ ያላችው የፖለቲካ ሃይሎች እንዲሁም ገዥው ፓርቲ፤ አሁን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ እያያችሁ ወደ ድጋፍ ማሰባሰብ ዘመጃ መግባታችሁ ውጥረቱን ያሰፋዋል። ሁሉም የፖለቲካ ኃይል ለጊዜው ትንፋሹን ሰብስቦ እና የዶ/ር አብይን አስተዳደርም አስጨንቆ ይዞ ማድረግ ያለበት አገሪቱ በቀጣይ ስለምትከተለው የለውጥ መንገድ እና ፍኖተ ካርታ መንደፍ ላይ ማተኮር ነው። ሕዝቡ የትም አይሄድ ይጠብቃችኋል። ለምስጋናም ይሁን ለቅስቀሳ በቂ ጊዜ ይኖራችኋል። አሁን አገሪቱን ልትታደጉ የምትችሉት እናንተ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ መንከውከዋችሁን አቁማችሁ አገራዊ ጉባዔ ማካሄድ ስትችሉ ብቻ ነው። የውድድር መደላድሉን ሳታመቻቹ እናንተ ካሁኑ የፉክክር ስሜት ውስጥ መግባታችሁ ነው ደጋፊዎቻችሁን፤ በተለይም ወጣቶቹ ወደ ፉክክር እንዲገቡ ያደረጋቸው። ወጣቶቹ ለጊዜው የሚፎካከሩበት የፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ የተለየ ዕርዮት አለም ስለሌላቸው በሚይዙት ባንዲራ እርዝመት፣ በየግርግዳው ላይ በለቀለቁት ቀለም መጠን እና በሰልፋቸው እርዝመት ነው የሚጋጩት። ይህ የፉክክር ስሜትም አሁን ወደ ለየለት ጸብ እና ሥርዓት አልበኝነት እየተቀየረ ነው። ከመዘግየቱ እና ብዙ ዋጋ ከማስከፈሉ በፊት እናንተ ሰክናችሁ ወጣቱም ሰከን እንዲል አድርጉ።
-
መንግስት ሕግ እና ሥርዓትን ከማስከበሩ ጎን ለጎን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአገር ውስጥ ስለተሰባሰቡ እና ሌላ የሚጠበቅ ኃይልም ስለሌለ ባፋጣኝ አገራዊ የምክክር ጉባዔ ሊጠራ እና የተቃዋዊ ፓርቲዎች ጋር በመምከር ከሕገ መንግስቱ ባሻገር ሁሉም ኃይሎች የሚገዙለት የጨዋታ ሕግ ማርቀቅ እና ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ አለበት።