ወያኔ፣ ኦነግ፣ አብን /መስፍን አረጋ/

ወያኔ፣ ኦነግ፣ አብን /መስፍን አረጋ/

ከጀታው ተላቆ ወደቀ ምሣሩ

ይሻለው ነበረ ተዋዶ መኖሩ::

ብቻውን በቁሙ ስለማይኖረው ኃይል

ተንቆ ይኖራል ዝጎ እስከሚጣል::

ጎጠኛ ማይም ነው ደንቆሮ የማያቅ

ከክፍሎቹ ድምር ሙሉው እንደሚልቅ::

አንድ ድር ቢበጠስ ተስቦ ባንድ ጣት

መቶ ድር በጅ አይልም ቢስቡት በምዕት::

ይህንን እውነታ ሲገልጽ አሳጥሮ

/መደመር/ ብሎታል ዐብይ ዘአጋሮ::

የስሑልን ንጥል ቴድሮስ እንደሰፋ

የመለስን ክልል ዐብይ አህመድ ያስፋ::

ክፍል ዒላ ክልል

ዐሎኛ (ተቃራኒ፣ ከዳተኛ፣ ሸፍጠኛ) ከሚለው ያማረኛ ቃል ዒላ (versus) የሚለውን መስተዋድድ(preposition) እናገኛለን፡፡  ዒላ ማለት ሲቃረኑ፣ ሲስተያዩ፣ ሲነጻጸሩ ማለት ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል ምሥራቅ ዒላ ምዕራብ (east versus west)፣ ቁር ዒላ ሐሩር ይሆናሉ፡፡

ኢጃ (ዓይን) ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ደግሞ ዒጃ-ዒጃ (vis-a-vis) የሚለውን መስተዋድድ (preposition) እናገኛለን፡፡  ዒጃ-ዒጃ ከዒላ ጋር ተመሳሳይ ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም ሲስተያይ፣ ሲዘማመድ፣ ሲነጻጸር፣ ሲመዛዘን ማለት ነው፡፡   ለምሳሌ ያህል ብር ዒጃ-ዒጃ ዶላር (birr vis-a-vis dollar) ማለት ብር ከዶላር ጋር ሲስተያይ ወይም ሲነጻጸር ማለት ነው፡፡

ክፍል ዒላ ክልል ማለት ክፍል እና ክልል የሚሉት ቃሎ ሲስተያዩ ወይም ሲነጻጸሩ ማለት ነው፡፡   ክፍለ ሀገር ማለት ያገር ክፍል ማለት ነው፡፡  ላንድ ሰው ሁሉም የሰውነቱ ክፍሎቸ የሱ እንደሆኑ ሁሉ፣  ላንድ አገር ዜጋም ሁሉም ያገሪቱ ክፍሎች የሱ ናቸው፡፡  

በሌላ በኩል ደግሞ የኔ ክልል ማለት ሌላውን የማይኮነስረው (concern) ለኔ ብቻ የተከለለ፣ የኔ ብቻ ቦታ ማለት ነው፡፡  በተጨማሪ ደግሞ የኔ ክልል ማለት፣ እኔ ተከልየ የተወሰንኩት በዚህ ቦታ ነው፣ ከክልሌ ውጭ ስለሚገኝ ስለ ሌላ ማናቸውም ቦታ ምንም ስለማይኮነስረኝ በቦታው ላይ ምንም መብት የለኝም ማለት ነው፡፡  ባጭሩ ለመናገር ክልል ማለት በተወሰኑ መብቶች የሚወሰኑበት እስር ቤት ማለት ነው፡፡  

ኦሮምያ ክልል ለኦሮሞው፣ አማራ ክልል ላማራው፣ ሱማሌ ክልል ለሱማሌው፣ ትግራይ ክልል ለትግሬው እስር ቤቶች ሲሆኑ፣ ለሁሉም የነጻነት ቤታቸው ደግሞ ጦቢያ ናት፡፡  ወያኔ ለሃያ ሰባት ዓመታት ያን ሁሉ ግፍ ሲፈጽም የነበረው አሮሞን፣ አማራን፣ ሱማሌን፣ ትግሬን … በክልል ገደብ ገድቦ ራሱን ደግሞ የሁሉም ክልሎች አዛዥ ናዛዥ አድርጎ በድፍን ጦቢያ ላይ በመንሰራፋት ነበር፡፡  አሁን የሚንጨረጨረው ደግሞ ኦሮሞና አማራ ከእስር ቤት አመለጡኝ ይልቁንም ደግሞ ሊያመልጡኝ ነው በሚል ስጋት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከማንምና ከምንም በላይ የሚጠላው ያማራ ሕዝብ ከእስር እንዳያመልጥ በግብራበሩ አብን (አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) አማካኝነት የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡

ብሔረ አማራ ዲሚክራሲያዊ  ንቅናቄ (ብአዴን)

ላለፉት ሃያ ሰባት የመከራ ዓመታት ያማራ ክልል እንደ ሌሎቹ  ክልሎች ሳይሆን የወያኔ የግል ርስትስለነበር፣ የክልሉን ሕዝብ ጭሰኛው አድርጎ የፈለገውን ጭቃሹም እየሾመና እየሻረ፣ የፈለገውን መሬት ቆርሶ ለራሱ እየወሰደና ለባዕድ እየቸረ፣ የፈለገውን ምርትና የደን ውጤት ወደፈለገው በማጋዝ እየቸበቸበ፣ የፈለገውን ጭሰኛ አማራ እየደፈረ፣ እያሰረ፣ እያሰቃየና እየገደለ ፣ በማናለብኝ መንፈስ እየታበየ እንዳሻው ሲሞዳሞድበት ነበር፡፡ አማራ በወያኔ የተዋረደውን ያህል በጣልያን አልተዋረደም፡፡

