የጎጃም ክልል ይመስረት/ስንል ዘረኝነትን መዋጋታችን ነው /ከይገርማል/

የጎጃም ክልል ይመስረት/ስንል ዘረኝነትን መዋጋታችን ነው /ከይገርማል/

ከጥቂት ቀናት በፊት የጎጃም ክልል ይመስረት በሚል ያስነበብሁት ጽሁፍ እንደነበር ይታወሳል። በጽሁፉ ውስጥ ያነሳኋቸውን ነጥቦች ተመርኩዘው አስተያየት የሰጡኝን ሁሉንም ሰዎች አከብራለሁ። አብዛኞቹ አስተያየቶች አስተማሪም ተቀባይነት ያላቸውም አይደሉም። በዴሞክራሲ አምናለሁ የሚል ሰው ባነሳኋቸው ምክንያቶች ላይ አሉታዊ ምላሾችን እንዴት ሊሰጥ እንደሚችል አይገባኝም። በሕወሀት ውስጥ የትግራይ የበላይነት አለ ብሎ የሚከስ፣ አዲስ አበባ በራሷ ሰው ነው መተዳደር ያለባት ብሎ የሚከራከር ሰው በጎጃም ላይ ማንም ቢሾም ችግር የለውም ለማለት እንዴት እንደሚደፍር ሲያስቡት ያስቃል። የብዙወቻችን ችግር የራሳችን ጥፋት የማይታየን መሆኑ ብቻ ሳይሆን ስህተታችን ቢነገረን እንኳ ይቅርታ ጠይቀን ለማስተካከል ከመሞከር ይልቅ ደረቅ ሙግት ውስጥ መግባታችን ነው። ተገፋን የሚል ስሞታ በማሰማቴ እንደሀጢያት ቢቆጠርብኝ ስህተቱ የእኔ ነው ብየ ልቀበል አልችልም።

በእርግጥ የአማራ ክልል የሥራ አስፈጻሚ ቦታ ከተወሰኑ አካባቢ በመጡ ሰዎች መያዝ በፈጠረብኝ የመገፋትና የመጠቃት ስሜት ተናድጀ ከረር ያሉ ቃላትን ተጠቅሜአለሁ። በዚህ አቀራረቤ ያስቀየምኋችሁን ሁሉ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይኸ ብቻ ሳይሆን የጎንደር ሕብረት አመራሮችንም ቢሆን ቀደም ብየ ባወጣኋቸው ጽሁፎች እንዳስቀየምኋቸው ይገባኛል። እነሱንም ይቅርታ እንዲያደርጉልኝ እጠይቃለሁ። የጎጃም ክልል ይመስረት የሚለውን ጥያቄየን ግን እቀጥልበታለሁ። ከዚህ በኋላ አዲሱ አደረጃጀት በቀድሞው ክፍላተሀገራት አደረጃጀት መሰረት እንዲሆን ከሚፈልጉት ጎን መቆሜን መግለጽ እፈልጋለሁ።

የሰው ልጅ እንዲህ እንዳሁኑ ባልረከሰበት ዘመን የራስ ያልሆነን ልጅ ወስዶ ለማሳደግ የነበረ ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነበር። ለትምህርት ወይም የተሻለ ሥራ ፍለጋ ከወላጅ ርቀው የሚሰደዱ ሰዎች ከዘመድ አንዳንዴም ከባዕድ ተጠግተው ተምረውና ጥሩ ደረጃ ደርሰው ለቁምነገር የበቁ እንዳሉ ብዙወችን በስም ጠቅሶ በዋቢነት ማቅረብ ይቻላል። ልጅ ወልደው ለማሳደግ አቅም የሚያንሳቸው ወይም ሳይታሰብ የመጣ እርግዝና ከወላጆቻቸው እንዳያቆራርጣቸው የሚሰጉ ወጣቶች የወለዱትን ሕጻን ከመንገድ ላይ መጣል ባይበዛም ከጊዜ ወዲህ የመጣ አይደለም። እኔ ባደኩበት አካባቢ ሆስፒታል ያሳደገው ተጥሎ የተገኘ ልጅ ነበር። የልጅ ነገር ሆኖ እንደቁስል የሚጠዘጥዘውን ወላጅ አልባነት እንዲሽር ከማድረግ ይልቅ እየነካካን ይበልጥ የምናሳምመው ብዙወች ነበርን። በስሙ ጠርተን “አባትህ ማነው?” ስንለው “እሱን ተውትና ሌላ እንጫወት” ሲል እዝን ብሎ ይመልሳል። የእሱ ሀዘን የእኛ የደስታችን ምንጭ ሆኖ በጨዋታ መሀል እየደነጎርን ያንኑ ጥያቄ ደጋግመን እናነሳበት ነበር። መልሱ አይለወጥም “እሱን ተውትና ሌላ እንጫወት!”

