ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደጻፍነው አዲስ አበባ ፊንፊኔ አይደለችም። ፊንፊኔ ወይንም ፍልውሃ አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬም ድረስ የምትገኝ አንድ ትንሽ መንደር እንጂ በሁለንተናዊ መልኩ ሰፊና ግዙፍ ከሆነችዋ አዲስ አበባ ጋር አንድ አይደለችም። እነኦቦ በቀለ ገርባ በዛሬው መግለጫቸው አዲስ አበባን ፊንፊኔ አድርገው ለማቅረብ ቢኖክሩም ያቀረቧቸውን መንደሮች ስም ዝርዝር ለሰማ ግን እነ ኦቦ በቀለ አዲስ አበባ ማለት ፊንፊኔ ማለት እንዳልሆነ ሳይታወቃቸው ነግረውናል።
እነ ኦቦ በቀለ የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተው ባወጡት በዛሬው መግለጫቸው፤
«ዛሬ ፊንፊፌ ከተማ የምትገኝበት ስፍራ የኤካ፣ የጉለሌና የገላን የኦሮሞ ጎሳዎች የዕምነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል እንደነበረች ማንም የሚክደው አይደለም። ነገር ግን እነዚህ ጎሳዎች የመኖሪያ፣ የእርሻና የግጦሽ መሬታቸውን በኃይል ተነጥቀው እንዲጠፉ ተደርገዋል» ሲሉ ተናግረዋል።
እነ ኦቦ በቀለ ገርባ ይህንን የውሸት ታሪክ የተማሩት ከኦነግ የፕሮፓጋንዳ ጸሐፊዎች ነው። ኦቦ በቀለ እንደ ዩኒቨርሲቲ መምህር ይህ የኦነግ ፕሮፓጋንዳ እውነት ስለመሆኑ መጽሐፍትን አገላብጠው ወይንም ምርምር ሰርተው አላጣሩትም። ጥናትና ምርምር ሳያካሂዱ ተረት እየደገሙ ትውልድ ሊያሳስቱበት ይችላሉ ይሆናል፤ የአገራችንን ታሪክ ላነበብንና ለመረመርን ሰዎች ግን ይህ የነ ኦቦ በቀለ ገርባ የውሸት ታሪክ አታውቁም ደንቆሮ ናችሁ ብሎ ከመስደብ አይተናነስምና ዝም ብለን ልናየው አንሻም። ስለሆነም የመረመርነውን ዶሴ ልንመዝ ተገደናል። ዶሴው ሲወጣ እነ ኦቦ በቀለ ገርባ የሚነግሩን የፈጠራ ታሪክ ቅቡልነት እስከምን ድረስ እንደሆነ እንደሚከተለው ይታያል።
የዐፄ ዳዊት ከተማ በረራ በግራኝ ወረራ ከወደመች ከሁለት መቶ አመታት በኋላ ሸዋን ጎብኝተው ታሪክ ጽፈው ካለፉ የውጭ አገር ሰዎች መካከል ጀርመናዊው ቄስ Johann Ludwig Krapf ቀዳሚው ነው። ቄስ Johann Krapf እ.ኤ.አ. በ1840ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ሸዋን የጎበኘ ሲሆን ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ጋር በተለያዩ ዘመቻዎች አብሮ በመጓዝ የተለያዩ የሸዋን አካባቢዎች ጎብኝቷል። Krapf እ.ኤ.አ. በ1840 ዓ.ም. ከንጉሡ ጋር በእግሩ ረግጦ ካለፈባቸው የሸዋ አካባቢዎች መካከል የዛሬው የአዲስ አበባ አካባቢ አንዱ ነው። Krapf ይህን የአዲስ አበባ አካባቢ በ1840ዎቹ ከጎበኘ በኋላ እ.አ.አ. በ1860 ዓ.ም. ከጀርመን ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ በታተመው «Travels, researches, and missionary labours, during an eighteen years’ residence in Eastern Africa» መጽሐፉ ገጽ 25 ላይ ዛሬ አዲስ አበባ በተባለው አካባቢ እነ ማን ይኖሩበት እንደነበር እንዲህ ብሏል፤