ግዙፉ የኦሮምያ ክልል ይቅርና፣ ትናንሾቹ ክልሎች (ሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል) በወያኔ ዘመን የነበራቸው አንጻራዊ ነጻነት ትልቁ ያማራ ክልል ከነበረው ነጻነት ሺ ጊዜ ይበልጥ ነበር፡፡  የነዚህ አናሳ ክልሎች የወያኔ ተለጣፊ አመራሮች ቢያንስ ቢያንስ ክልላቸውንና የክልላቸውን ሕዝብ የሚጠሉ አልነበሩም፡፡  ያማራው ክልል የወያኔ ተለጣፊ አመራሮች (በተለይም ደግሞ በረከት ስምዖን እና አዲሱ ለገሰ) ግን ከስብሃት በላይ ወያኔ፣ ከመለስ በላይ ፀራማራ ነበሩ፡፡  ሥራቸው ሁሉ መራራ ፀራማራ መሆናቸውን ለወያኔ አለቆቻቸው በተግባር ማሳየት ስለነበር፣ ክልሉን በሁሉም መስፈርቶች (በትምህርት፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ወዘተ.) የሁሉም ክልሎች ውራ አደረጉት፡፡

በቀሩት ሁሉም ክልሎች ባንጻራዊ ደረጀ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ ት/ቤቶች በየጎጡ ሲሠሩ፣ ባማረ ክልል ግን ቅድመወያኔ የነበሩት ት/ቤቶች ስማቸው ብቻ ተለውጦ በቆሙበት እንዲበሰብሱ ችላ ተባሉ፡፡  ላብነት ያህል በጦቢያ የመጀመርያው ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የነበረው በደሴ ከተማ የሚገኘው አንጋፋው የንጉሥ ሚካኤል ት/ቤት አሁን በሚገኝበትፍርስርስ ሁኔታ ለልጆች መማርያነት ቀርቶ ለሲሚንቶ መጋዘንነትም አደገኛ ነው፡፡  ንጉሥ ሚካኤልና የቀሩት ያማራ ክልል ት/ቤቶች በቁማቸው እንዲፈራርሱ ወያኔ የሰጠውን ጥብቅ ትእዛዝ በታታሪነት ታስፈጽም የነበረችው ደግሞ ወሎየ ነኝ የምትለው (ወሎየወች ዮዲት ጉዲት የሚሏት) ገነት ዘውዴ፡፡  በማራ ክልል በሚገኙት አሸር ባሸር ት/ቤቶች የተማሩ  ተማሪወች ሥራ እንዳያገኙ ደግሞ በመንግሥት መ/ቤቶች ያማራ ተቀጣሪወች ኮታ እንዲቀነስ አማራን እወክላለሁ የሚለው በወያናዊ የቁጩ ስም ተፈራ ዋልዋየሚባለው ያቅም ግንባታ ሚኒስቴር በቴሌቭዥን መስኮት ግልጽ ትእዛዝ ሰጠ፡፡  

የሁሉም ክልሎች የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምር፣ ያማራ ሕዝብ ግን መክኖ፣ ተኮላሽቶ፣ በጥይት ተረፍርፎ፣ በበሽታ ረግፎ ቁጥሩ በሚሊዮኖች እንዲቀንስ ተደረገ፡፡  ያማራ ሕዝብ ቁጥር ለማመን በሚያስቸግር መጠን መቀነሱን ደግሞ ያማራ ክልል መሪ ነኝ ይል የነበረው ታላቁ ፀራማራ አዲሱ ለገሰ፣ የተሰጠኝን ተልዕኮ ከተጠበቀው በላይ አሳክቻለሁ ከሚል ስሜት በመነጨ የኩራት መንፈስ እየተጀነነ ፓራላማ ላይ ተናገረ፡፡  ሰይጣኑ መለስ ዜናዊ ደግሞ ባሽከሩ ሥራ በመደሰት ጨጎጎት ፊቱን በፈገግታ አፈካ፡፡  

ወያኔ መሠረታዊ ጠላቴ ነው የሚለውን አማራን ለማጥፋትና ከጥፋት የተረፈውን ደግሞ በማሸማቀቅ አንገቱን ለማስደፋት ያልፈነቀለው ዲናጋ፣ ያልቆፈረው ጉደጓድ አልነበረም፡፡   ላብነት ያህል የትግራይ ክልል ዐልማቅ (flag) ውራጅ የሆነው ያማራ ክልል አሳፋሪ ዐልማቅ እና በክልሉ መዲና በባሕር ዳር የሚገኘው ኔፋል ወደብ (airport) አሳፋሪ ስያሜ፣ የክልሉ ባለርስት ማን እንደሆነ ለማያውቅ በግልጽ ማሳወቂያወች ነበሩ፡፡

የወያኔ ጭቃሹሞቹ ስብስብ የሆነው ብአዴን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጭቃሹምነት በቃኝ፣ ካሁን በኋላ ያማራን ክልል ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ሽንጤን ገትሬ የምታገል የክልሉ ሕዝብ ምስለኔ ወይምእንደራሴ እሆናለሁ ማለት ጀምሯል፡፡   ይህን የሚለውእንደ ወትሮው አልኩ ለማለት ሳይሆን የምሩን መሆኑን ያማራ ሕዝብ እንዲያምንለት ከፈለገ ግን ጭቃሹምነታቸውን ሙጥኝ ያሉትን አባሎቹን አንድም ሳይቀር ሁሉንም (በረከት ስምዖን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ታደሰ ካሳ፣ አለምነው መኮንን፣ ህላዊ ዮሴፍ፣ ዳዊት ዮሐንስ፣ ከበደ ጫኔ፣ ካሳ ተክለብርሃን ወዘተ..) ሙልጭ አድርጎ አስወግዶ ባማራ ሕዝብ ላይ ለፈጸሙት ወደር የለሽ ወንጀል ተጠያቂ በማድረግ ለፍርድ ካቀረባቸው በኋላ፣ ክልሉን ከወያኔ ቆሻሻ ሙልጭ አድረጎ የማጽዳት ሥራውን ሀ ብሎ መጀመር ያለበት በክልሉ ዓልማቅና በባሕርዳሩ ኔፋል ወደብ ስያሜ ነው፡፡

