Thursday, November 21, 2024
በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትና በሌሎች ግለሰቦች ተወስዷል የተባለ 130 ሚሊዮን ብር ታገደ

በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትና በሌሎች ግለሰቦች ተወስዷል የተባለ 130 ሚሊዮን ብር ታገደ

የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ

‹‹የዕርቅና የሰላም አባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይድረሱልኝ››

አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ)

ለሶማሌ ክልል በድጎማ ከተመደበ በጀት ላይ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድና በሌሎች ግለሰቦች መወሰዱን ጠቅሶ፣ ገንዘቡ እንዳይንቀሳቀስ ፖሊስ አሳገደ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተለያዩ የምርመራ መዝገቦች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ባቀረበው ማመልከቻ፣

የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) እና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥ የነበሩት አቶ አብዱራህማን አብዱላሂን ጨምሮ፣

በ11 ሰዎች ለግል ጥቅም ተወስዷል ያለውን በአጠቃላይ 132.2 ሚሊዮን ብር እንዲታገድ ጠይቋል፡፡

የተሻሻለውን የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ (8) በመተላለፍ የተፈጸመና የተጠቀሰውን ያህል የብር መጠን ያለው ጉዳት፣

በመንግሥት ላይ የደረሰ መሆኑን በማስረዳት ገንዘቡ እንዲታገድ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተጠቀሰው ገንዘብ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ እንዳይንቀሳቀስና ተጠብቆ እንዲቆይ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎች ባንኮችም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረቡት አቶ አብዲ መሐመድ፣ የክልሉ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ራህማ መሐመድ፣

የዳያስፖራ ተወካይ አቶ አብዱራህማን ሳኒና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ፈርሃን ጣሂር ላይ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ተጠይቆባቸው አሥር ቀናት ተፈቅዷል፡፡

በቋንቋቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መነጋገር መከልከላቸውን፣ የፀሐይ ብርሃን በማያገኙበት ሁኔታ መታሰራቸውን፣

ሕክምና አለማግኘታቸውንና ፍርድ ቤት ለሦስት ጊዜያት ያስተላለፈው ትዕዛዝ ተፈጻሚ እየተደረገ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ አብዲ፣

በተለያዩ ግለሰቦች የሚደርስባቸውን ጫና መንግሥት እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤትም ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ከማመልከታቸውም በተጨማሪ፣

‹‹የዕርቅና የሰላም አባት ዶ/ር ዓብይ አህመድ እንዲደርሱልኝ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ተጠርጣሪው ለፍርድ ቤቱ የተናገሩትና ያመለከቱት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት በተፈቀደለት 14 ቀናት ውስጥ የሠራውን ካስረዳ በኋላ ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ የሠራውን እንዳስረዳው፣ የ41 ምስክሮችን ቃል ተቀብሏል፡፡

ከሐምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በጅግጅጋ ከተማና አካባቢው በሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያስረዳ ሰነድ ማሳሰቡን፣

የተዘረፉና ወደ ጎረቤት አገር የተወሰዱ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ማስመለሱን፣

ከልማት ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት ስለተዘረፉ የተለያዩ ነገሮች የሚያስረዳ ሰነድ መሰብሰቡን አስረድቷል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ የተደራጀውና ‹‹ሄጎ›› በመባል በሚጠራው የጥፋት ቡድን የተገደሉ 18 ሰዎች አስከሬን ምርመራና የ438 ግለሰቦች ከባድና ቀልል የአካል ጉዳት ምርመራ ውጤት ሰነድ መሰብሰቡን፣

ወንጀል የተፈጸመባቸው በርካታ የጦር መሣሪያዎችና ከመንግሥትና ከግለሰብ የተዘረፈ በርካታ ገንዘብ መያዙን፣ በጥቃት ቡድኑ የተደፈሩ በርካታ ሴቶችና ሕፃናት የምርመራ ውጤት የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ፈርሃን ጣሂር የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተውና ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ባደራጁት ‹‹ሄጎ›› ከሚባለው ቡድን ጋር አብረው ዘረፋ ላይ መሰማራታቸውን፣

በመኪና እየተንቀሳቀሱ ነዋሪዎችን በዘርና በሃይማኖት በመለየት ጥቃት እንዲደርስባቸው፣ ተቋማት እንዲዘረፉና እንዲቃጠሉ በማድረግ፣

በእስር ላይ የነበሩ የተለያዩ የብሔር ተወላጆችን ወዳልታወቀ ቦታ በማስወሰድ እንዳስረሸኗቸው ማስረጃ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ መከላከያ ክልሉን እንደወረረ በመንገር ‹‹ሄጎ›› በሚል  ስያሜ ያደራጁት ቡድን ዕርምጃ እንዲወስድ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የሞት፣ የአካል ማጉደልና የንብረት ውድመት እንዳደረሱ አስታውቋል፡፡

