አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ከንቲባ የላትም። በምክትል ከንቲባ ነው የምትመራው። የአዲስ አበባ ምክር ቤት ከአባላቱ መካክል ከንቲባ መምረጥ ሲገባው፣ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ብቻ ሳይሆን ምክትል ከንቲባ መሆን ይችላል የሚል ሕግ፣ ፓርላማው፣ ሰው ትኩረት ባልሰጠበት ወቅት አጸደቀ። የአዲስ አበቤዎችን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብትን በመጨፍለቅ።
ብዙም አልቆየም ኢንጂነር ታከለ ኡማ በምክትል ከንቲባነት፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን የከተማዋም ነዋሪም ሳይሆን ፣ የኦህዴድ ሹመኛ ሆኖ ፣ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ ምክትል ከንቲባ ተደረገ። ከኢንጂነር ታከለ በፊት ምክትል ከንቲባ ሆና ትሰራ የነበረችው ፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ በምክትል ከንቲባነቷ ቀጠለች፣ በአሰራር ክኢንጂነር ታከለ በታች ሆና።
ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ክጉባዬተኛው ትልቅ ድጋፍ ነው ያገኘችው። ከብዙ እጮዎች መካከል ተወዳድራ፣ የብአዴን/አዴፓ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ ብአዴን/አዴፓን ወክላ የኢሕአዴግ የፖሊት ቢሮ አባል ሆና ተመርጣለች። ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የአዲስ አበባ ምክር ብቃት ያላት አባል እንደመሆኗ፣ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆና መቀጠል ነበረባት።
አሁንም ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሸገር ሙሉ ከንቲባ ትሆን ዘንድ እጠይቃለሁ።አንደኛ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ናት፣ ሁለተኛ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት፣ ሶስተኛ ብቃት ያላት ናት።እርሷን ከንቲባ ማድረግ በሕግ አንጻር፣ የአዲስ አበቤዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ካለመጨፍለቅ አንጻር አዋጭ ነው።
አንዳንድ ወገኖች ኢንጂነር ታከለ ኡማ ቢቀጥል ምን ችግር አለው ሊሉ ይችላሉ። በተለይም ኢንጂነሩ የዶ/ር አባይ ወዳጅ በመሆኑ። አስፈላጊ ከሆነ በምክትል ከንቲባነት፣ የወ/ሮ ዳግማዊት ረዳት ሆኖ መቀጠል ይችላል። ግን የአዲስ አበባ መስተዳደር ቁንጮ ሆኖ መቀጠል የለበትም። ታከለ ኡማ የሸገርን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎትን የሚያስቀድም ነው የሚል እምነት ብዙዎች የላቸውም። ሸገሮች ከአሁን ለአሁን የዶ/ር አብይ ወዳጅ ነው በሚል፣ ለሸገር ህዝብ ጥቅም ያልቆመን መሪ የሚሸከሙበት ምንም ምክንያት አይኖርም !!!!
አዴፓ በጉባዬው አዲስ አበባ የነዋሪቿ ናት በሚል በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለዉን አቋም ግልጽ አድርገዋል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ህዝብ ፍላጎትና ጥቅምን የሚያስጠበቅ አስተዳደር ይኖር ዘንድ በአዋሳው ጉባዬ ግፊት ማድረግ መቻል አለበት። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ፣ የአዲስ አበባን ጥቅም የሚያስጠብቅ ከንቲባ ያስፈላጋል። ለዚህም ነው ህዝብ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን ለከንቲባነት የምለው። !!!!!
በነገራችን ላይ ላለፉት 27 አመታት አንድ ያልተጻፈው ሕግ አለ። የብ አዴን አባል ጠቅላይ ሚኒስተርና የአዲስ አበባ ከንቲባ አይሆንም። አሁንም ይሄ ሕግ ካለም አዴፓ ይሄንን ሕግ ማስቀየር አለበት።