ያማራ ክልል ሕዝብ ውርደት መግለጫ የሆነው የትግራይ ውራጅ ጨርቅ ካለበት ሁሉ ተሰብስቦ መቃጠል፣ አለያ ደግሞ በጨዋ ደንብ  አኮቴ ግን አልፈልግም (thanks, but no thanks) በማለት ከጨርቁ በተሰፉ ስልቻወች ታጭቆ ተጭኖ ለባለቤቱ ለወያኔ መላክ አለበት፡፡  ቢፈልግ በልዋጭ ልዋጭ ቁሳቁስ ይግዛበት፡፡

አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

ወያኔ ላስራ ሦስት ዓመታት በሽፍትነት ላስራ ሰባት ዓመታት ደግሞ ባምባገነንነት በጠቅላላው ላርባ ዓመታት በጦቢያ ሕዝብ ላይ በተለይም ደግሞ በቀንደኛ ጠላትነት በፈረጀው ባማራ ላይ ፈጸመውሰይጣናዊ ግፍጭቆና፣ ሰቆቃና ጭፍጨፋነውርና ብልግና ሳቢያ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰኘው ትናንት መጤ ድርጅት በክልሉ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል፡፡

አብዛኛው የአብን ደጋፊ በቅጡ ያልተረዳው ግን አብን በግልብ ሲመለከቱት ላማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚታገል ሲምካአማራ (proamhara)ቢመስልምበደንብ ሲያስተውሉት ግን ከወያኔ ባይብስ እንኳን የወያኔን ያህል ፀራማራ (ፀረ አማራ) መሆኑን ነው፡፡ ፀራማራ ያሰኘው ደግሞ እኩይ ዓላማው ነው፡፡

እልፍ አእላፍ ጦቢያውያን ለእልፍ ዓመታት ደማቸውን እያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን እየከሰከሱ ጦቢያ የምትባል፣ ዳር ዳሯ እሳት መኻሏ ገነት የሆነች፣ በውበቷ ወደር የሌላት ባለ አስራ አራት ክፍል ትልቅ ቤት ሠርተው ለማናቸውም ጦቢያዊ በመረጠው ክፍል ውስጥ በቤተኝነት የመኖርና ከክፍል ክፍል እንዳሻው የመዘዋወር ሙሉ ነጻነት አጎናጽፈውታል፡፡

ወያኔ ደግሞ ክፍሎቹን ወደ ክልሎች ቀይሮ የክልሉን ነዋሪወች በመሠረተቢስ መስፈርት መጤ በማለት ከፋፍሎ ጤወቹን ቤተኛ መጤወቹን ኪራይተኛ አደረጋቸው፡፡

የአብን ዓላማ ደግሞ የወያኔን መሠረተቢስ ክለላ በመተግበር ያማራ ሕዝብ አብናቶቹ (ማለትም አባቶቹ እና እናቶቹ) በገነቡለት የራሱ በሆነችው ጦቢያ በምትባለው ትልቅ ቤት ውስጥ ተስፋፍቶና ተንሰራፍቶ ከመኖር ይልቅ፣ በቤቱ ውስጥ በምትገኝ፣ ወያኔ በሁሉም አቅጣጫወች ኮርኩሞ ባጠበባት፣ የበሬ ግንባር በምታክል ትንሽ ክፍል ውስጥ በመጨናነቅ ተጨብጦ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡  በሌላ አባባል የአብን ዓላማ ያማራን ሕዝብ አማራ በሚባለው ክልል ከልሎ በማጎር የክልሉ እስረኛ አድርጎ ጦቢያዊነትን መንፈግ ነው፡፡  

ስለዚህም አብን ፀራማራ ብቻ ሳይሆን ፀረጦቢያም ነው፡፡  የፀረጦቢያነት ሊቅ ደግሞ ወያኔ ነው፡፡  ስለዚህም ለመመንጠር ካልፈለጉ በቀር፣ አብን የወያኔ ደቀመዝሙር መሆኑን መጠርጠር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ አብን ያማራ ለምድ የለበሰ የወያኔ ተኩላ እንደሆነ የሚያጋልጡት አያሌ ምልክቶች አሉ፡፡

አብዛኛው ያማራ ክልል ሕዝብ (ከሌሎች ክልሎች ጦቢያዊ ወገኖቹ ጋር በመተባበር) አያሌ ልጆቹን ለእስር፣ ለስቃይ፣ ለኩልሽትና ለሞት እየገበረ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለበት ወያኔ የነፈገውን ጦቢያዊነቱን መልሶ የማስከበር እልክ አስጨራሽ ተጋድሎ ከድል አፋፍ ሲደርስ፣ አብን የሚባለው መሠሪ ድርጅት በድንገት ተከስቶ ተጋድሎውን መና ለማስቀረት መጣጣር ጀመረ፡፡  ይህ የሚያመለክተው ደግሞ አብን ባማራ ጠላቶች የተሠየረ አደገኛ ፀራማራ ሤራ መሆኑንና፣  ቀንደኛ ሠያሪው ደግሞ በፀራማራነት ደቁኖ የቀሰሰው መሠሪው በረከት ስምኦን ሳይሆን እንደማይቀር ነው፡፡  

