ወልዲያ!!!!! /ጃኖ ከየጁ/

ወልዲያ!!!!! /ጃኖ ከየጁ/

ካአባይ እስከ ትግራይ፤
ከፋሲል እስከ አክሱም፤
ከሸዋ እስከ ከረን፤ከደሴ እስከ አስመራ፤
አንች ነበርሽ አሉ፤
ማገር አከፋፋይ፤
አውራጅ አደላዳይ፤
አገር ስትበጃጅ፤ አገር ስትሰራ።

ከሰራሽም አይቀር፤
ካሰራሩሽ አይቀር፤ ሃገርና ድንበር፤
ወልዲያ አባ ዲንሳ፤
በወይብላ ማርያም፤
በየጁዎች ደብር፤
በሹምባሽ ጀምኣ፤ እስቲ እንነጋገር፤
ለስንቱ ማግረሻል፤
ላዩን በጀነቶ፤ ታቹን በጎንደር በር???
ያገር ደም ልዩ ነው፤
ደም አለው ደም ግባት፤ ቀልብን የሚሞላ፤
አንች ነሽ ደም ግባት፤
ከየጎራው ፈሰሽ፤
ሃገር የምትሆኝ፤ የሰንደቅ ዘለላ።
ደግሞ ካገር ብልት፤
አንዳንድ አለ መሰል፤
ዛላው የሚመዘዝ፤ ወርዱ የሚሰፈር፤
ከራማ ደፍቶበት፤
የማንም ያልሆነ፤
ሁሉ ለኔ ሚለው፤ የሁሉም ዳር ድንበር።
ከዳር ድንበሩ ላይ፤
ሰው መሆን በሚሉት፤ ድካው የተፃፈ፤
በናፍቆት እፁብ ሃር፤
እንደ መልጎም ጥለት፤ የተከፈከፈ፤
እንደ ትኩስ ዘማች፤
እጅ ይነሳል አንችን፤
እንደ ክቡር አሽከር፤ እየተሰለፈ።

ከሰልፉ መሃከል፤
ወደው የማይጠግቡ፤
አቅፈው የማይበርዱ፤
ናፍቀው የማይክዱ፤
እኒያ ውብ ልጆችሽ፤ ቃል ማተብ በጠሱ???
የሞት ማንቂያቸውን፤
ያን ታምር ክንድሽን፤ ቃልሽን ረሱ???
ብዬ ላማሽ ነበር፤
ልጅ አልወጣላትም፤
ወንፈል አልሞላትም፤
ባጎረሰችው ልክ፤ ባበላችው እጅ፤
ደረሰልሽ አሉ፤
ጎጆሽን ሰራ አሉኝ፤
የሙጋዱ ሰንደቅ፤ የሩቂያ ልጅ።
ላዩን በአባ ይርዳው፤
ታቹን በሩቂያ፤ በሙጋድ ሪጋ፤
ሰርተው ሰጡሽ አሉ፤
ጎጆሽን ሰውየው፤ ጫጉላሽን አረጋ።
የጁ ውድመን ላይ፤
ባንቱ መጀን ብሎ፤
በደጋጎች ቱፍታ፤ ጀማው ሲሰማማ፤
ይሁን የሚባለው፤
አሚን የሚባለው፤
መቻሬ ሜዳ ላይ፤ ወልዲያ ከተማ።

እኮ የጁ ማለት፤
እኮ መርጦ ማለት፤ የትኛው የትኛው፤
አደራ ወንድሜን፤
ሃጃውን ሙላለት፤
እያለ በዱኣው፤
እያንጎራጎረ፤
ድቤ እየደለቀ፤ ሌሊት ማይተኛው፤
የሚለማመነው፤
እያለ ወንድሜን፤
ክፉ እንዳይነካብኝ፤
ማህተምህ ይርጋልኝ፤ ደግሞ ለዳግመኛው።
እኮ የጁ ማለት፤
ባለ ሦስት መንበር፤ ባለ ሶስት ካባ፤
መንገድ ለጠፋበት፤
መንገዱን ሚያሳይ፤
ጓል ከመይ እያለ፤አስመራ ሚያገባ።
ደግሞ ዘወር ብሎ፤
በአባ ጃሌ እያለ፤ በአፄ ፋሲለደስ፤
የተዋበችን ልጅ፤ የመይሳውን ልጅ ጎንደር ላይ
ሚያደርስ።

ደግሞ የቀናው ቀን፤ ሙሃባው ሲገባ፤
የወልዲያ መንገድ፤
ስንቱን መንገድ መራው፤
በጀነቶ መንገድ፤ በሸዋ ጎዳና።
ቃል ከመርጦ እየሱስ፤
ቱፍታ ከሸህ ዳና፤ የተዋሰ ከንፈር፤
ይዞ መች ይለቃል፤
እንደሲላ ጭልፊት፤ እንደ አንበሳ ጎፈር።
እናም ከቃል መሃል፤
የሰባ ቃል መርጠው፤ ለቃልሽ ያደሩ፤
መቻሬ ሜዳ ላይ፤
ዳስ ጥለዋል አሉኝ፤ አንችን ሊሞሽሩ፤
ጉባርጃ ከንፈርሽ፤
ጉባላፍቶ ባትሽ፤
መቻሬ ወገብሽ፤
ውድመን አንገትሽ፤
መርጦ ሚያየው አይንሽ፤
ዛሬም ናፍቆት በልቶት፤
ዛሬም ሰው ርቆት፤ ቺፍ ይላል ወዘናው፤
እንደ የጁ ጥንቅሽ፤
ኑ ብሉኝ እያለ፤ ያስቀናል ቁመናው።
ያጎደለው ሞልቶ፤
ያጣው በጁ አትርፎ፤
የከዳው ቃል አስሮ፤
ዛሬም የጁን ይላል፤ አንችን ተጠምጥሞ፤
ከአሊ ጓንጉል መንበር፤
ከጣይቱ ማጀት፤ መርጦ ላይ ተሹሞ።
ራስጌሽ ውድመን፤ ተረከዝሽ ሃራ፤
አይቻለሁ ባይኔ፤
ሰው በሚሉት አጀብ፤ ሰው በሚሉት ጎራ፤
ሆደ ሰፊው ጉያሽ፤ በጥበብ ሲሰራ።

በታች ቆላ ዳና፤ በከረም ዛውያ፤
በወይብላ ማርያም፤
የፍቅር ሙዳይ ነሽ፤
የሁሉም አድባር ነሽ፤ አውቃለሁ ወልዲያ።
መገን ኪቢ ቃሎ፤ መገናይ ደፈርጌ፤
ኩማንዳ ጠባ ላይ፤
ፍቅር ታጥኛለሁ፤ መውደድ አደግድጌ።
ደግሞ ለጀብራራ፤
ለቆላ ጃውሳ፤ አውሊያ ለሞላበት፤
እርጎ መከኬ ጋር፤
ደብረ ገሊላ ላይ፤ ይገማሸርበት፤
ይሽራል ህመሙ፤
እያሚና በሎ፤ ሃበሎ ሲልበት።
ወልዲያ ዘመናይ፤
የመርጦ ቅምጥል፤
የውድመን ሸጋ፤ የራስ አሊ ልጅ፤
ልትዳር ነው ሲሉት፤ ዛቷ ሲበጃጅ ፤
ወትሮስ ምን ሊወጣው፤
የጁ እንደለመደው፤
እያሚና በሎ፤ ሃበሎ ነው እንጅ።
እያያ ያሚና በሎ!!!”

LEAVE A REPLY