«The first campaign which I thus made in January and February 1840 led me into the territories of the tribes of the Abeju, Woberi, Gelan, Dembichu, Finfini, and of the Mulofalada, Metta Robi, Wogidi, Metta and Kuttai, all Gallas»
ይህ የ Krapf ጽሑፍ ወደ አማርኛ ሲመለስ፤ «በጥር እና የካቲት 1833 ዓ.ም. የጀመርነው የመጀመሪያው ዘመቻ የአብቹ፣ የገላን፣ የወበሪ፣ የደምብቹ፣ የፊንፊኔ፣ የሞሎፋላዳ፣ የሜታ ሮቢ፣ የወግዲ፣ የቤኤና የጉታይ ኦሮሞ ጎሳዎች በሚኖሩበት ወሰደኝን» እንደማለት ነው።
ይህ የKrapf ምስክርነት የሚነግረን ፊንፊኔ፣ የካ፣ ጉለሌና ገላን የተባሉት ቦታዎች በየራሳቸው የኦሮሞ ጎሳዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች እንደሆኑ እንጂ እነ በቀለ ገርባ ሊነግሩን እንደፈለጉት ፊንፊኔ የካ፣ ጉለሌና ገላን የተባሉ የኦሮሞ ጎሳዎች የመኖሪያ፣ የእርሻና የግጦሽ መሬት እንደነበረች አይደለም። በሌላ አነጋገር ፊንፊኔ ልክ እንደ የካ፣ ገላንና ጉለሌ ራሷን የቻለች መንደር፤ የየካ፣ የገላንና የጉለሌ ጎሳዎች አካል ያልሆነ የራሷ ጎሳ ይኖርባት የነበረች እንጂ የየካ፣ የጉለሌና የገላን ጎሳዎች የመኖሪያ፣ የእርሻና የግጦሽ ቦታ አልነበችም። ለዚህም ነበር አዲስ አበባ ማለት ፊንፊኔ ማለት አይደለም ስንል የከረምነው። አዲስ አበባ ፊንፊኔ/ፍል ውሃ ፣ ገላን፣ የካ፣ ጉለሌ፣ አቧሬ፣ ግንፍሌ፣ ወዘተ የሚባሉ መንደሮችን በውስጧ የያዘች ከተማ ናት እንጂ በፊንፊኔ ልክ ተሰፍታ በፍል ውሃ ልክ የታጠረች አንድ ትንሽ መንደር አይደለችም። በKrapf ምስክርነት መሠረት አዲስ አበባን ፊንፊኔ ብሎ መጥራት አዲስ አባን ገላን ብሎ እንደመጥራት፤ ከጉለሌ ጋር እኩል እንደማድረግና ከየካ ጋር እንደማስተካከል ነው። ለዚያም ነው አዲስ አበባን ፊንፊኔ ብሎ መጥራቱ ምንም አይነት የታሪክ ተጨባጭነት የማይኖረው።
Krapf አዲስ አበባን አካባቢ በጎበኘበት ወቅት በአካባቢው ፊንፊኔ፣ የካ፣ ጉለሌና ገላን የሚባሉ መንደሮች እንደነበሩ ብቻ ጠቅሶ አያበቃም። በፊንፊኔ፣ በየካ፣ በጉለሌና በገላ የሚኖሩት የኦሮሞ ጎሳዎች የቱለማ ኦሮሞዎች እንደሆኑ ይነግረንና እነዚህ ኦሮሞዎች ወደነዚህ ቦታዎች መቼ እንደሰፈሩም ጭምር በገጽ 234 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፤
<<…Three sons were called Tulema, Kereyu, and Mechaa; and hence the Tribes of these names— that when they thought they were strong enough, they began to fight with the Abyssinians, and frequently vanquished them, particularly on one occasion near the river Gala, and hence they have been called Gallas to the present day. When Mahomed Gragn desolated Shoa and Gurague, the Gallas entered and took possession of many fine places>>
ይህ ታሪክ ባጭሩ ወደ አማርኛ ሲመለስ፤ «የቱለማ፣ የከረዩና የሜጫ ኦሮሞዎች የጉራጌና የሸዋን አካባቢዎች ኗሪዎች ግራኝ ሲያፈናቅላቸው ኦሮሞዎች ወረሩና ለምለሙን ምድር የራሳቸው አደረጉት» እንደ ማለት ነው።