ወያኔ ጦቢያን ወደ ሞት አፋፍ እየወሰዳት በነበረበት ጨለማ ዘመን የትም ያልነበረው አብን፣ ጎሕ ቀዶ ጦቢያ ማንሰራራት ስትጀምር ከየት መጣ ሳይባል በድንገት ተፈጠረ፡፡  የጦብያውያን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ጥቁር ሕዝቦች መኩርያ የሆነውን ሞኣ አንበሳ (የድል አድራጊውን አንበሳ) ጥላቻ ከወያኔ እንደቀሰመ በሚጠቁምበት ሁኔታ ደግሞ ዐርማውን የምዕራባውያን ዘረኞችና ቅኝ ገዥወች መታበያ የሆነውን ንሥር አደረገ፡፡  ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ እንደሚባለው ደግሞ ወያኔ አምርሮ የሚጠላውን ታላቁን ጦቢያዊ ታማኝ በየነን ባማራ ሕዝብ ለማስጠላትና የመናገር መብቱን ለመግፈፍ ሞከረ፡፡  እድሉን ካገኘ ደግሞ መንቀሳቀሱን ብቻ ሳይሆን እስትንፋሱንም እንደሚያቆም አመላከተ፡፡  ይህ ሁሉ የሚያሳየው ደግሞ አብን የሚባለው ባቄላ ካደረ እብን ሁኖ ስለማይቀረጠም አስቀድሞ መቃምእንደሚበጅ ነው፡፡  ሳይቀጠል በቅጠል፣ ሳያብን በእብን፡፡  ሳይደነግይ በድንጋይ፡፡  አብን ሳያብን በእብን፡፡

አማራ ማለት ከጎጠኝነት በፀዳ ስሜት ዘር ወይም ሐይማኖት ሳይጠይቅ ተጋብቶና ተዋልዶ በሁሉም የጦቢያ ክፍሎች በቤተኛነት እየኖረ የጦቢያን ሕዝቦች ባንድነት ያሰናሰለ ሰንሰለት ማለት ነው፡፡  ወያኔ አማራን ማፈናቀሉን ተቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው ደግሞ ጦቢያን ገነጣጥሎ ለመበታተን ይችል ዘንድያሰናሰላትን አማራዊ ሰንሰለት መበጣጠስ እንዳለበት ስለሚያውቅ ነበር፡፡  አብን አማራን ጎጠኛ ለማድረግ የሚጣጣረው ደግሞ አሰናስሎ አስተሳሳሪ የሆነውን አማራን አስፈንጥሮ በታታኝ በማድረግ ጦቢያን ዳግማዊ ዩጎዝላቪያ ለማድረግ ነው፡፡

ወያኔና አብን መምህርና ደቀመዝሙር ስለሆኑ፣ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታወች ናቸው፡፡  አብን ለማጠናቀቅ ያለመው፣ ወያኔ ካርባ ዓመት በፊት ጀምሮት ከፍጻሜ አፋፍ ያደረሰውን እኩይ ሥራ ነው፡፡

ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ማራ ጥላቻ አስክሮበርስበርስ ጦርነት በመማገድ የስልጣን መቆናጠጫ ጭዳ አደረገው፡፡  የወያኔ ደቀመዝሙር የሆነው የአብን ዓላማ ደግሞ ዘረኝነትን ነቃፊ፣ ጥበትን ተጸያፊ፣ ሁሉን አቃፊ፣ ልበሰፊ የሆነውን ታላቅ ሕዝብ፣ ደደቢት በርሓ በሚበቅል የጎጠኝነት አብሾ መርዞአፍዞ በማደንገዝ የስልጣን መወጣጫማድረግ ነው፡፡

አብንን መደገፍ ማለት በፊት በር እያዋከቡ ያባረሩትን እኩዩን ወያኔ በኋላ በር እየተንከባከቡ ማስገባት ማለት ነው፡፡  ያማራ ሕዝብ ከቀረው የጦቢያ ሕዝብ (በተለይም ደግሞ ከኦሮሞ ሕዝብ) ጋር በመቀናጀት ወያኔን እምብርቱ እተቀበረበት እደደቢት ሊቀብረው እቀብሩ አፋፍ እንዳደረሰው፣ አብንንም በተመሳሳይ መንገድ ሊያከስመው ይገባል፡፡   ያማራ መብት የሚከበረው የጦቢያውያን መብት ሲከበር ብቻ ስለሆነ፣ ትግሉ ማትኮር ያለበት ጥቃቅኑ ዝርዝር ላይ ሳይሆን ትልቁ ሥዕል ላይ ነው፡፡

ወያኔ ማለት በመሠሪነታቸው አምሳያ በሌላቸው በነበረከት ስምዖን የሚመራ መሽለኩለኪያውን እንኳን ሌላው እሱ እራሱ አስቀድሞ የማያውቀው አደገኛ እባብ መሆኑን የጦቢያ ሕዝብ በደንብ ያውቃል፡፡  በእባብነቱ ምን ያህል እንደተካነበት ግን አብዛኛው ሕዝብ በሚገባ የተገነዘበ አይመስለኝም፡፡  በዚህ ምክኒያት ነው ወያኔ አንዱ ሤራው ሲነቃበት፣ ሌላ ሤራ እየፈጠረ ሲያታልል የኖረው፡፡  ወያኔ ማለት አንዱን ጉድጓድ ሲደፍኑበት ባልታሰበበት ሌላ ጉድጓድ ወዲያውኑ ብቅ የሚልብአዴንን ሲዘጉበት አብንን የሚከፍት የተረገመ ሸለመጥማጥ ማለት ነው፡፡  ወያኔ ማለት እንዳመችነቱ መልኩን እየቀያየረ ደም የሚጠጣ በጥላቻ የተመረዘ፣ ባፍቅሮተ ነዋይ የሰከረ፣ በእኩይ ባሕርያት የተጨማለቀ፣ ጭካኔው ድካት (limit) የሌለው እስስታዊ ጭራቅ ማለት ነው፡፡  

የወያኔ ጥፍጥፍ የሆነው አብን ደግሞ የወልቃይትን፣ የመተከልንና የራያን ጥያቄ የሚደሰኩረው በጥያቄወቹ ፍትሐዊነት በማመን ሳይሆን፣ ያማራን ለምድ በመልበስ አማራን አታሎ በበጎች መኻል በመሠማራት ወያኔ የሰጠውን ጭራቃዊ ተልእኮ ለማሳካት ብቻና ብቻ ነው፡፡  ባማራ ጫንቃ ተፈናጦ በለስ ቀንቶት ስልጣን ቢጨብጥ ደግሞ የመጀመርያ ሥራው የሚሆነው እነዚህን ፍትሐዊ ጥያቄወች የሚያነሱትን ግለሰቦች ስማቸውን አጠልሽቶ እያሳደደ ድምጥማጣቸውን ማጥፋት ነው፡፡

