“የእናት መቀነት የፈታ ሌባ” /ዮፍታሔ/

“የእናት መቀነት የፈታ ሌባ” /ዮፍታሔ/

ትናትን በተጠናቀቀው የኢሕአዴግ ጉባኤ መክፈቻ ንግግር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሌብነት ላይ ያላቸውን ጠንካራ አቋም ለሁለተኛ ጊዜ ገልጸዋል። ሌብነት “ኪራይ ሰብሳቢ” እና “ሙስና” በሚሉ ቃላት መሽሞንሞኑ ቀርቶ በግልጽ ቋንቋ ሌብነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል በማለት ተናግረዋል። መፍትሔ ችግርን ከማመንና ከመገንዘብ ይጀምራልና ይህ ይበል የሚያስኝ ነው። ሆኖም ዜጎች ተቃውሞው ከቃላት አልፎ በተግባር እንዲተረጎም ይፈልጋሉ።

ፋና ቴሌቪዥን በቅርብ ጊዜ በለቀቀው ቪዲዮ የዓባይ ግድብ ስለሚገኝበት ሁኔታና ስለወደፊት ዕጣው ጥሩ ዘገባ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። በዚህ ዘገባ አዲስ የተሾሙት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሜቴክ ኃላፊዎችና የሳሊኒ (Salini Impregilo) ባለሙያዎች ተጠይቀዋል።

እንደ ዘገባው፤ ሜቴክ (METEC) ሊሠራ ከተስማማው ሥራ ያከናወነው ከ 30% በታች ቢሆንም 65% ክፍያውን ግን ወስዷል። አንደኛው ኃላፊ በግልጽ እንደተናገሩት ሜቴክ ላልሠራው ሥራ ከ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ተከፍሎታል። እውነቱን ለመናገር ግን ሜቴክ ሳይሠራ የተከፈለው (በጠራራ ፀሐይ ከእናቶች መቀነት እየፈታ የዘረፈው ነው መባል ያለበት) ከዚህ በላይ ነው። ምክንያቱም አጠቃላይ ሥራውን ጨርሶ ሊከፈለው የተስማማው 25.58 ቢሊዮን ብር ሲሆን እስካሁን የተከፈለው 16.79 ቢሊዮን ብር ስለሆነ ከሠራው (25 – 30%) ሥራ ጋር ሲመጣጠን ሊከፈለው ይገባ የነበረው ቢበዛ 7.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር። ስለዚህ ከተከፈለው 16.79 ቢሊዮን ብር ላይ ይህ ሊከፈለው ይገባ የነበረው 7.6 ቢሊዮን ብር ሲቀነስ 9.19 ቢሊዮን ብር ላልሠራው ሥራ የተከፈለው መሆኑን መረዳት ይቻላል። ይህ ደግሞ እስካሁን ባለሥልጣናት የገለጹት እንጂ ኦዲተሮች ሲመረምሩት (የሚመረመር ከሆነ ማለት ነው) ከዚህም የሚዘገንን ሌብነት ዕርቃኑን እንደሚወጣ የታመነ ነው።

ሳሊኒ የተስማማበት የሥራ ዓይነት – ሲቪል ግንባታ
ሳሊኒ ሥራውን ሲጨርስ ሊከፈለው የተስማማበት ጠቅላላ ገንዘብ – 3.3 ቢሊዮን ዩሮ (በጊዜው ምንዛሪ 22 ቢሊዮን ብር አካባቢ)
እስካሁን ያጠናቀቀው ሥራ – 75% (በገለልተኛ አካል ያልተጣራ)
እስካሁን የተከፈለው ገንዘብ 17.5 ቢሊዮን ብር (ከጠቅላላው ክፍያ 79%)

ሜቴክ የተስማማበት የሥራ ዓይነት – ኤሌክትሮ ሜካኒካልና (የብረትና የተርባይን ሥራዎች) ከውኃ ጋር የተገናኙ ሥራዎች።
ሜቴክ ሥራውን ሲጨርስ ሊከፈለው የተስማማበት ጠቅላላ ገንዘብ – 25.58 ቢሊዮን ብር
ሜቴክ እስካሁን ያጠናቀቀው ሥራ – ከ25 – 30% (በገለልተኛ አካል ያልተጣራ)
ሜቴክ እስካሁን የተከፈለው ገንዘብ – 16.79 ቢሊዮን ብር (ከጠቅላላው ክፍያ 65%)

ዶ/ር ዐቢይ በተለያየ ጊዜ “የእናት መቀነት የፈታ ሌባ” እና “አገር የዘረፈ ሌባ” በማለት የገለጹትም ይህን የመሰለውን እንደሆነ አያጠራጥርም።

ሆኖም በዚህ ግድብ ላይ የተሠራው ደባ ይህ ብቻ አይደለም። እስካሁን የተነጋገርነው ስለ ገንዘቡ ብቻ ነው። ዲዛይኑን በሚመለከት ያለው ችግር ገና ምኑም አልተነካም። በዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር በኩልም ስለዲዛይኑ እስካሁን ለሕዝብ የተገለጸ ነገር የለም።