ጎጃም የብዙ ጎሳወች ቅይጥ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ከሌሎች ክ/ሀገር ሕዝቦች ጋር የሚወራረሳቸው የጋራ ማንነቶች እንዳሉት ሁሉ የግሉ መለያወችም አሉት። ምሻምሾ፣ እንግጫ ነቀላ፣ ሩፋሩፌ፣ ቀበርቾ ቁፈራ፣ የመሳሰሉት የግል መገለጫወቹ ናቸው። የገና ጨዋታ፣ የበአላት አከባበር፣ የሰርግ፣ የዘፈን፣ የልቅሶ፣ የቅርርቶና የፉከራ ባህሉ፣ አለባበሱ፣ አነጋገሩ፣ የጸጉር አቆራረጡ ሁሉ ከሌላው አካባቢ ጋር አንድ ነው ማለት አይቻልም ብቻ ሳይሆን በተለየ መልኩ የሚተረጎሙም አይጠፉም (ለምሳሌ በሸዋ አካባቢ ሰው ሲሞት የሚደረገው የልቅሶ ሥነስርአት በጎጃሞች ዘንድ እንደ ጭፈራ የሚታይ ነው)። ልጆች የሚጫወቱት የጨዋታ አይነት እንኳ ከሌሎች የሚለይበት ብዙ ነገር አለው። አደን፣ ትግል፣ ቡስትንን፣ ዳጥ፣ ስትራይኳን፣ዶቃ ጨዋታ፣ በለበቅ ላይ አንዳሁላ ሰክቶ በማስወንጨፍ መደባደብ፣ ኪሳራ፣ ውሀ መራጨት፣ ሞርና ቀስት ብይ ጨዋታወች – – – በሌላው ዘንድ አይታወቁም ወይም የሚለዩበት ብዙ ነገር ይኖራል። ይህ ብቻ አይደለም። ጎጃም ራሱን በራሱ በማስተዳደር ረጅም ታሪክ ያለው ነው። ስለዚህ ወደዚያው መመለስ ይኖርብናል። ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የማይፈልግ ይኖራል ተብሎ መቸም አይታሰብም። የራስ ጌታ መሆንን ማን ይጠላል? በራሴ ሳይሆን በሌላ መተዳደር ነው የምፈልገው የሚል ጤነኛ ሰው ይኖራል ብየ አላምንም። በርግጠኝንት መናገር የምችለው ጎጃም በአንድ ወቅት በኃይል የተነጠቀውን የራስን በራስ የማስተዳደር መብት በዘመናዊ አሰራር ቃኝቶ ሊጠቀምበት እንደሚፈልግ ነው። የጎጃምን ክልላዊ መንግሥት ምስረታ የሚቃወሙ ቢኖሩ እነሱ በጎጃም ላይ አዛዥ ናዛዥ ሆነው መቀጠል የሚፈልጉ በአማራ ስም የነገሱብን የአዴፓ ሰዎችና ተከታዮቻቸው ብቻ ነው ሊሆኑ የሚችሉት። አማራነት ከደማችን ውስጥ ያለ የተወሰነው ክፍል ነው። ሌላውን የደማችንን ክፍል ከሰውነታችን አስወጥተው በአማራነት ስም ሊገዙን የሚፈልጉትን መቸም አንቀበልም። የጎጃም ሕዝብ ጎጃሜ ነው።

በክፍለሀገር ወይም በክልል ስም፡ ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ሸዋ ተብለው እንዲደራጁ ቢደረግ አንድም ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ማረጋገጥ ነው። ሁለትም በመሀክል የሚፈጠረውን ጥላቻና አለመተማመን ማስወገድ ነው። እኒህ ክ/ሀገሮች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በሌሎች ጉዳዮች ተባብረው መስራት ይችላሉ። በእኔ ስር መሆን አለብህ የሚለው አካሄድ በህዝቦቻችን መሀል መቃቃርን ከመፍጠር የዘለለ ትርጉም ሊኖረው ስለማይችል ባይታሰብ መልካም ነው። ሁሉም ራሱን ይቻል ሲባል የሚያገናኘን ነገር አይኖርም ማለት አይደለም። ሰላምና ዴሞክራሲን በማስጠበቅ ደረጃ እየተናበቡ መስራት የሚያስችል ጓዳዊ ግንኙነትን በመፍጠር፣ የአንዱ ጉዳት ለሌላውም ጉዳት እንደሆነ አድርገን በመውሰድ፣ ጥሩውን ለማጎልበት መጥፎውንም ለመታገል መተባበር ይቻላል።