ወያኔ ታማኝ በየነንና መሰሎቹን ሕብረብሔራዊ ጦቢያውያን በቀጥታ ማጥቃት አላዋጣው ሲል ስልቱን (tactic) በመቀየር በአብንና በግብራበሮቹ አማካኝነት በተዘዋሪ መንገድ ያጠቃቸው ጀመር፡፡  ወያኔ ስልቱን እንዳመችነቱ ቢቀያይርም ትልሙ(strategy) ግን መቸም የማይቀየር ቋሚ ነው፡፡  የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ሊያሳካው የሚቋምጠው ቋሚ ትልሙ ደግሞ ጦቢያዊነትን ማሽመድመድ  ነው፡፡

አንባቢ ሆይ፣ እስኪ ራስወን ይጠይቁ፡፡  አብን የጦቢያዊነት ቀንደኛ ጠላት በሆነው ወያኔ ላይ ከማለም ይልቅ፣ ጦቢያዊነትን በሚያቀነቅነው ሕብረብሔራዊ ግንቦት ሰባት ላይ ለምን አነጣጠረ? ወያኔ ሁሉን በጁ በደጁ አድርጎ፣ አዛዥ ናዛዥ ሁኖ ጦቢያውያንን መቆሚያና መቀመጫ ባሳጣበት ድቅድቅ ጨለማ ዘመን ያልነበረው አብን፣ ጎህ መቅደድ ሲጀምር ከየት ብቅ አለ?   ስም ባለፈ ደረጃብቸኛ ሕብረብሔራዊ ድርጅት በመሆን ፀረ ወያኔነቱን በተግባር ያስመሰከረውን ግንቦት ሰባትን ነጋ ጠባ የሚወቅሱና የሚከሱት ጋዜጠኛ ተብየወችስ ድርጓቸውን የሚሠፍርላቸው ማን ነው?   ግንቦት ሰባት ላይ ጸያፍ ዘለፋወችን ማዝነብ የማይታክታቸው ወያኔያዊ ማሕበራዊ ሂርሳኮች (social media) ቆዳው ሲታይ በፀረ ወያኔነቱ ወደር የሌለው በሚመስለው አብን ላይ ትንፍሽ የማይሉት ለምንድን ነው?  

ወያኔን የነቀፈ ይቅርና ለመምከር የሞከረ ሁሉ ማዕከላዊ ተከርብጆ (tortured) ዓለም በቃኝ በሚወረወርበት ያፈና ዘመን ያሻውን ሁሉ በሙሉ ነጻነት እየለፈለፈ፣ የጦቢያን እጣ በተመለከተ ከኔ በላይ አዋቂ ላሳር ነው በሚል ስሜት በሁሉም ቦታ እዩኝ እዩኝ ሲል ኖሮ፣ ወያኔ ራሱ በፈለፈለው ዋሻ ውስጥ ተከርችሞ አንጻራዊ ነጻነት ሲሰፍን ግን ለሂወቴ ስለፈራሁ ደብቁኝ፣ ደብቁኝ ያለው ሽከታ(politics) ቁማርተኛው ልደቱ አያሌው፣ ግንቦት ሰባት በመጣ ማግስት ቃሉን አጥፎ የግንቦት ሰባት አመራሮችን በመጠዝጠዝ የወያኔን ቆሻሻ ከማጽዳት ዋና ዓላማቸው ሊያዘናጋቸው የሚጣጣረው ለምንድን ነው?  በመጀመርያ ነብታሚ (professor) አስራት ወልደየስን አንድዶ እንጀራውን አበሰለ፡፡  ቀጥሎቅንጅትን ለማፍረስ ያንበሳውን ሚና ተጫውቶ የወያኔን እድሜ በመቀጠል የጦቢያውያንን መከራ ባሥራ  ሦስት መት አረዘመ፡፡  አሁንስ?  መቀሌ ሂዶ ያማራ ደም እጃቸውን ካቀላው ቀንደኛ ወያኔወች ጋር አብሮ በመታደም፣ ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበትን የተጋድሎ ውጤት በማንቋሸሽ ዐብይ አብዮት ቶሎ ታይቶ ቶሎ የሚጠፋ ንፋስ ያነሳው አቧራ በመሆኑ ስጋት ሊገባን አይገባም ማለትስ ምንን ይጠቁማል? ጎጠኛውን መለስን አንቱ፣ ሕብረብሔራዊውን ዲባቶ(doctor) ብርሃኑን ግን በመዘርጠጥ አንተ ማለትስ ምን ያመላክታ?  

የወያኔ ተኩላወች

ወያኔን በጨዋነት የተቹት እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌ ከሰውነት ተራ ሲወጡ፣ ወያኔን በደፋርነት ያበሻቀጡ የሚመስሉት (የሚመስሉት ይሰመርበት) ልደቱ አያሌውና ሙሸ ሰሙ ኮልኮሌ አወጡ፡፡  

የተናቀ ይነቀንቃልና፣ ጠላት ምንጊዜም ጠላት ስለሆነ ለጠላትነቱ የሚገባውን ክብር አለመስጠት ዳፋው ለራስ ነው፡፡  አሾክሿኪን ግን ……      