ለዚህም ነበር ከዚህኛው ጽሑፍ ቀደም ሲል በጻፍሁትና ለጸጋዬ አራርሳ በሰጠሁት ምላሽ ላይ የዐፄ ዳዊትንና የዐፄ ልብነ ድንግልን ልጆች ያያታቸው ዋና ከተማ ለነበረችው የቀድሞዋ በረራ የኋላዋ እንጦጦና የዛሬዋ አዲስ አበባ ዙሪያ መጤና የዋና ከተማችን እንግዳ አድርጎ ማቅረቡ ነውረኛነት ነው ያልሁት። በግራኝ ወረራ ምክንያት የሞቱና ከርስታቸው የተፈናቀሉትን ለአዲስ አበባ እንግዳና መጤ አድርጎ በማቅረብ ኋላ የመጣውን ኦሮሞን ብቸኛ የአዲስ አበባ ባለቤት አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ነውረኛነትን ከማሳየት ባለፈ ታሪካዊ እውነታውን አይለውጠውም።
ሌላው እነ በቀለ ገርባ በመግለጫቸው ያነሱት አስቂኝ ነገር ስለ የካ፣ ጉለሌና ገላን ኦሮሞዎች በኃይል ተነቅለው እንዲጠፉ ተደርገዋል የሚለው የመነቸከ ተረት ተረት ነው። አዲስ አበባ እንደገና ስትመሰረት የተመሰረተችው ገላን፣ የካና ጉለሌ ላይ አይደለም። አዲስ አበባ እንደገና የተቆረቆረችው ፍል ውሃ አካባቢ የተገኘውን በግራኝ ዘመን የፈረሰ የማርያም ቤተ ክርስቲያን መሠረት አድርጎ የተሰራውን የንጉሠ ነገሥቱን ቤተ መንግሥት [የዳግማዊ ምኒልክን ቤተ መንግሥት] ማዕከል በማድረግ ነው። ከዚህ መሠረትና አንድ ሺህ ከማይሞሉ ቤቶች ተነስታ ዛሬ አዲስ አበባ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የግል ይዞታ የሆኑ ቤቶችን በማቀፍ በሁለንተናዊ መልኩ የሰፋችና የገዘፈች አለማቀፍ ከተማ ሆናለች።
እነ ኦቦ በቀለ አዲስ አበባ ስትቆረቆር የገላን፣ የካና የጉለሌ ጎሳዎች በኃይል ተነቅለው ነው ያሉት የፈጠራ ታሪክ ነው። እንኳን ያኔ ዛሬም የባለርስቶቹ ዘሮች ከልዩ ልዩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተዋልደውና በዝተው ባያቶቻቸው ርስት ላይና በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ይኖራሉ። ከአዲስ አበቤው ጋር ተዋልደው፣ እንደ ሌላው ራሳቸውን አቅልጠው አዲስ አበቤ ስለሆኑ ዛሬ ላይ ከብት የሚያስግጡና እርሻ የሚያርሱ ግን አይደሉም። ከብት ማጋጥንና እርሻ ማረስን እንደ ሥራ ምርጫ እንኳን የዛሬዎቹ ልጆቻቸው የያኔዎቹ አያቶቻቸውም ትተውት ከተሜ ሆነው ነበር ይኖሩ የነበረው።
ለዚህ አንድ ምሳሌ የጉለሌውን ባላባት የደጃዝማች አበቤ ቱፋ አባት ቱፋ ሙናን መጥቀስ ይቻላል። የልጃቸው የአበቤ ቱፋ ቤት ዛሬም እዚያው ጉለሌ ውስጥ ይገኛል። እነ ኦቦ በቀለ እንደተነቀሉ የሚነግሩን አበቤ ቱፋና መሰል የጉለሌው ባላባቶች ከነራስ ጎበና ጋር አገር ያቀኑ ናቸው። ኦነጋውያን ግን መሬቱን እንጂ ሰዎቹን ስለማይፈልጓቸው እነዚህ አገር አቅኝዎች «ጎበናዎች» እያሉ በማሸማቀቅ ሲያሳድዷቸው ነው የኖሩት።
የጉለሌው ባላባት ደጃዝማች አበቤ ቱፋ እነ በቀለ ገርባ እንዳሉን እንኳን ከቦታቸው ሊጠፉና ሊነቀሉ ይቅርና አበቤ ቱፋ ካለፉ ከዘመናት በኋላ የተፈጠረው ድምጻዊ ካሳ ተሰማ፤
እነ አበቤ ቱፋ እንደገሩት ፈረስ፣
ወርዶፋ ጨንገሬ እንደገራው ፈረስ፣
ጡቷ ደንገላሳ ይላል መለስ ቀለስ፤
ብሎ ዘፍኖላቸው ከጉለሌ አልፎ ዝናቸውን በመላ አዲስ አበባና በመላ ኢትዮጵያ ተክሎላቸዋል። ደጃች አበቤ ጽኑ ክርስቲያን ነበሩ። ሱሉልታ ውስጥ የሚገኙ የጥንት ቤተ ክርስቲያኖችን ያሰሩት እሳቸው ናቸው። ከፍ ሲል እንዳመለከትሁት ቅርሳቸው ግን ከሱሉልታ ቤተ ክርስቲያኖች አልፎ ዛሬም ድረስ ጉለሌ በሚገኘው ግቢያቸው ውስጥ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ወልደው ተዋልደው አዲስ አበቤ ሆነው ይኖሩበታል።