ከ60 በላይ የሚሆኑ ግብረ አበሮችን የመያዝ፣ በጅምላ ተጨፍጭፈው በአንድ ጉድጓድ የተቀበሩ ዜጎችን አስከሬን የማውጣት፣

የመለየትና የማስመርመር፣ ቀሪ የምስክሮችን ቃል የመቀበል፣ የተደፈሩ ሴቶችና ሕፃናትን የምስክርነት ቃል የመቀበል፣ የተሸሸጉ የጦር መሣሪያዎችን አፈላልጎ የማግኘት፣

ለወንጀሉ መፈጸሚያ ከተሰጡ (ከተከፋፈሉ) ሞባይሎች የተገኘን የምርመራ ውጤት የመቀበልና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እንደሚቀረው መርማሪ ቡድኑ አስረድቶ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለምን በተሰጠው ጊዜ ምርመራውን እንዳልጨረሰ መርማሪ ቡድኑን ሲጠይቀው፣

ወንጀሉ ውስብስብ ከመሆኑም በተጨማሪ ፈጻሚዎቹ ወደ ጎረቤት አገር ሸሽተዋል በማለት ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር አስረድቷል፡፡

ሰነዶችን ማስተርጎም እንደሚቀረውም አክሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ክርክር እንዳስረዱት፣

መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እያቀረበ የሚገኘው የምርመራ ሥራ ተመሳሳይ ነው፡፡

የምስክሮችን ቁጥር ጠቅሶ 41 ምስክሮች ቃል እንደተቀበለ ቢናገርም፣ ምን ያህል ምስክር እንደቀረው ግልጽ አላደረገም፡፡

የሚፈልጋቸው ግብረ አበሮች እንዳሉ እንጂ ስንት እንደሚሆኑም አልገለጸም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የትርጉም ቤቶች ስላሉ፣ ማስተርጎም እንደቀረው የሚገልጸው አሳማኝ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የተጠርጣሪዎቹ ኃላፊነትና የፖለቲካ ሹመታቸው የተለያየ በመሆኑ፣ የሥራ ኃላፊነታቸውም ስለማይገናኝ የምርመራ መዝገባቸው ተለይቶ መቅረብ እንዳለበት ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡

በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው 14 ቀናት ሊፈቀድለት እንደማይገባና የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት መከበር እንዳለበት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አቶ አብዲ እንዲናገሩ ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እንዳስረዱት፣ ፍርድ ቤቱ ሕክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ ቢሰጥም አልተፈጸመላቸውም፡፡

ጨጓራና የደም ግፊት እየታመሙ ቢሆንም፣ በታሠሩበት ቦታ ቀርበው የሚመረምሯቸው ነርሶች እንጂ ዶክተሮች አለመሆናቸውንና እነሱም ደማቸውን ብቻ ለክተው እንዲሚሄዱ አስረድተዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸው እንዲጠይቋቸውም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ በሶማሊኛ ቋንቋ እንዳይነጋገሩ በመከልከላቸው እናታቸው ሊጠይቋቸው መጥተው ሳይጠይቋቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

ባለቤታቸው በሶማሊኛ ‹‹ሰላም ነህ›› ሲሏቸው ‹‹ሰላም ነኝ›› ብለው መልስ በመስጠታቸው፣ ባለቤታቸው አንድ ቀን እንዳይጠይቋቸው በመከልከል ሲቀጡ እሳቸውን ደግሞ ምግብ እንዳይመጣላቸው  በማድረግ በምግብ እንደቀጧቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

የታሰሩበት ክፍል የፀሐይ ብርሃን የማይገባበት መሆኑን፣ መታጠብ መከልከላቸውንና በግለሰቦች እየደረሰባቸው ያለውን ጫና መንግሥት እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡

ይኼ ድርጊትም፣ ‹‹ለዕርቅና የሰላም አባት ዓብይ አህመድ እንዲደርስልኝ እፈልጋሁ፤›› ብለዋል፡፡

በቤታቸው እንደተገኘ የተነገራቸውን መሣሪያ በሚመለከት እንዲፈርሙ በመርማሪ ቢጠየቁ፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው የተወሰደ መሆኑን ገልጸው ‹‹አልፈርምም›› በማለታቸው ብዙ ማስፈራራትና ጫና እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የዳያስፖራ ተወካይ አቶ አብዱራዛቅም ላለፉት 33 ቀናት (እስከ ዓርብ መስከረም 18 ቀን 2011 ድረስ) ጨለማ ቤት መታሰራቸውን ተናግረዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸውን አግኝተው እንደማያውቁ፣ ምግብ በጠበቆቻቸውና በወታደሮች በፌስታል ተደርጎ እንደሚሰጣቸው፣ የታሰሩበት ክፍል እንደማይፀዳላቸውና በራሳቸው ወጪ እንደሚያፀዱ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