በቅርብ በእንግሊዝኛ የተሰራጨ አንድ ዘገባ እንደሚያመለክተው ከዓለም አቀፍ ቴክኒካል ባለሙያዎች የተውጣጣው ኮሚቴ እ.ኤ.አ በ 2013 በዓባይ ግድብ ላይ በርካታ የዲዛይን (የምሕንድስና) ማስተካካያዎች እንዲከናወኑ ማሳሰቡ ተገልጿል። ከነዚህ መካከል አንዱና ዋናው የግድቡ መሠረት አስተማማኝ በሆነ የዐለት ንጣፍ ላይ ያልተገነባ ስለሆነ ግድቡ የመንሸራተት አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል የሚጠቁም ነው።

ይህ የባለሙያዎች ማስተካከያ ከቀረበ በኋላ ደግሞ ከዚህም የከፋ ዜና መሰማቱን ዘገባው ጨምሮ ያትታል። ይኸውም ከሥር በቁፋሮ የተገኘው ዐለት ሥራው ከመጀመሩ በፊት ከተደረጉት የሥነ-ምድር ጥናቶች (geological studies) ጋራ ፍጹም የማይጣጣም ሆኖ መገኘቱ ነው።

“This second recommendation dealt with the structural integrity of the dam in context with the underlying rock basement as to avoid the danger of a sliding dam due to an unstable basement. It was argued by the panel, that the original structural investigations were done with considering only a generic rock mass without taking special conditions like faults and sliding planes in the rock basement (Gneiss) into account. The panel noted, that there was indeed an exposed sliding plane in the rock basement, this plane potentially allowing a sliding process downstream. The panel didn’t argue that a catastrophic dam failure with a release of dozens of cubic kilometers of water would be possible, probable or even likely, but the panel argued, that the given safety factor to avoid such a catastrophic failure might be non-optimal in the case of the Grand Ethiopian Renaissance Dam. It was later revealed that the underlying basement of the dam was completely different from all expectations and did not fit the geological studies as the needed excavation works exposed the underlying Gneiss. The engineering works then had to be adjusted, with digging and excavating deeper than originally planned, which took extra time and capacity and also required more concrete.”

ይህ እንግዲህ አንደኛ ግድቡ አሁን ባለበት ደረጃ ከደረሰ በኋላ ተመልሶ የመሠረት ሥራ ማስተካከል ይቻላል ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሣል። ሁለተኛ ከዚህ በኋላ መስተካከል የሚቻል ቢሆን እንኳን አሁን ካለበት በበለጠ ጥልቀት መቆፈር፣ ያንን አፈር ማውጣትና ከዚያም ኮንክሪት መሙላት ስለሚጠይቅ እጅግ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ አያጠራጥርም። ሆኖም ግድቡን ማጠናቀቅ የሚቻልበትን አቅምና እውቀት ፈጥሮ ሥራውን መጨረስ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ግድቡ ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳው በዋጋ አይተመንምና።

ነገር ግን ሥራውን በአስተማማኝ ሁኔታ ከፍጻሜ ለማድረስ በዶ/ር ዐቢይ አገላለጽ “ይህን የመሰለ ግድብ መገንባት ቀርቶ ዓይቶ የማያውቀውን” ሜቴክ ያለ አግባብ የወሰደውን ገንዘብ እንዲመልስ አድርጎ ከሥራው ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ያስፈልጋል። ካለበት የብቃት ማነስ በተጨማሪ ከዚህ በኋላ በሥራው እንዲቀጥል መፍቀድ የወንጀል ተባባሪም ያደርጋል። ከዚህም ሌላ ከመጀመሪያም ያለጫራታ ሥራውን እንዲወስድ የተመቻቸለትና ይህን ሁሉ ጉድ ተሸክሞ ዛሬም ሥራዬን 75% ጨርሻለሁ እያለ የሚመጻደቀው የጣሊያኑ የሳሊኒ ድርጅት ተሰናብቶ በአዲስ መልክ በገለልተኛ ባለሙያዎች ተጨማሪ የማስተካከያ ጥናት ተደርጎ በግልጽ ጫራታ ደረጃውን በሚያሟላ ዓለማቀፋዊ ድርጅት ሥራው መከናወን ይኖርበታል።

በአገር ላይ የተፈጸመው ደባ ይቅር ለመባባል ያማያስችል እንደሆነ እስካሁን ያወቅነው እንኳን ከበቂ በላይ ነው። “ዓባይን የደፈረው ባለ ራዕዩ መሪ” መለስ ዜናዊም ሆነ መላው የሕወሐት ባለሥልጣናት ተስማምተውበት አገር ተዘርፋለች። እናቶች ከመቀነታቸው እየፈቱ ያዋጡትን ገንዘብ የበላና የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ተስፋ እንደጉም ያተነነ አካል ዛሬም ለፍትሕ አልቀረበም። በሕግ ይጠየቃሉ የተባሉ በተገባው ቃል መሠረት ሊጠየቁና ከአገር ተዘርፎ በውጭ ባንኮች የተቀመጠውን ገንዘብ ለማስመለስ የተጀመረው እንቅስቃሴ የት እንደደረሰም ሊገለጽ ይገባል። ፍትሕ ካልተከናወነ ይህ ጉዳይ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር የቋንጃ ቁስል ሆኖ ይቀጥላል።

ቃል ወደተግባር ይለወጥ!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

LEAVE A REPLY