ወርዶፋ ጨንገሬም ሌላው አዲስ አበባ ውስጥ ፈረስ የሚያስጋልብ ርስት የነበራቸው የአካባቢው ባላባት ነበሩ። አበሻን የናቀን አንድ ትቢተኛ ፈረንጅ በጦርና ጋሻ ፍልሚያ ተዋግተው ድል ካደረጉ በኋላ በዐፄ ምኒልክ ፊት ቀርበው፤
ዘራፍ አካኪ ዘራፍ፣
ከጥንት እስከ ዛሬ፣
ጀግና ላልነጠፈባት ሀገሬ፣
ዛሬም አሸንፏል ወርዶፋ ጨንገሬ፤
ዘራፍ ዘራፍ አካኪ ዘራፍ.. .
እያሉ ፎክረው ለሰሩት የጀግንነት ተግባራቸው ንጉሠ-ነገሥቱ ካመሰገኗቸው በኋላ የሚፈልጉትን ቢጠይቁ እንደሚደረግላቸው ቃል ገብተውላቸው ጃን ሜዳ አካባቢ ያለውን ሰፈር ሰፈር ልባቸው የፈቀደውን ያህል በፈረሳቸው ጋልበው ጠይቀው የተሰጣቸው ባላባት ናቸው። የሳቸው ዘሮችም ዛሬም እዚያው ይኖራሉ።
የሱሉልታ ገዢ የነበሩት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አጎትና የልዑል ራስ መኮነን ወንድም ደጃዝማች ኃይሌ ጉዲሳም ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት የቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ባለ ርስት ናቸው። የደጃች ኃይሌ አባት ኦቦ ጉዲሳ ቦጃ የአካባቢው ታዋቂ ዳኛ ነበሩ። ይህንን የሚያውቁት የሱሉልታ ኦሮሞዎች ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲኔግዴ ገዢ ተደርገው ቢሾሙላቸው «የጌታችንን ልጅ ይሹሙልን» ብለው ለዳግማዊ ምኒልክ አቤት በማለታቸው አባ መላን አንስተው ደጃች ኃይሌ ጉዲሳን ገዢ አድርገው ሾመውላቸዋል። የፊንፊኔውን የደጃች ኃይሌ ርስት ወራሽ የሆኑት የወንድማቸው ልጅ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ የግል ርስታቸው በሆነው ቦታ ላይ ከአባታቸው በርስትነት ያገኝትን በመጨመር ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትን አሰርተው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በማድረግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በርስትነት ማስረከባቸውን ባለፈው ከጻፍነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ጋር ባያያዝነው በንጉሠ ነገሥቱ በራሳቸው የተፈረመ የንብረት ማስረከቢያ ዶሴ ላይ አሳይተናል።
እንግዲህ! ፊንፊኔ፣ የካ፣ ጉለሌና ገላን እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የተለያዩ መንደሮች እንጂ አዲስ አበባና ፊንፌኔ አንድ አለመሆናቸውን፤ የየካ፣ ጉለሌና ገላን ጎሳዎች ልጆችም ዛሬም ድረስ አዲስ አበቤ ሆነው ከቅድሚያ አያቶቻቸው ከወረሱት ርስት መካከል ከፊሉን ሸጠው፤ አብዛኛውን ደግሞ እን ኦነግ በዋናነት ባወጡት የደርግ የከተማና ትርፍ ቤት ደርግ ተወርሶባቸው፤ በተረፈው ርስታቸው ላይ ግን አሁንም ድረስ ስም የሚያስጠሩ ልጆች በቦታው ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ጉለሌ በሚገኘው የባላባቱ የአበቤ ቱፋ ቤት በመሄድ ዘሮቻቸውን አግኝቶ «በኃይል ተነጥቀው እንዲጠፉ ተደርገዋል» የሚለውን የኦነግ ተረት የፈጠራ ወሬነት ማረጋገጥ ይቻላል።