አሁን ያለው አዴፓ የቁርቋሶ ሜዳ የሆነው ገና በጠዋቱ በብአዴን ስም የተደራጁት የወያኔ ሎሌወች ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነገሮች ውስጥ ለውስጥ እየተብላሉ፣ ቅራኔወች እየሰፉ ሄደው እዚህ ደረጃ ደርሰዋል። በምርጫና በምደባ ወቅት ያለው አካባቢያዊ መሳሳብና ቡድናዊ ደባ ለአንድ አላማ በተሰለፉ ሰዎች መሀል ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ ተስፋ አስቆራጭ ክስተት ነው። በእንዲህ አይነት የጥላቻና የፍትጊያ ማህበር ውስጥ ፍትሀዊ አሰራር አስፍኖ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚታሰብ አይደለም። የሚገርመው ደግሞ የአማራ አማራ መኖር ብቻ ሳይሆን የወሎም ወሎ የጎንደርም ጎንደር ያለው መሆኑ ነው። ግራም ነፈሰ ቀኝ የጎጃም፣ የወልቃይትና የራያ ጥያቄ ተመሳሳይ ነው። ወልቃይትና ራያ ትግርኛ ትናገራላችሁ ተብለው በግድ በትግራይ ስር እንዲኖሩ ተገደዋል፤ ጎጃምም ቢሆን አማርኛ ትናገራለህ ተብሎ በአዴፓ እግር ተረግጦ እየተገዛ ነው ያለው።

በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት የአማራ ታጋይ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች የአማራው አንድነት ተጠብቆ እንዲቀጥል የሚፈልጉ እንደሆኑ እገነዘባለሁ። አማራ ተብሎ በጠላትነት የተፈረጀው ሕዝብ ሊድን የሚችለው በአንድነት መታገል ሲቻል ነው ብየ አምን ስለነበር እኔም ቢሆን አማራው ተደራጅቶ ራሱን እንዲከላከል የአቅሜን ሞክሬአለሁ። እየቆየሁ ስሄድ ግን ከአማራነት በላይ ጎጃሜነት እንደሚያስጠቃ ለመገንዘብ ቻልሁ። እንደአማራ በጠላትነት ተፈርጀን መከራ እየተቀበልን ነው፤ እንደጎጃም ደግሞ የእኛ ባልሆኑ ሰዎች ተረግጠን በባርነት እየተገዛን ነው። የአዴፓ ሥራአስፈጻሚ ምርጫን ካየሁ በኋላ ሁኔታውን ለማጣራት ባደረኩት ጥረት ዕውነትነቱን በተግባር አረጋግጫለሁ። “የጎጃም ክልል ይመስረት” በሚል ጽሁፍ ሳወጣ ለዚያ ያበቃኝን ምክንያት መርምረው ወገናዊ አስተያየት የሰጡኝ የሉም ማለት ይቻላል። አራዳ ሌቦች “ሌባ!” ሲባሉ እነሱም በተራቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ሌባ! ሌባ!” እያሉ እንደሚያምታቱ ሁሉ በሁካታ ርዕስ ለማስቀየር የሚደረግ ተራ ጩኸት እኔን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ጎጃሜ እንደሚያሳምም መታወቅ አለበት። ምክንያቱም ህመሙን ቀድመው የታመሙት ብዙሀኑ ጎጃሜወች በመሆናቸው። “ኢትዮጵያዊ ከሆነ በሁሉም ቦታ ቢሾምና ቢገዛ ምናለ” በማለት ለወያኔ ሊሟገቱ ያልፈቀዱ ሁሉ “አማራ እስከሆኑ ድረስ የተወሰኑ አካባቢ ሰዎች በመላው አማራ ላይ ቢሾሙና ቢገዙ ምን ችግር አለው፤ ይህን የሚቃወም አስተሳሰብ ጠባብነት ነው” ብለው ሲከራከሩ መስማት የቁጭት ሳቅ ያስቃል። እንደ እኔ ከሆነ ጠባብነት ይህ ነው፤ ወገኔ የሚሏቸው ሰዎች ጥፋት የማይታያቸው፤ በሰው ቁስል እንጨት የሚሰዱ ሰዎች ተግባር።