በጦቢያ ጥላቻው ልቡ እሚለው ቅጥል

ጎጠኛው ወያኔ የፈረንጅ ባለሟል

ባንዳነቱ ታውቆ ተለይቶ በውል

እንደ ገብስ ጠላ ገፈት በመንጓለል

ተገፍቶ እንዲወገድ በለውጥ ማዕበል

ሕዝቡ ሲነሳሳ ተቀናጅቶ በኃይል፣

የሕዝቡን አብዮት ቀልብሶ ለመጣል

ወያኔ መልምሎ ባፉ የሚደልል

ተኩላወች ይሰዳል በበጎች መካከል፡፡

እንደነ ልደቱ የኢዴፓው ባሻ

አፍን በመጠቀም ሆድን ማድበስበሻ፣

መስሎ የሕዝብ አጋር የብሶት ማበሻ

ውስጥ ውስጡን በመሆን የጎጠኛ ጋሻ

ወያኔን ሊፈጀው ባሳጣው መድረሻ

በለውጥ እሳት ላይ ውሃ መከለሻ፣

ኅሊናን በመሸጥ ለወያኔ አምባሻ

በሄደበት ሁሉ በገባበት ዋሻ

ሁሉ ተጸይፎት እንደ ርኩስ ቆሻሻ፣

መኖር ከተባለ የኑሮ ተልካሻ

ለመኖር ይቻላል እንደ መንደር ውሻ፡፡

ወያኔም ውሻውን መስሎ የሚያሞግስ

በልቡ እየናቀው እያለው ልክስክስ

ከሕዝብ ባሕር ወጥቶ የጎጥ ጤዛ እሚልስ፣

እያደፋፈረው እያለው ጃስ፣ ጃስ

ዐብዮቹን ጀግኖች ያብዮቱን ራስ

እንዲናከስ አርጎ ጥርስ እስካለው ድረስ፣

ጥርሱ ሲወላልቅ፣ ለመናከስ ሳይበጅ

ሥራውን ሳይሠራ አምባሻ እንዳይፈጅ

በር ይዘጋበታል አውጥቶ ጥሎ ደጅ፡፡

ውሻውም ይልና ተገልጦለት ያኔ

እንጀራ ሳለልኝ አምባሻ ለምኔ፣

ይጰነጥጥና በውሸት ምናኔ

በንባ እያላዘነ ስለ ጽድቅ ኩነኔ

ይሆናል ጓደኛ የታምራት ላይኔ፡፡

በየገዳማቱ በቅዱሳን ቦታ

ጦቢያ እያለቀሰች እያነባች መንታ

ዞትር እያሰማች ምሕላ አቤቱታ

የጸለየችውን እጆቿን ዘርግታ፣

ቃል ኪዳን ስላላት የናቷ ልደታ

መቸም አይቀርና የማታ የማታ

ፊቱን አዙሮላት የሰማት ቀን ጌታ፣

ፈጥና ትነሳና ከዘመናት እንቅልፍ

በእድገት ጎዳና በፍጥነት በመክነፍ

የጣሏትን ጥላ በልጣቸው በእጥፍ

የቀድሞ ዝናዋን በመጎነጻጸፍ

በክብር ዙፋን ላይ ተቀምጣ ብላ ከፍ፣

እንዳልተዋረደች ባልተገራ ክፍት አፍ

እየተወደሰች በእልፍ አእላፍ

ትገናለች ባለም ከአጽናፍ እስካጽናፍ፡፡

ኢሳያስ እንዳለው ትንቢት ሲተነብይ

ያንገት ማሰርያዋን ፈታ ባደባባይ

ማራኪዋን ማርካ ጥላ ልታደባይ፣

ዳግም ሳይበቅልባት መርዘኛ እንጉዳይ

በጸጋ ተሞልታ ተርፏት ያለም ሲሳይ፣

አሸብርቃ ደምቃ ተውባ በአደይ

ሞገስ ተጎናጽፋ ጸድላ እንደ ፀሐይ፣

እጆቿን ዘርግታ እያለች ጌታ ሆይ

ጦቢያ ትነሳለች በክብር ወደ ሰማይ፡፡

ግንቦት ሃያ

ግንቦት ሃያ ለትግራይ ክልል ባያሌ ዘርፎች እጅጉን እንደጠቀመና ክልሉን በመሠረተ ልማት፣ በትምህርትና በጤና ከሌሎች የጦቢያ ክፍሎች እጅግ እንዳናረው መካድ ማለት ግመል ሰርቆ ማጎንበስ ማለት ነው፡፡  ስለዚህም የዚህ ክልል ሰወች ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የጨለማ ዓመታት ናቸው ሲባሉ፣ በተቃራኒው የብርሃን ዓመታት ናቸው ቢሉና ድልድዩንም ግድቡንም ሕዳሴ ቢሉት አልተሳሳቱም፡፡ ባይሳሳቱም ግን አጭበርባሪው ወያኔ አታሏቸዋል፡፡ የተታለሉት ደግሞ ወያኔ መቶ ሚሊዮን ዘርፎ፣ ዘጠኛ ዘጠኙን ለራሱ ወስዶ፣ ዘረፋውን በነሱ ለማሳበብ አንዷን ሚሊዮን ብቻ ይጥልላቸው እንደነበር አለማወቃቸው ነው፡፡  ከመቶ ዘጠና ዘጠኙ የሰረቀ ሌባ መሆኑን ስለማያውቁ፣ ከመቶ ባንዱ በሠራው ተደስተው ያወድሱታል፡፡  ይበልጥ የሚረኩት ደግሞ ይህ ሥራው ከሌሎች ክልሎች ወንድሞቻቸው እንዲበልጡ ስላደረጋቸው ነው፡፡  ይህንን ከወንድም የመብለጥ እርካታ እስካገኙ ድረስ አገራቸው በሁሉም ረገዶች የዓለም ጭራ መሆኗ ማስቆጨት ቀርቶ ቅር አያሰቸውም፡፡  የደረሱበትን ከነበሩበት ጋር እያስተያዩይፈነጫሉ እንጅ ሊደርሱ ይችሉበት የነበረውን እያሰላስሉም፡፡  ዐባይን ስላላዩ ምንጭ ያመሰግናሉ፡፡  የምዕራባውያን ግሳንግስ ማራገፊያ የነበረችው ኮርያ በተራቀቁት ኪንሲናዊ (technological) ምርቶቿ አጥለቅልቃቸው የተሳለቁባትን ያህል ልትስቅባቸው የፈጀባት ጊዜ አርባ ዓመት ብቻ ነበር፡፡  

