≪የቴዎድሮስ የመጨረሻው ሰዓት በመቅደላ ምን ይመስል ነበር?!!≫ /ተመስገን ባዲሶ/

≪የቴዎድሮስ የመጨረሻው ሰዓት በመቅደላ ምን ይመስል ነበር?!!≫ /ተመስገን ባዲሶ/

«ተዋከበና ተዋከበና
ወዲህ ዞር ቢል ሰው የለምና!!»

የዝነኛውን ድምፃዊ የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ እየሰማው ነው። ኢትዮጵያ በተሰኘው አምስተኛ አልበሙ ላይ ከተካተቱ ሙዚቃዎች ውስጥ ቴዲ ቦታ ከሰጣቸው የዘፈን መልዕክቶች እና ጭብጦች መካከል ገናናውን ንጉስ ዳግማዊ ቴዎድሮስን የዘከረበት ዜማ አንዱ ሲሆን፣ ዜማው ትዕይንት የመፍጠር ልዩ አቅም ያለው ዘፈን ነው ማለት ይቻላል። አማኑሄል ይልማ በቅንብሩ የተጠበበበት ይሄው ሙዚቃ በኖታ ጅረት እላይ ታች እየጋለበ ከቴዲ የአዘፋፈን ስልት ጋር ምርጥ ውህደት ፈጥሮ በምናብ ወደ መቅደላ ይወስደናል። ዘፈኖች መቼትን የመፍጠር ጉልበት አላቸው፣ ቴዎድሮስን በብዙ ቦታ አስቀምጦ የመግለፅ ልቅ ሥልጣን እና ነፃነት ሙዚቃ አላት። ቴዲ በርካታ በቴዎድሮስ ዙሪያ ከተሰሩ ሙዚቃዎች ውስጥ አፄውን ያነሳበት መቼት የመቅደላውን የመጨረሻው ሰአትን ድባብ የሚያሳይና ሰው የሚባል ከንጉሡ ጎን የታጣበትን የጭንቅ ሰአታቶች የተመለከተ ሲሆን፣ ቴዲ የአፄ ቴዎድሮስን በጠላት መከበብ፣ ውድቀትና ሽንፈት የመጨረሻው መስመር ላይ መድረሳቸውን፣ ለማሰቢያ የሚሆን ጊዜ ማጣታቸውን እና ሁሉ ነገር በወከባ የተሞላ መሆኑን፣ እንዲሁም ቴዎድሮስ በዚህ ዓለም ከራሱ በላይ የሚያምነው ብቸኛው የልቡ ሰው ገብርዬን ዞሮ እንዳጣው ዘፈኑ ይተርክልንና ራሱን በጀግንነት ሲያሰናብት ያሳየናል።

ይሄ የዘፈኑ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ የመቼት ድባብ ሲሆን ሌሎቹ ቅጥያ ታሪኮች ግን ይሄን ትውልድ ለማስተማር ተያይዘው የቀረቡ ናቸው። ግን የመጀመሪያው የዜማው ምዕራፍ ላይ ያለው ጭንቀት የቴዎድሮስን በአማራጭ ዕጦት የተከበበ ሁኔታን ገልፆ፣ የአማራጭ ዕጦትም፣ ለወከባ ስሜት አሳልፎ ሲሰጠው፣ በመጨረሻም አፄው የኩራት ሞት እንጂ የጠላቶቹ መጫወቻ መሆንን ካለመፈለግ የሚወሰደውን የሞት ውሳኔ በጥይት አሩር ሲደመድም የዘፈኑ ተረክ ይነግረናል። ዜማው ሕይወት አለው የምለውም እያደመጣችሁት የቴዲ የሲቃ አገላለፅ በጆሯችሁ ገብቶ፣ በአዕምሯችሁ ወደ 150 አመት የጊዜ ምዕዋር ወደኋላ ወስዶ የንጉሱን የመጨረሻ የጭንቅ ሰአት …እንዲህ እያለ ያሳየናል።

ተዋከበና ተዋከበና
ወዲህ ዞር ቢል ሰው የለምና!