የተጠረጠሩበትና ሲሠሩ የነበረው የማይገናኝ በመሆኑ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የታሰሩበት ክፍል አየር ስለማያስገባ፣ የአስም ሕመምተኛ በመሆናቸው እንዲስተካከልላቸው፣ ‹‹ክቡር ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ዓይተህ መፍትሔ ስጠኝ፤›› ብለዋል፡፡

የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ራህማም ተመሳሳይ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነገር ማቅረቡ ሥራውን በአግባቡ አንዳልሠራ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተከሰሱበት በቢሮ ኃላፊነታቸው ወይም በግለሰብነታቸው ይሁን ስላልገባቸው ግልጽ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡

ምግብ በፌስታል ይመጣላቸዋል እንጂ ቤተሰቦቻቸውን እንደማያገኙ፣ መርማሪ ቡድኑ ስለተደፈሩ ሴቶችና ሕፃናት ቀሪ ምርመራ እንዳለው እየገለጸ ያለው እሳቸውም የሚታገሉለትን መሆኑን ጠቁመው፣

‹‹እኔ ሴት አልደፍር በእኔ ላይ የሚያደርገው ምርመራ ምንድነው?›› በማለት ፍርድ ቤት የታደሙትን ፈገግ አሰኝተዋቸዋል፡፡

በመሆኑም ዋስትና እንዲከበርላቸው በጠበቃቸው አቶ ሞላልኝ መለሰ አማካይነትና በአስተርጓሚ ክርክራቸውንና ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ፈርሃንም ተመሳሳይ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

በማንነታቸው እየተሰደቡ መሆኑን ተናግረው፣ በአግባቡ ሊመረመሩና ጥፋተኛም ከሆኑ ፍርድ ቤትና መንግሥት ሊጠይቃቸው ይገባል እንጂ ሊሰደቡ እንደማይገባ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄን ተቃውሟል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብሎ ያቀረበው ቀሪ የምርመራ ሒደት ውስብስባና ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ በመግለጽ ነው፡፡

እስከ ዕለቱ ድረስ (መስከረም 18 ቀን ድረስ) የ158 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን አረጋግጦ፣ ቀሪ ምስክሮቹን ለማነጋገር የምርመራ ሒደቱ እንደሚወስነው አስረድቷል፡፡

የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ስለነበር ነዋሪዎች ከተፅዕኖው ሊወጡ ስላልቻሉ በጣም አስቸጋሪ መሆኑን፣

ከ60 በላይ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን ለመያዝም ተመሳሳይ ችግር እንዳለም አክሏል፡፡

ነገር ግን የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶ እየተከታተለ መሆኑን አሳውቋል፡፡

በርካታ ዜጎች በጅምላ ተጨፍጭፈው በጅምላ የተቀበሩ መሆኑን የሚያሳይማስረጃ ማግኘቱንና እየሠራ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

አስተዳደራዊ ችግሮች የተባለው መርማሪዎች በተገኙበት ተጠርጣሪዎቹ ሲጠየቁ ‹‹ችግር የለም›› እንደሚሉ ተናግሮ፣ አለ ከተባለ ከኃላፊዎች ጋር በመነጋገር እንዲፈታ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ሕክምናም ቢሆን እስከ ሪፈራል ድረስ መታከም የሚችሉበት ስላለ ችግር እንደሌላ አክሏል፡፡

በማንነት ላይ የተሰነዘረ ስድብ አለ ከተባለ እንዲስተካከል እንደሚያደርግም ገልጾ፣  14 ቀናት እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

ግራ ቀኙን የሰማው ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎቹ አቤቱታ መሠረት በተደጋጋሚ የሰጠው ትዕዛዝ አለመፈጸሙን በማረጋገጡ፣ የምርመራ ኃላፊው በቀጣይ ቀጠሮ ቀርበው ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

እስከ ቀጠሮው ድረስ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡት የአያያዝና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲስተካከሉም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ የሠራው ብዙ ነገር እንዳለ የምርመራ መዝገቡን ፍርድ ቤቱ ተመልክቶ ለመገንዘብ ቢችልም፣

ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ቀሪ ሥራዎቹን በአሥር ቀናት ውስጥ አጠናቆ እንዲቀርብ በመንገር ተጠርጣሪዎች የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ አልፎ ለመስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

LEAVE A REPLY