ብአዴን የሚባለው የፋሽስት ወያኔ ነውረኛ ድርጅት ሊድን የማይችል የሆዳም አማሮች፣ የአማራ ጥላቻ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ የሚሰማቸውና በአማራ ጥላቻ የናወዙ ከንቱዎች ስብስብ ነው። ብአዴን በእድሜ ዘመኑ አንድ ጊዜም ተሳስቶ ተግባሩና ሥራው ለአማራ ሕዝብ የሚበጅ ሆኖ አያውቅም። ብአዴን ሁል ጊዜ ምክትልነት ነባር ይዞታው ነው። ብአዴኖች የምክትልነት ረዥም ልምድ ስላላቸው ማንም ከላያቸው ቢጫን ምክትልነትን ኮርተው ይቀበሉታል። ብአዴኖች ምንም እንኳ ነባር ይዞታቸው የምክትልነት ማዕረግ ቢሆንም ስራቸው ግን የምክትልነት ሳይሆን የሻንጣ ተሸካሚነት ነው።
ብአዴን በታሪኩ ለጌቶቹ ያለውን ያህል ታማኝነትና ተቆርቋሪነት ለአማራ ሕዝብ ተሳስቶ እንኳ አንድም ቀን አሳይቶ አያውቅም። ብአዴን ለአማራ ሕዝብ ከሚገባው ቃል ኪዳን በላይ ሎሌ ሆኖ ታማኝ በመሆን ለጌቶቹ በየመድረኩ እየተገኘ መሃላ መፈጸምን ተልዕኮው ያደረገ ድርጅት ነው። ብአዴን ታድሻለሁ ቢልም ዛሬም ግን የአማራ ሕዝብ ካነሳቸው ጥያቄዎች ይልቅ የምክትልነት ነባር ይዞታውን ለማስጠበቅ ደፋ ቀና የሚልባቸው አጀንዳዎቹ ይበልጡበታል። ትናንትና ለፈጣሪያቸው ሕወሓት በታማኝነት ሎሌ ሆነው እንዳገለገሉ ሁሉ ዛሬም አዲስ ማተብ አጥልቀው በሌላ ምክትልነት ማዕረግ በሻንጣ ተሸካሚነት ተልዕኮ ለማገልገል ወደ ተግባር ከገቡ ውለው አድረዋል።
የብአዴን ባሕል ከአማራ ትግል ውስጥ መውጣት አለበት። የታላቁን የአማራ ሕዝብ ስምና ዝና አንግበው ደግመው ደጋግመው ሻንጣ ተሸካሚ በመሆን ሕዝቡንም የሻንጣ ተሸካሚነታቸው አካልና አምሳል ማድረጋቸው የራሳቸውን የታመመ የምክትልነት ጥማት ቅድሚያ በመስጠትት የአማራን ሕዝብ ክበር ዝቅ ማድረጋቸው ሊበቃ ይገባል።
ብአዴን በትግርኛ እያሰበ ብአዴን የሚል የትግርኛ ስም ካወጣለት ከመለስ ዜናዊ ድርጅት ሞግዚትነትና ከበረከት ሰምዖን ሎሌነት ተላቅቄያለሁ ቢልም ቅሉ አሁንም ግን ስለ አማራ የሚያስበው የበረከት ሰምዖንና የመለስ ዜናዊን ጥላ እየተከተለ ነው። ባለፈው ሳምንት መለስ ዜናዊ ያወጣልኝን ስሜን ልቀይር ነው ብሎ ሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቆ ነበር። በብአዴን ተስፋ የሚያደርጉ የአማራ «ምዕመናን» ብአዴን መዳን የሚችል መስሏቸው የድርጅቱን ስም የሚጀምረው «የአማራ ሕዝቦች» በሚለው ፈጽሞ መሆን እንደሌለበት፤ የድርጅቱ ስም መጀመር ያለበት «የአማራ ሕዝብ» በሚለው መሆን እንዳለበት በርካታ ሰው አስተያየት ሰጥቶ ነበር። መስሚያ የሌለው ብአዴን ግን አሁንም በመለስ ዜናዊና በበረከት ሰምዖን ጭንቅላት እያሰበት የተሰጠውን ሕዝባዊ አስተያየት አፈር ድሜ አብልቶ ሕዝብ ያልመረጣቸውን «የአማራ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» እና «የአማራ ክልል ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» ከሚሉት ስያሜዎች መካከል አንዱን በመምረጥ የድርጅቱ ስም እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል።
ብአዴን ከመለስ ዜናዊና በረከት ሰምዖን የወረሰው ሕዝቦች የሚለው ስያሜ ኢትዮጵያን አማራ «ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በመውረር የፈጠራት የተለያዩ አገራት ሕዝቦች እስር ቤት ናት» በሚል ዋለልኝ መኮነን የፈጠረው ትርክት ቅጥያ ነው። ኢትዮጵያ አገር ከሆነች ሕዝቧ ኢትዮጵያ ሕዝብ ይባላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው እየተባለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፋይ አካል የሆነው የአማራ ሕዝብ « የአማራ ሕዝቦች» የሚሆነው ብአዴንን በፈጠሩት ፈላስፎች በነመለስ ዜናዊና በበረከት ሰምዖን ሒሳብ ብቻ ነው። የአማራም ሕዝብ በሰጠው መልስ «ሕዝቦች ሳይሆን ሕዝብ ነን» ብሎ በግልፅ ነግሯቸው ነበር። እነሱ ግን አልሰሙትም! ሊሰሙትም አልፈለጉም! አይችሉምም! እነሱ በየጊዜው ጌታ የሚያደርጓቸው አለቆቻቸው ጉዳይ አስፈጻሚ እንጅ ባለጉዳይ አይደሉምና!