በጦርነቱ መሀል እዚህ ላይ ቴዎ ለብቻው አይታያችሁም? በእርግጥ የጀግና ፍፃሜ በሽንፈት ሲደመደም ያሳዝናል፣ በዚህ ምድር ቀን ጎድሎም ለብቻ እንደመቅረት ምን አስቀያሚ የህይወት ድምዳሜ አለ? እስኪ « KASE And KASA BY INSTITUTED OF ETHIOPIAN STUDIES A,A UNIVERSTY TRUN ከተሰኘው መፅሓፍ ከገፅ 205 አንስቶ እስከ 14 የቴዎድሮስን ታሪክ ከሚመለከተው ክፍል ወስደን፣ በቴዲ ዜማ ታጅበን ወደመቅደላ አቀበት በመውጣት በወቅቱ በመጨረሻው ሰአት ላይ ምን እንደተፈጠረ ለማየት በታሪክ ጀልባ ተሳፍረን ወደዚያው እናምራ…

ለቀናት በቴዎድሮስና በእንግሊዝ ሠራዊት መካከል የተደረገው ጦርነት በቴዎድሮስ መዳከምና በጠላት የአሸናፊነት ሚዛን ማየል ወደፊት መግፋቱን ይዟል። የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ ዕለተ_ሰኞ ሚያዚያ 6/1860 ዓመተ ምህረት ወደ ማቆሙ ተቃረበ። መቅደላን ከብቦ የቆየው የእንግሊዝ ሠራዊት አፄ ቴዎድሮስን ማርኮ ለመያዝ በየአቅጣጫው መሯሯጥ ጀመረ። የቴዎድሮስን ሁኔታ አስመልክቶ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሪፖርተር የነበረው ሔንሪ ኤም. ስታንሊ ሲናገር « ሰኞ ቀን ከቀኑ አሥር ሰአት አካባቢ እንግሊዝ መቅደላ ላይ ካሰማራቻቸው ወታደሮች መካከል ሁለት የአይሪሽ ወታደሮች አንዳች የሽጉጥ ተኩስ ሰምተው እና ድምጹን ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተክለፈለፉ እንደደረሱ፣ አንድ ያልታወቀ ኢትዮጵያዊ ከመሬት ላይ ተዘርሮ ለመሞት በማጣጣር ላይ ያገኙታል፣ የግለሰቡ ጣር ምንም አይነት ስሜት ሳይሰጣቸው ≪ቀድሞውንም ከእኛ የተሰረቀ ነው!≫ በማለት በቀኝ እጁ አቅጣጫ የወደቀውን ሽጉጥ አንስተው ይወስዱበታል። ይሄም አልበቃ ብሏቸው የጣቱን የወርቅ ቀለበት እና የአንገቱን የወርቅ መስቀል ከላዩ አውልቀው ይዘርፉታል፣ ከዚያም የወሰዱትን ሽጉጥ እያገላበጡ በአድናቆት ሲመለከቱ ከጎኑ በኩል ከብር ተቀርጾ የተለበደ ፅሁፍ ያገኙበታል። ጽሁፉም ≪ እንደ ኤ,አ 1854 ለአሽከሬ ለፕላውደን የአቢሲኒያው ንጉሥ ቴዎድሮስ ላደረጉለት ቅንነት የተሞላበት ደግነት ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ ከታላቋ ብሪታኒያና የአየርላንድ ንግሥት ቪክቶሪያ የተላከ ሥጦታ≫ የሚል ነበር።

