ማታ ሰልፍ እና የታክሲ አድማ እየተባለ ፌስቡክ ላይ ሲሰራጭ፣ ሰልፉን መገደብ ባይቻልም የታክሲው አድማ ግን መደረግ እንደሌለበት ፅፌ ነበር።
ሆኖም ሰው ስሜቱ ስለተነካ የሚመራውም ስለሌለ በስሜቱ ተነሳስቶ ሰልፍ እንደሚወጣ ጠብቄ ነበር፣ ጠዋት ከቤቴ ስወጣ ሰልፍ ይጀመራል ብዪ ግን አልገመትኩም ነበር፣ ሆኖም ገና አንዋር መስጂድ ስደርስ ጎርፍ የሆነ ህዝብ መፈክር እያሰማ ከወደ አውቶብስ ተራ ሲመጣ ተመለከትኩ፣ በቃ ቁር መንገድ እቀምሳለው ብዪ ሰልፉን ተቀላቀልኩ፣ ሰው እራሱን እያሰተባበረ፣ እራሱ ሰላሙን እያስከበረ፣ እራሱን እየመራ ጉዞ መዘጋጃ አርጎ ወደ ጊዮርጊስ ተጓዘ።
በየመንገዱ የሚገኙ ፖሊሶች እንደማንኛውም ሰው ከማየት ውጭ ምንም አይተናኮሉም ነበር፣ ከዛም በፒያሳ አርገን ቸርቸርን ተያያዝነው፣ አንዳንድ ሰው በመሃል የተከፈቱ ሱቆችን ሲያይ ዝጉ! እያለ ሲጮህ ከመሃል የወጡ ወጣቶች ነበር ለማረጋጋት የምነወሞክረው፣ ወጣቱ እርስ በእርሱ መደማጡ ያስደስት ነበር፣ፖሊስም ሆነ ፌደራል በህዝቡ መሃል እያቆራረጡ በመኪናቸው ሲያልፉ ወጣቱ ፌደራል እኛ ነው! የሚል መፈክር ያሰማ ነበር፣ እነሱም በፈገግታ ነበር የሚያልፉት።
በዚህ አይነተ ሆኔታ ቸርቸርን ጨርሰን EBC ህንፃ ጋር ደረስን፣ ለፊት ለፊት አድማ በታኝ ፖሊሶች ቆመዋል ሰው ከእነሱ ጋር እንዳይጋጭ እዛው የነበር ወጣቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን ሰው ወደ አምባሳደር አቅጣጫ እንዲሄድ አደረግነው፣ ወደ እዛ አቅጣጫ መስመር መያዙን ስናረጋግጥ ወደ ሰልፉ ገባን ወዲያው ከወደ ፊት አካባቢ ተኩስ ይተኮስ ጀመር፣ ሰው ተሯረጠ፣ እኔ ብዙውን ጊዜ እንደማደርገው ዝም ብሎ ከመሮጥ ጥጌን ይዤ ወደ ፊት ጠጋ ለማለት ሞከርኩ፣ በዚህ መሃል ቀይ ለባሾች እየተኮሱ እንደሆነ አየሁ፣ ከፊት ለፊት የተወሰኑ ሰዎች ሲወድቁ አየሁ።
እዛው ካገኘኋቸው ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተነጋግረን ሰውን ማረጋጋት እና ወደ ቀይ ለባሾች ጠጋ ብለን ለምን ተኮሳቹ!? ብለን ስንጠይቅ፣ በዱላ ሊያስፈራራን ሲሞክር፣ ዝም ብለን ቆምን ከመሃላቸው አንዱ ወደ እኛ ሲያነጣጥር፣ የእራሱ ጓደኛ ጨምድዶ ይዞት ወደ ኋላ መለሰው እና ወደ እኛ መጥቶ እንባ እየተናነቀው ለሞቱት እናዝናለን ያልታሰበ ነው እያለ ይናገራል፣ እሺ ሬሳዎቹን ስጠን!? የሚሉበወጣቶች ነበሩ፣ ቆይ አምፑላስ ይመጣል በቀ እናንተ ሂዱ ይላል፣ በዚህ መሃል ቀዥቃዣው ወንድማቹ በለመደ እጁ ሞባይሌን አውጥቼ ፎቶ አነሳሁ፣ ቀይ ለባሹ ፊት ለፊት እያየኝ ሰለነበር ዱላውን ሰነዘረብኝ በዚህ ቀጫጫ እጄ ቀብ አርጌ ይዤ ስንፋጠጥ በመሃል ወጣቶች ተረባርበው ወደ ዳር አስወጡኝ፣ ሆኖም ከዛ በኋላ ሊተናኮለኝ አልፈለገም፣ በወቅቱ እንዳየሁት መከላከያንም ይጠብቁ የነበሩ መተኮሱ ገርሟቸው ሰውን ለማረጋጋት ይሞክሩ ነበር፣ ፌደራሎችም በቃ ተረጋጉ የሞቱትን እኛ እናነሳለን፣ እያሉ ህዝቡን ለማረጋጋት ሲተጉ አይቻለው፣ የፀጥታ አስከባሪው እንደዚህ እየተባበረ ለምን ሰው እንደሞተ አልገባኝም!?
(ይህን ፅሁፍ ፅፌ ስጨርስ ፖሊስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን አምኗል)