«የአማራ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» የሚለውን ስም የመረጡት ሕወሓት በፈጠረው የአማራ ክልል ውስጥ አሉ የተባሉትን ሌሎች ነገዶች ለማቀፍ ፈልገው ነው አሉ። አብዛኛው የብአዴን አመራሮች የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምሕራን ናቸው ይባላል። የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ስለነበሩ አንብበው ስለ ርዕዮተ ዓለምና ታሪክ ባያውቁ ቢያንስ የአማርኛ ሰዋሰው ያውቃሉ ብሎ መገመት ይቻላል። ብአዴኖች ግን ሆዳቸው እንጂ የጭንቅላታቸው ቁልፍ ዛሬም በበረከት ሰምዖን እጅ ስላለ በክልሉ ይኖራሉ የተባሉት ሌሎች ነገዶች በድርጅቱ ስያሜ ውስጥ መታቀፍ ካለባቸው አማራ የሚለው መውጣት ይኖርበታል እንጂ የአንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፋይ የሆነው አማራ «የአማራ ሕዝቦች» መባሉ የአማርኛ ሰዋሰወዊ ግድፈት እንደሆነ እንኳ መገንዘብ አልቻሉም።
ብአዴን የሚቀያይራቸው ጌቶች ጉዳይ አስፈጻሚና ሻንጣ ተሸካሚ እንጂ የአማራ ድርጅት ስላልሆነ በአማራጭነት ከቀረቡት ሁለት የመጨረሻ ስሞች መካከል ሁለተኛው «የአማራ ክልል ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» የሚለው ስም የአማራ ሕብዝ በተቂስ ወጥቶ ሲያቀርባቸው የከረማቸውን ጥያቄዎች የመስሚያ ጊዜ ስለሌላቸው ስያሜው ከአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ጋር እንደሚጣረስ እንኳ አንዳች ልብ አላሉትም። ለነገሩ በጽሕፈት ቤቱን ቅጥር ግቢ ውስጥ የትግራይ ወታደሮች ስናይፐር እየጠመዱ የአማራ ልጆችን እንዲጨፈጭፉበት የፈቀደ ድርጅት በየጊዜው ብቅ የሚሉ ጌቶች ሻንጣ ተሸካሚ ሊሆን እንደሆነ እንጂ የአማራ ሕዝብ አካል አይደለምና የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ባይሰማ አይፈረድበት።
የአማራ ሕዝብ ባካሄዳቸው ሰልፎች ሁሉ የአማራ ክልሉ ኢትዮጵያ እንደሆነች፤ ሕወሓት የፈጠረውን የአማራ ክልል አማራ እንደማይቀበል በሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ በየአደባባዩ አስተጋብቶታል። ብአዴን ግን ሻንጣ ተሸካሚ ስለሆነ የአማራ ክልል የሚለውን የጌቶቹን ሸቀጥ በአማራ ዘንድ ቅቡል ለማድረግ በፓርቲ ጥብቆነት አሰርቶ በአማራ ላይ ለማጥለው የድርጅቱ ስያሜ አድርጎ ሊጠቀምበት እያጎበኮበ ይገኛል።
እንግዲህ! አኩሪና የሺዎች ዓመታት ዝነኛ ታሪክ ያለው ኢትዮጵያዊው የአማራ ሕዝብ ስሙንና ዝናውን አንግበው በየጊዜው ለሚነሱ ጌቶች የምክትልነት ነባር ይዞታቸውን በማጽናት ሻንጣ ተሸከሚ በመሆን ሕዝባችንን እየደጋገሙ የሻንጣ ተሸካሚነታቸው አካልና አምሳል ማድረጋቸው የሕዝቡን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነውና የአማራ ሕዝብ ከማይድኑ ሻንጣ ተሸካሚ ብአዴኖች ቀንበር መላቀቅ አለበት።