በመጨረሻ «ሕገ መንግሥት» ለተባለው የወያኔ ፕሮግራም ጠበቃ ሆነን ካልቆምን ሞተን እንገኛለን ላሉን ለነ ኦቦ በቀለ ሁለት ጥያቄዎች ማቅረብ እፈልጋለሁ። እንደሚታወቀው «ሕገ መንግሥት» ተብዮው ሲረቀቅ አማራ አልተሳተፈበትም። አክብሩ እያላችሁን ያላችሁት እኛ ያልተሳተፍንበትን የቅሚያ ደንብ ነው። እኛ አማሮች «ሕገ መንግሥት» የተባለውን ከማንፈልገባቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ እኛ ተወክለንበት የተዘጋጀ ባለመሆኑ ስለማይመለከተን ነው። እኔ ግን እንደ አንድ አማራ ወንድሜ የምለው የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ሳይሳተፍ በተረቀቀና በጸደቀ ሕገ መንግሥት ተገዛ ብዬ የምጠይቅበት ህሊና የለኝም! ኦሮሞን ባልተሳተፈበት ሕገ መንግሥት እንዲገዛና ሕጉን እንዲያከብር መጠየቅ በአፓርታይድ ሕግ፤ በቅኝ ግዛት ደንብ ተገዛ ብሎ እንደመፍረስ ያለ ደመኛነት ነው። አማራንም በተመሳሳይ መልኩ ባልተሳተፈበትና ባላጸደቀው ሕገ መንግሥት ተገዛ ብሎ መግለጫ እስከማውጣት ድረስ የሚያደርስ ስብዕና በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ከማለት የተለየ ነውረኛነት አይደለም!
የሆነው ሆኖ ነገሮችን እንዳሉ እንውሰድና ሕገ መንግሥት የተባለውን የወያኔ ፕሮግራም ካላከበራችሁ በሕልውናችን እንደመጣችሁ እንቆጥረዋለን ያሉንን እነ ኦቦ በቀለ ገርባን የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች መጠየቅ ወደድሁ፤
አንደኛ፡ በዶክተር ነጋሶ ፊት አውራሪነት ተዘጋጅቶ የጸደቀው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49(1) ላይ «የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው» ይላል። ሆኖም ግን መግለጫ ያወጡት አምስቱም የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕሰ ከተማችንን አዲስ አበባ ብለው ጠርተው አያውቁም። ጤና ይስጥልኝ እነ ኦቦ በቀለ?! የፌዴራል መንግሥቱን ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ብሎ አለመጥራት ካላካበርነውና ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን የምትሉትን ሕገ መንግሥት መጣስ አይደለም? ነው ይህ ሕገ መንግሥት እንድናከበር የተፈረደብን እኛ ብቻ ነን?
ሁለተኛ፡ ካላከበርነውና ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን የምትሉት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንቀጽ 49(5) «አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል ትገኛለች» ይላል እንጂ «የኦሮምያ ክልል» አካል ናት አይልም። ይህ ከሆነ እናንተ መግለጫ ያወጣችሁት አምስቱ የኦሮሞ ፓርቲዎች «ፊንፊኔ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም የኦሮምያ አካልና የኦሮሞ ሕዝብ መኖሪያ ናት» ያላችሁት የሕገ መንግሥት ጥሰት ነው። እናንተ ራሳችሁ ካላከበርነውና ካላስከበርነው የምትሉትን ሕገ መንግሥት አናት እያፈረሳችሁ ሌላውን በአፍራሽነት የመክሰስ የሞራል ልዕልና እንዴት ሊኖራችሁ ይችላል? እስቲ መልሱልን!