/መላኩ አላምረው/
…
በጉባኤው ዋዜማ ስለብአዴንን ያለኝ የመጨረሻ ግላዊ ሐሳብ/ምክር/ማስገንዘቢያ ይህ ነው፦
…
ባሕር ዳር በለውጥ ወይም በነውጥ ዋዜማ ላይ ነች። ዛሬ ከሰዓት 12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ይከፈታል።
አንድ ነገር ተስፋ አደርጋለሁ። ብአዴን ከስምና ከአርማ ለውጥ ባሻገር መሠረታዊ ውላጤ /Transformation ያደርጋል። ሲሆን እስከ 85% ቢያንስ ግን ከ50% በላይ የአመራር ለውጥ ያደርጋል። በምትኩም ለውጡን የሚሸከሙ ኃይሎችን ከራሱ አባላትም ከውጭም ያስገባል። የአመራር ምልመላ መስፈርቱንም ከተለምዷዊ “የአባልነት ግዴታን መውጣትና የድርጅት መርህን ማክበር” ወደ “አማራ ሆኖ ለአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ ምግባር ብቁ ሆኖ መቆም” ወደሚል ይቀይረዋል። ይህ ሲሆን በአባላቱ ሳይታጠር አመራ የሆነን ሁሉ እይታው ውስጥ ያስገባል። ይህን ካደረገ በአማራ ሰማይ ስር ከበቂ በላይ ብቁ አመራር አያጣም። ጠንካሮችን በማስገባት ይለወጣል። ይህ ተስፋችን ነው።
.
ይህ ካልሆነ… ብአዴን አንድ ሁለት ሰዎችን ለይስሙላና ለማስመሰል ቀይሮና ተጠጋግኖ ከቀጠለ… ከአባላቱ ውጭ ማንንም አልፈልግም ካለ… በተለይም በሕዝብ ጠልነታቸው በሕዝቡ የተጠሉትን ሸፋፍኖ ይዞ የሚቀጥል ከሆነ… ከአማራ ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጣላል። ትንሽ ተስፋ ያለው ሕዝብ ተስፋውን ሟጦ ይጥላል። ግልጽ ተቃውሞ ይጀመራል። በተለይ በየወረዳው ያለው የቆሰለ ሕዝብ አመራሮችን በጉልበት ማባረር ይጀምራል። ብአዴንም ከአፈርሁ አይመልሰኝ ብሎ ድብድብ ውስጥ ይገባል። ክልሉ ለውጥ ሳይሆን ነውጥ ይከተለዋል። ይህ ሟርት አይደለም። መጥፎ ምኞትም አይደለም። ክፉ ማሰበም አይደለም። የብአዴን አለመለወጥ የሚያመጣው ክልላዊም ሆነ ሀገራዊ ጥፋት ግልጽ ነው። ይህን ለመተንበይ ልሂቅነት አይጠይቅም። አሁን በየወረዳው ያለውን ውጥረት ማየት በቂ ነው።
አንዳንድ ወረዳዎች ሙሉ የብአዴን አመራሮችን በጉልበት አስወግደዋል። (መርጦላ ማርያምን ይጠቅሷል።) የሚከብደው በጉልበት ጠርጎ ማስወገዱ አይደለም። በብዙ ወረዳዎች አመራሩ በየቡድን ሆኖና ሕዝቡን ከፋፍሎ “እኔ ነኝ እኔ ነኝ የምቀጥለው” አይነት ፉክክርና ጠብ ጀምሯል። አመራሮች የየራሳቸውን ደጋፊ የማሰባሰብ ዘመቻ ላይ ናቸው። ሕዝቡም ተከፋፍሎ የየቡድኑ ድጋፍ ሰጭ መሆን ጀምሯል። ይህ የአንድ ወይም የተወሰኑ ወረዳዎች ብቻ እውነታ ቢሆን ባልገረመ። በግልጽ ታየም አልታየም። የአብዛኞቹ እውነታ ነው። ይህ ነው ነገን አስቀያሚ የሚያደርገው። ብአዴን በክልል ደረጃ ጥገናዊ ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥ አምጥቶ ከላይ እስከታች ያሉ ብቁ ካለመሆንም በላይ በተራ ውንብድና ላይ ያሉ አመራሮችን ጠርጎ ካላስወገደ በወረዳ ደረጃ የሚደረግ መቧደን ጥፋትን ብቻ እንጅ ሌላ ለውጥ አያመጣም። የብአዴን ከላይ ከላይ ከአናቱ አለመለወጥ ብዙ ጥፋትን፣ ሁከትንና ነውጥን ያመጣል የምንለው ዝም ብለን አይደለም። በተግባር ከምናየው ወደዚያ ሊያመራ የሚችል ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት እንጅ። በግምት ሳይሆን በተጨባጭ መረጃ።
.
