ዐማራ አክራሪ ብሔርተኝነትን አያቅፍም /አንዱዓለም ተፈራ/

ዐማራ አክራሪ ብሔርተኝነትን አያቅፍም /አንዱዓለም ተፈራ/

የታሪክን የወደፊት ጉዞ የሚያግድ ማንም የለም። የሀገራችን መሪዎች የያዙት የለውጥ ሂደት፤
ትክክለኛ፣ ጊዜውን የተከተለ፣ አጠቃላይ ገጽታው በጎ ሆኖና መስተካከል ያለባቸውን ድክመቶቹን ይዞ፤
ሊደገፍ የሚገባው ሂደት ነው። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር የፈጠረው፤ “የአንድ ሀገር ሕዝብ
ሳንሆን፤ የተለያየን ሕዝቦች ነን! ሀገራችንም የኢትዮጵያዊያን ንብረት ሳትሆን፤ የተለያዩ ሕዝቦች
በያሉበት ለየብቻቸው ተከልለው የተሰባስቡባት ሀገር ናት!” የሚለው ትርክት፤ አሁን እየተካሄደ ላለው
ለውጥ፤ ከፍተኛ ደንቃራ ሆኗል። ይህ ደግሞ፤ ሀገራችንን እንደ ሀገር፣ ዜጎቿን እንደ አንድ ሕዝብ፣ “እኛ
ኢትዮጵያዊያን!” ብለን ወደፊት እንዳንሄድ ያደርገናል።

መሠረታዊ የሆነው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር አጥፊ መነሻ፤ “እያንዳንዱ የየራሱን፤ ማለትም የትግሬ ወገኑን፣ የኦሮሞ ወገኑን፣ የደቡብ ወገኑን፣ የሶማሌ ወገኑን፣ የዐማራ ወገኑን፣ የአፋር ወገኑን፣ የአኝዋክ ወገኑን፣ የቤንሻንጉል ወገኑን፣ የሐረር ከተማ ወገኑን፣ የአዲስ አበባ ወገኑን እንጂ፤ ጠቅላላ ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያን ማስብ የለበትም!” ነው። ይህ” “የተለያዩ ሕዝቦችና የተለያዩ ብሔሮች!” የሚለው ትርክት፤ አሁን ካለንበት ወደፊት ለመሄድ፤ ትኩረት ተሠጥቶት መልስ ማግኘት አለበት።

እስካሁን በነበርንበት የሃያ ሰባት ዓመታት የጠበበ ወገተኛ አገዛዝ፤ ይህ መርዝ በምንም ዓይነት ሊካድ
የማይችል ጉዳት ከማድረሱ በላይ፤ በቀላሉ ሊጠፋ የማይችል ቅሪት ትቶልን ሄዷል። ዋናው እንቅፋቶች፤
አክራሪ ሆነው በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ጠባቦች ናቸው። ይሄን በሀገር ደረጃ በመድረክ አውጥተን፤
መነጋገርና መፍትሔ ማግኘት አለብን። ጉዳዩ፤ መሠረታዊ የሆነ የመፍትሔ ማዕዘን ደንጋይ ካሁኑ
ማስቀመጡ ላይ ነው። ለዚህ የሚረዳው፤ አክራሪነትን ከወዲሁ በያለንበት በትክክል ምንነቱንና
ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አውጥቶ ማስቀመጡ ላይ ነው። ዐማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ደቡብነት፣
አፋርነት፣ ሶማሌነት፣ ቤንሻንጉልነት፣ አዲስ አበቤነት፣ ትግሬነት፤ አደሬነት የፖለቲካ ማንነት በሆነበትና፤
ከነኚህ ውስጥ የአንዱ ወይንም የሌላው አክራሪ መሆን የበለጠ ተቀባይነትን የሚያስገኝ ጉዳይ በሆነበት
ሀቅ፤ እያንዳንዳችንን ሊያሳስበን የሚገባው፤ “ከዚህ እንዴት ወጥተን፤ ኢትዮጵያዊ ነን እንላለን!”
የሚለው ነው።

የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ በዐማራው ላይ የተለዬ ትኩረት አድርጎ፤ ከአነሳሱም፤ “በዐማራው
መቃብር ላይ የትግሬዎችን ሩፑብሊክ እመሠርታለሁ!” ብሎ፤ ለአርባ ዓመታት ዐማራውን ለማጥፋት
የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ ኖሯል። ቀጥሎም ከሌሎች የኢትዮጵያ “ክልሎች!” ዐማራውን መንጥሮ
በማውጣት፣ ለዝርፊያ፣ ለስደት፣ ለእንግልትና ለግድያ ዳርጓል። ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ ዐማራው ቦታ
እንዳይኖረው አድርጓል። ለዐማራው በተመደበለት “ክልል!” እንኳን፤ ዐማራው ሁለተኛ ዜጋ እንዲሆንና
ውስጡ ሰላም እንዳያገኝ፤ አገው፣ ቅማንት፣ . . . ዐማሮች አይደሉም በማለት፤ ዘለዓለማዊ ነቀርሳ
ተክሏል። የደረሱ ወላዶችን ለማምከን የዘር ማጥፋት ደባ ሠርቶቷል። ይኼ ሁሉ፤ ሊደረግ የሚችል ደባ
ተፈጽሞበት ግን፤ ዐማራ፤ ጠባብ አክራሪ ብሔርተኝነትን የኔ ብሎ አያቅፍም። ይህ የግል ፍላጎቴ
መግለጫ ሳይሆን፤ ኅብረተሰባዊ ሀቅ ነው። በርግጥ፤ ዐማራው የተፈጥሮ ግዴታ ሆኖበት፤ በዐማራነቱ
የደረሰበትን በደል ለመከላከል፤ በዐማራነቱ ተደራጅቶ፤ ጥፋቱን ተቋቁሟል። አሁንም ያ ሀቅ እንዳለ
ስለሆነ፤ የግድ የመከላከል ግዴታውን መቀጠል አለበት።

ዐማራ በመላ ኢትዮጵያ ተበትኖ፤ “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” ብሎ የሚኖር ሕዝብ ነው። ዐማራ ኢትዮጵያን
ኢትዮጵያ ለማድረግ፤ ጠባብነትን ሳያነግትና በዐማራነቱ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያዊነቱ ለኢትዮጵያ ለዘመናት
የታገለ ነው። በዚህ ሂደት፤ ዐማራነቱን ለኢትዮጵያዊነቱ አስረክቧል። ዐማራ ዐማራነቱን የሚነግረ አይፈልግም። ዐማራነቱን ራሱ ጠንቅቆ ያውቀዋል። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር፤ አንድ ሕዝብ ነን ብሎ
ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፤ ተዛምዶ፤ ከጠባብ የክልል አጥር ይልቅ የሕዝብን ዝምድና አንግቶ፤ “ሀገሬ
ኢትዮጵያ ናት!” በማለት፤ አንድነትን ስብኮና ተግብሮ፤ ኖሯል። ይልቁንም ዐማራ ብሔርተኝነትን የኔ
ብሎ፣ አጥር ዘርግቶ፣ በር ስላልዘጋበት፤ ድክመት ተደርጎ ተወስዶ፤ እንዲጠቃበት ሆኗል። ሆኖም ግን
ይሄን የመሰለ ጠባብነት፤ የዐማራው መገለጫ አይደለም።

ለዘመናት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና እንድትቀጥል ዐማራው ያደረገው አስተዋፅዖ፤ ለጠባብ ወገንተኛነት በር እንዲከፍት አያዳዳውም። ከኅብረተሰብ ደንብ ውጪ፤ ጽንፈኛ በመሆን፤ ያልተለመደው፤ ነውሩንና ጸያፉን ነገር፤ “መደረግ ያለበት ጥሩ ነገር!” አድርገው የሚያቀርቡና ለዚያ የሚታገሉ፤ በሁሉም ወገን አሉ። እኒህ
እንደጥንካሬያቸው፤ አንዱን ወገን ከሌላው በማጋጨት ብጥብጥ ይፈጥራሉ። በዐማራው መካከል
እንዲህ ያሉት ሥር ለመያዝ፤ ለሙ መሬት የላቸውም። ለዚህ ነው፤ “ዐማራ አክራሪ ብሔርተኝነትን
አያቅፍም!” በማለት ለዚህ ጽሑፌ ርዕስ የሠጠሁት። ለም መሬት የሌለው ደግሞ አያድግም። ወዲያው
ይጠወልጋል። እያንዳንዳችን እኒህን በያሉበት አጋልጦና ማንነታቸውን አሳይቶ፤ የአንድነቱን ሰንደቅ
የማነገት ኃላፊነት አለብን።

ሐሙስ ጥቅምት ፩ ቀን፣ ፳፻፲፩ ዓመተ ምሕረት

LEAVE A REPLY