አገር አውቋቸው፣ ፀሐይ ሞቋቸው ያደባባይ ሚስጥር የሆኑትን የገነት ዘውዴን እና የቴድሮስ አድሃኖምን ወንጀሎች ብንተዋቸው እንኳን፣  መሠረተ ልማትን በተመለከተ ትናንሽ የትግራይ ኑስተማወችን (towns) አቋርጠው የሚያልፉ፣ በግራና በቀኞቻቸው የተዘረጉት ሰፋፊ የእግር መንገዶች እምብዛም ተጠቃሚ ስለሌላቸው ሣር የዋጣቸው፣ በመካከላቸው ባሉት ደሴቶች በቅርብ ርቀት የተተከሉ ዘመናዊ የመብራት ምሰሶወች የተገጠገጡባቸው፣ ባለ አራት መም (lane) የትግራይ ክልል አውራ መንገዶችን፣ የሌሎች ክልሎችን (በተለይም ደግሞ የፈረደበትን ያማራን ክልል) ትልልቅ ከተሞች ሰንጥቀው ከሚያልፉ ሻል ሲሉ ሽሮ ፈሶሶች  አለያ ደግሞ ገረጋንቲወች ጋር በማነጻጸር ብቻ የዚያድ ወልደገብሬልን  ወንጀል በገሃድ ማየት ይቻላል፡፡  በመብራት እና በግድቦች ላይ የፈጸሟቸውን ሕዝብ በዳይ አገር ገዳይ ወንጀሎች ደግሞ ምሕረት ደበበ እና አዜብ አስናቀማንቁርታቸውን ተይዘው መናዘዝ አለባቸው፡፡

በተለይም ደግሞ ትላልቆቹ ወንዞች ባሮና ዴዴሳ ከመገራታቸው በፊት መታሰብ እንኳን ያልነበረበት፣ ቢሊዮኖች ተከስክሰውበት ሚሊዮኖች የተመዘበሩበት፣ ሃይል የማመንጨት አቅሙ ካንድ የንፋስ ነኮርኳር(wind turbine) የማይበልጠው የተከዜ ግድብ ጉዳጉድ መዘክዘክ አለበት፡፡  ጣናን በትንሽ ወጭ በመንከባከብ ፍላጎትን ማርካት ሲቻል፣ ወሃው በትነት (evaporation) እና በሥርገት በከፍተኛ ስትነት (rate) የሚባክን ያሣ ማጥመጃ ኩሬ ለመሥራት ቢሊዮኖችን መከስከስባገር ክህደት አስከስሶ ለከፍተኛ ቅጣት የሚዳርግ ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡

በቁራ በረራ (as the crow flies) ካሥር ኪሎሚትር በማይዘል፣ በጠመዝማዛ የመኪና መንገድ ደግሞ ከስልሳ ኪሎሚትር በማይበልጥ ርቀት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሁለት ትልልቅ ኔፋል ወደቦች (airports)የተሠሩበት ክልል ትግራይ ብቻ ነው፡፡  ወያኔ ይሄን ትርጉም ቢስ ሥራ በማናለበኝ መንፈስ የሠራው ደግሞ መሪው መለስ ዜናዊ ኃየሎምን በማስገደሉ ሳቢያ ያኮረፈውን፣ የውየና እምብርት የሆነውን የሽሬ ከተማን ሕዝብ ለማስደሰትና በዚሁ አስታኮ ደግሞ ሚሊዮኖችን ለመዝረፍ ብቻና ብቻ ነበር፡፡  ብዙ ሚሊዮኖች የተከሰከሱበት በቀን አንድ ትንሽ ኔፋልፒዳ(airplane) ብቻ (ለዚያውም አብዛኛውን ጊዜ ከግማሽ በላይ ባዶ የሆነች) የሚያስተናግደው ኔፋል ወደብከሚያስገባው ገቢ ይልቅ ሣር እንዳይውጠው ለመከላከል የሚወጣው ወጭ ይበልጣል፡፡  

የመቀሌው ኔፋል ወደብ (airport) ባሉላ አባነጋ፣ የአክሱሙ ደግሞ ባጼ ዮሐንስ ስም ሲሰየም፣ የባሕርዳሩ ግን ግንቦት ሃያ ተባለ፡፡  ይህ ማለት ደግሞ በወያኔወችና በግባራበሮቻቸው አተያይ ስሙ ሊዘከር የሚገባውና ለወጣቶች አርአያ ሊሆን የሚችል ጀግና በክልሉ ውስጥ የለም ማለት ነው፡፡  

ጎጠኛው ለገሰ የባንዳው ዝርያ

ከባንዳው ስብሃት በቀሰመው ሙያ

ማጥፋት ስለሚሻ አርበኛን ከጦቢያ

እንዳይሆን በመስጋት የበላይ መጠርያ

አየር ማረፊያውን አለው ግንቦት ሃያ፡፡

የባሕርዳሩን ኔፋል ወደብ በታሪካዊ ዕለት መሰየም የግድ ቢያስፈልግ እንኳንበመለስ ዜናዊ አዛዥነት በወርቅነህ ገበየሁ አስፈጻሚነት ባዲስ አበባ ጎዳናወች ለተረፈረፉት ሰማዕታት መታሰቢያ ሰኔ 1 ኔፋል ወደብመባል ነበረበት፡፡  ያጤ ኃይለ ሥላሴ የደህንነት ሃላፊ የነበረውን፣ በለጋ እድሜው ሂወቱን ከማንምና ከምንም በላይ ለሚያፈቅራት እናት አገሩ የሰጠውን፣ የታላቁን ጦቢያዊ ጀግና ዐሲና ዐምዱላ (lieutenant colonel) ወርቅነህ ገበየሁን ስም ለማጠልሸትወያኔ ወርቅነህ ገበየሁ ብሎ የሰየመው የሻሸመኔ ጭራቅ የሕጻናትን ደም ባፈሰሰባቸው ያዲሳባ ጎዳናወች በነጸነት ሲንጎባለል ከማየት የበለጠ አንጀት አቃጣይ የለም፡፡  