እናም እላለሁ።
1ኛ. ብአዴን ለዚህ የተገፋ ሕዝብ መከራ ማቆም ሲል ይለወጥ። ጥገናዊ ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥ ይለወጥ። ያለበለዚያ የሚከተለው ድጋፍ ሳይሆን የተቃውሞ ነውጥ ነው።
2ኛ. በተለይ በየወረዳው ያለው ሕዝብ በትዕግስት መጠበቅ አለበት። አመራሮች ለራሳቸው ሥልጣንና ጥቅም ማቆያ ብዙ ስልት ሊቀይሱ ይችላሉ። የየራሳቸውን ደጋፊ ለማሰባሰብ መጣራቸውም አይቀርም። ይህ ብዙ የሚገርም አይደለም። አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ሁኑ። ብአዴን በትክክል ሕዝባዊ ሆኖ ከተለወጠ ማንም በመሠረተው የቡድን ድጋፍ አይቀጥልም። በትክክለኛ የአመራር ብቃትና በንፁህ ሰብዕና የተገነባና ሕዝቡ ያለ ተቃውሞ የሚቀበለው መሪ ብቻ ይቀጥላል። ወረዳ ላይ መቧደኑም በሐሜትና ንትርክ መጠመዱም ከንቱ ልፋት ነው። ብአዴን በጠቅላላ አማራ ሆኖ ካልተለወጠ ከአማራ ይወገዳል። ያን ጊዜ የቡድን ድጋፍ ማንንም ከመወገድ አያስጥልም። ዝም ብሎ በማይሆን ነገር ጊዜ ማጥፋትም ሆነ እርስ በርስ በሃሜትና በተራ አተካራ መጠመድ ትርጉም የለውም የምለው ለዚህ ነው።
3ኛ. ብአዴን በጉባኤው ላይ ሕዝቡ የሚቀበለውን የአመራር ለውጥ አመጣ ማለትም በአንድ ጀምበር ከክልል እስከወረዳ ያለውን የአመራር ችግር አሰተካክሎና ደካሞችን ባንዴ ጠርጎ አስወግዶ ያስተካክላል ማለት አይደለም። ከላይ ያለው ለውጥ ካማረ ለታችኛው መለወጥ ቅድመ ሁኔታ ነው የሚሆነው። ነገር ግን ለውጡ በአንድ ጀምበር አይሆንም ማለትም በተለመደው መንቀራፈፍ ይቀጥላል ማለት አይደለም። በጣም ሳይዘገይ በተቻለ ፍጥነት ለውጡ በተጠና መልኩ ይወርዳል። ሁሉም ግን ከሕዝቡ ጋር በመመካከርና በመተማመን መሆን አለበት።
4ኛ. አሁን ከክልል ጀምሮ እስከወረዳ ለለውጡ ሲባል ከአመራርነት የሚገለሉ ቢኖሩ… እነርሱን እንደሕዝብ ጠላት ማየት የለብንም። በመሠረቱ አንድ ሰው ከአመራርነት የሚወገደው መጥፎና ፍጹም የማይረባ ስለሆነ ብቻ አይደለም። ጎበዝ ሆኖም በንጽጽር እይታ ሌላ ከእርሱ የተሻለ ሰው ካለ ለተሻለው ቦታ መልቀቅ ስላለበት ይቀየራል። ስለዚህ ከአመራርነት ለሚወርዱት መጥፎ እይታ መኖር የለበትም። በቆዩበት ጊዜ ይብዛም ይነስም ለሕዝብ ሠርተዋል። በቀጣይም ለውለታቸው ተመስግነው ያጠፉት ካለ አርመው የበደሉት ካለ ክሰውና ከሕዝቡ ጋር ተስማንምምተው አገልግሎታቸውን ይቀጥላሉ እንጅ ከአመራርነት ተቀየሩ ማለት ከሕዝቡ ወይም ከሥርዓቱ ተለዩ ማለት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፤ ከሆነም አይጠቅምም።
5ኛ. ለተሻለ ለውጥ ሲባል በየደረጃው ከክልል እስከ ወረዳ ከአመራርነት የምትወርዱ ወይም ወደ ሌላ ኃላፊነት የምትዘዋወሩ አመራሮችም ለውጡን በፀጋ ተቀብሎ ሕዝባዊ ወገንተኝነትን ከመቀጠል የተሻለ ምርጫ እንደሌላችሁ ማወቅ አለባችሁ። በክብር መሸኘትም መልካም ነው። እናንተም የደከማችሁት ለተሻለ ለውጥ ነው ከተባለ አሁን ለዚሁ ያላችሁን ቁርጠኝነት አሳዩ። ለውጥን ማምጣት ማለት ሥልጣን ላይ ሆኖ ብቻ ሳይሆን ሥልጣን ለቆም መሆኑን የምታሳዩበት ወርቃማ አጋጣሚ ላይ ናችሁ። በጨዋ ደንብ ሽግግሩን ተቀበሉና በክብር ተሸኙ። ይህ ካልሆነ ተቃራኒው ይሆን ዘንድ ግድ ይላል።