ወታደሮቹ ጽሁፉን ካነበቡ በኋላ ከነከናቸው። አንደኛው ወታደር «ይሄ ሰው ቴዎድሮስ ይሆን እንዴ!?» በማለት ነብሱ ልትወጣ የተቃረበውን ግለሰብ ማስተዋል ጀመረ። ምናልባትም ወታደሮቹ ሊለዩዋቸው ያልቻሉበት ምክንያት አፄ ቴዎድሮስ ተደራጅቶ በመጣውና ዙሪያ እንደከበባቸውም የእንግሊዝ ጦር በተረዱ ጊዜ ቤተሰቦቻቸውን እና የቅርብ ተከታዮቻቸውን ተሰናብተው ወደመቅደላ አፋፍ ከወጡ በኋላ በሽጉጥ ተኩሰው ራሳቸውን እንደጣሉ የተከተላቸው የቤታቸው አሽከር ወልደጋብር ጠላት እንዳይለያቸው በማሰብ ወዲያውኑ አዘውትረው የሚደርቡትን ባለቀጭን ጥለት ነጠላቸውን እና ታጥቀውት የነበረውን ባለከፋይ ቀበቶዋቸውን አውልቆ ወስዶ ስለነበር እንዲሁም ሌላኛው ምክንያት በወቅቱ የቴዎድሮስ አለባበስ ከአንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የተለየ አልነበረም። በተለይም ባዶ እግራቸውን ያለጫማ መታየታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከደረታቸው ስፋትና ከትከሻቸው ትልቅነት በስተቀር፣ ቁመታቸው መካከለኛ እንጂ ረጅምና ግዙፍ ባለመሆኑ፣ እኒያ በሀገራቸው ላይ የተነሱባቸውን ሽፍቶች ከመደምሰስ አልፈው ተርፈው በጄኔራል ናፒየር ለሚመራው ዘመናዊ የእንግሊዝ ጦር «እጄን አልሰጥም!» በማለት በድንገት የወደቁ ታላቁ አንበሳ ስለመሆናቸው የሚያሳምናቸው ነገር ማየት አልቻሉም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መቅደላ በእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ሆነች። ቀደም ሲል የቴዎድሮስ እስረኞች የነበሩትም ኢትዮጵያዊያን በግርግር የታሰሩበትን ቤት በመስበር፣ የእግር ብረታቸውን መሬት ለመሬት እየጎተቱ በአደባባይ መታየት ጀመሩ፣ ከፊሎቹ እስረኞችም እንግሊዞቹ በወቅቱ ሰፍረውበት ከነበረው የጦር ካምፕ ሄደው ተቀላቀሉ። ወዲያውኑ አንድ ግለሰብ እየሮጦ ሄዶ ለጄኔራል ናፒየር የቅርብ ረዳት ለሰር ቻርልስ_እስቴቨሊ «ወዲያ ማዶ አንድ ግለሰብ ተዘርሯል፣ ሰዎች የተዘረረው ቴዎድሮስ ነው እያሉ ነው!» በማለት ሪፖርት አቀረበ። የናፒየር ረዳት ግን ሰውዬው የነገረውን ሪፖርት አላመነበትም ነበር!..በዚህም ምክንያት ይህ ማንነቱ ያልታወቀውን ሬሳ በቃሬዛ ላይ በማድረግ አምጥቶ ለማሳየት ግለሰቡ ሬሳው ወደ ወደቀበት ሥፍራ ተመልሶ ሄደ።

ጭካኔ በተሞላበት አኳኋን ሁለት እግሮቻቸውን በመጎተት፣ ለቃሬዛ መሸከሚያ ተብሎ ከተሰራው የእንጨት ርብራብ ላይ እንደጣሏቸው በመጨረሻም አፄ ቴዎድሮስ ሦስት ጊዜ ካቃሰቱ በኋላ ሕይወታቸው ልታልፍ ችላለች!!» ብሏል የኒውዮርክ ታይምሱ ጋዜጠኛ ሔንሪ ኤም. ስታንሊ።

በሌላም በኩል ይህንን ድርጊት አስመልክቶ ሲ.አር. ማርክሀም ሲያብራራ «ወታደሮቹ የአፄ ቴዎድሮስን ቃሬዛ ተሸክመው ለሰር ቻርልስ ለማሳየት እንደደረሱ ታስረው የተፈቱት እስረኞች በመሽቀዳደም መጀመሪያ መልካቸውን አተኩረው ካዩ በኋላ አንድ ነገር ትዝ አላቸውና የግራ እጃቸውን ከፍ አድርገው ጣታቸውን ማየት እንደጀመሩ አንደኛው ጣታቸው ሰባራ ሆኖ አገኙት፣ አፄ ቴዎድሮስ ከሚታወቁበት አካላዊ መለያ አንዱ ነበር። የሞቱት እሳቸው መሆኑን ያረጋገጡት የእንግሊዝ ወታደሮች ጥይት ወደሰማይ እያንጣጡ ፈነጠዙ፣ የሀገራቸውን መዝሙር ዘምረውም፣ ሰንደቃቸውን አውለበለቡ። ቀጥታ ወዲያው የገቡትም ወደ ዝርፊያ ነበር። ምን ምን ዘረፉ? የሚለውን ሌላ ጊዜ ልመለስበት።

ሲ.አር.ማርክሀም በመጨረሻ እንዳለው «ራሳቸውን ያጠፉት የአቢሲኒያው ንጉሥ የቴዎድሮስ ፊት ብሩህ የነበረ ሲሆን፣ በህይወት ሳሉ ታይቶባቸው የማያውቅ ውብ ፈገግታ በገፃቸው ላይ ፈክቶ ይታይ ነበር!!» ሲል የተመለከተውን አስክሬን በፅሁፉ ገልፆታል።

የክብር ሞት አይደል? እንዴት አይመር ገፃቸው።

«የደከመላት ውበቱን ያቺን የቃል መስታየት
ሞቶ ገደላት ቴዎድሮስ ቆሞ ሥቃይዋን ላለማየት! አይደል ያለው ሣልሳዊው።

LEAVE A REPLY