ግንቦት ሃያ /የመጣላቸው/ ክፍሎች ዕለቱን በያመቱ በከፍተኛ ድምቀት ባያከብሩትና የዕለቱ ውጤት የሆኑትን የተለያዩ ግዙፍ ተቋማት ባይሰይሙበት ሊያፍሩ ይገባል፣ እፍረት የሚያውቁ ከሆነ፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ ግንቦት ሃያ ለመጣባቸው ላብዛኞቹ የጦቢያ ክፍሎች ዕለቱ የሃያ ሰባት ዓመት የውርደት ዘመን መባቻ ስለሆነ፣ ውርደቱ መቸም እንዳይደገሞ እያንዳንዱን ተተኪ ትውልድ በጥብቅ ለማሳሳብ የውርደት ቀን እየተባለ በያመቱ በመሪር ሐዘን መዘከር አለበት፡፡  በግንቦት ሃያ የተጠቀመ ግለሰብ ካሰኘው ግንባሩ እና ቅንጡ ላይ በወስፌ ይወቀረው፡፡  ይሄም ሲያንሰው ነው ካለ ደግሞ ደረቱና ጀርባው ላይ በጋለ ብረት ይተኮሰው፡፡   አለያ ግን ግንቦት ሃያ የግድ መጻፍ ካለበት፣ መጻፍ ያለበት በሽንት ቤት ወረቀት ላይ ብቻ ነው፡፡

ቄሮ፣ ፋኖ

ቄሮ ማለት ሲራገጥ፣ ሲላፋ፣ ሲጫወት የሚውል ወጠጤ ማለት ነው፡፡  ስለዚህም የቃሉ ትክክለኛ ያማረኛ አቻ ውርጋጥ ነው፡፡  ውርጋጥ ያልበሰለ እንጭጭ ስለሆነ፣ መወርገጡን እንጅ የውርገጣው ውጤት ምን እንደሚሆን አስቀድሞ ማሰላሰል አይችልም፡፡

ማናቸውም ግለሰብ ጨዋነትን የተላበሰ፣ ሕገ ልቡናን (common sense) የታጠቀ፣  ግራ ቀኙን የሚያመዛዝን፣ ምራቁን የዋጠ፣ ጸያፉን የከተተ ሙሉ ሰው ከመሆኑ በፊት ማናቸውንም ሽከታዊ ድርጅት(political organization) መቀላቀል የለበትም፡፡  አለያሽከታ (politics) ቁማርተኞች መጫወቻ በመሆን፣ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት እያለ በማገዱበት ያለምንም መጠራጠር ይማገዳል፣ የሰበኩትን ያለምንም ጥያቄ ያምናል፣ ስገድ ላሉት ያለምንም ቅሬታ ይሰግዳል፣  ንከስ ያሉትን ደግሞ ያለምንም ማቅማማት ይነክሳል፡፡  

ሰው ደግሞ ሙሉ ሰው ሆነ ለመሆን የሚችለውከሠላሳ ዓመት በኋላ ነው፡፡  ስለዚህም ቄሮ ሙሉ ሰብእናን ያልተላበሰ ኮበሌ ነው ማለት ነው፡፡  ሙሉ ሰብእናን ስላልተላበሰ ደግሞ መረን እንዳይወጣ ነጻነቱ መገደብ አለበት፡፡  አለያ እንዳሻው እየወረገጠ አገር ያጠፋል፡፡

ነጻነት ፈልጎ ነጻነት ሲጠየቅ

አስቀድሞ ያሻል ምንነቱን ማወቅ፡፡

ነጻነት ሰይፍ ነው ባለ ሁለት ሥለት

አንገት እየቀላ የሚቆርጥ ሰንሰለት፡፡

ሰነሰለቱን ሲቆርጥ አንገት እንዳይቀላ

ሊያዝ ይገባዋል በጥበብ በመላ፡፡

ጠንቅቆ ለማያቅ አያያዙን በደንብ

በተለይም ደግሞ ለሚባል ሰፊው ሕዝብ

የእወቀቱን ደረጃ ገምግሞ በማሰ

ነጻነት ይወሰን በሕጋዊ ገደብ፡፡

አለዚያ ያፈሳል የሰው ደም በከንቱ

አስተውሎ ሳያይ አዙሮ ባንገቱ

የነጻነቱን ሰይፍ ሲመዘው ካፎቱ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ፋነነ ማለት ሳይታዘዝ በፈቃዱ ዘመተ ማለት ሲሆን፣ ፋኖ ማለት ደግሞ በፈቃዱ የዘመተ አለቃ የሌለው ወዶ ዘማች ማለት ነው፡፡  ስለዚህም ፋኖ እና ቄሮ እንደ ዱባና ቅል እየቅልናቸው ማለት ነው፡፡  ለወገኑ ክብር /ለመሰዋት/ በራሱ አነሳሽነት የዘመተውን ጭምቱን ፋኖ፣ ተራግጦ ካልጠገበው ከውርጋጡ ቄሮ ጋር ማመሳሰል ፋኖን መዘለፍ ነው፡፡

ስላነበቡኝ አኮቴ (thanks)::  በሌላ ጦማር (article) እስከምንገናኝ ደህና ይሰንብቱ:: የጦቢያ አምላክ አብሔር (God) ይጠብቅወ::

መስፍን አረጋ ዘነገደ ኩሽ

የትብቱ ቀብር ደሴ ሳላይሽ::

mesfin.arega@gmail.com

LEAVE A REPLY