ከእንግዲህ በኋላ የሚደረግ ማስተካከል ትርጉም የሚኖረው አይመስለኝም። ቅሬታወችን አስታሞ ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት ከመስራት ይልቅ በጀሌወች ወከባና ውግዘት ለማለባበስ የተሄደበት መንገድ በሕዝብ መሀል የበለጠ ጥርጣሬ እና ጥላቻ ስር እንዲሰድ ምክንያት ሆኗል። ከዚህ በላይ የሚደረግ አፈና ቢኖር ጉዳቱን እያከፋው እንደሚሄድ መታወቅ አለበት። የሚበጀው ሁሉም በዱሮ ማንነቱ እንዲካለል መፍቀድ ብቻ ነው።

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በክልል ደረጃ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን እስከ ቀበሌ ድረስ የሚሰራ መሆን አለበት። ቀበሌወች ወይም ወረዳወች ወይም ዞኖች የሚመሯቸውን ሰዎች መርጠው የመሾም ብቻ ሳይሆን የሰራተኛ ቅጥርም በየደረጃቸው በመሰረቱት አስተዳደር ውስጥ ባሉ መሥሪያቤቶች የሚፈጸም መሆን ይገባዋል። በቀበሌ የሚፈጸም ቅጥርን የሚያሟላ ባለሙያ በቀበሌ ደረጃ ማግኘት ባይቻል ውክልናውን ለወረዳ መስጠት፣ ወረዳው የማይሸፍነውን ለዞን፣ ዞኑ የማይሸፍነውን ለክልል፣ ከክልሉ አቅም በላይ ለሆነ ጉዳይ ለፌደራል መንግሥቱ በመስጠት የሚፈጸም ቢሆን ተቀባይነት ይኖረዋል። በቀበሌ፣ በወረዳም ሆነ በዞን የአስተዳደር ቦታወች ላይ የሚሾሙት ህጉን ተከትሎ በተመረጡ በራሳቸው ሰዎች መሆን ይኖርበታል። ማንም ከሌላ ቦታ አምጥቶ እንዲጭንባቸው ሊፈቀድ አይገባም። አዲስ አበባ በራሷ ከንቲባ መመራት አለባት ስንል የነበረው በዚህ ምክንያት ነው። አዲስ አበባ በራሷ ሰዎች መመራት አለባት የሚባለው አንደኛ የራስን በራስ ማስተዳደርን መብት ለማስከበር ሲሆን ሌላው ደግሞ የጎደለበትን የሚያውቀው ከማንም በላይ ኗሪው በመሆኑ ነው። ለከተማዋ ዕድገትና ለሕዝቡ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ የሚችለው ከሌላ አካባቢ ከመጣ ሰው ይልቅ ባለቤቱ አዲስ አበቤው መሆኑም መዘንጋት የለበትም። ይህን ዕውነታ ልክ ነው ብለን ከተቀበልን ጎጃም በሌሎች ይተዳደር የሚል መከራከሪያ ሊኖረን አይችልም።

እኔ እስለከማውቀው ድረስ በየደረጃው ያሉ ብዙወቹ የካቢኔ አባላት በአማራ ስም ከሌላ አካባቢ መጥተው የተሾሙብን ሰዎች ናቸው። በተለይ የአስተዳዳሪው፣ የጸጥታው፣ የማስታወቂያ ጽ/ቤት ኃላፊው፣ የፖሊስ አዛዡ ቦታ በኢሕዴን ታጋይነታቸው ጊዜ መስዋዕትነት ከፍለዋል ለተባሉ የአንድ አካባቢ ሰዎች እንደድሮ ጋሻ መሬት የተሰጠ ሽልማት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህ የተዛባ አሰራር መስተካከል የሚችለው ሁላችንም የየራሳችን ጎጆ ባለቤቶች ስንሆን ብቻ ነው።

ከአሥተዳደር ውጭ ባሉት ቦታወች የትኛውም ኢትዮጵያዊ ተቀጥሮ ሊሰራ የሚችልበት አሰራር መዘርጋት ተገቢ ነው። በግል ሰርተው ለመኖር የሚፈልጉትም ቢሆን የየአካባቢውን ህግ አክብረው እንደማንኛውም ዜጋ በዕኩልነት ሰርተው የመኖር መብታቸው መጠበቅ ይኖርበታል። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ሌሎችን መግፋት ማለት አይደለም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል ሄዶ የመስራትና የመኖር መብቱ ሊከበር ይገባል። በሚኖርበት አካባቢ ሕዝብ ተመርጦ በሀላፊነት እንዲያገለግል የተሾመ ሰው ቢኖር የሕዝቡ ምርጫ ስለሆነ ማክበር ያስፈልጋል። በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እሳቤ ሕዝቡ የማያውቀውንና ያልመረጠውን አምጥቶ በኃላፊነት ቦታ ላይ ማስቀመጥ ግን በንቀትና በማናለብኝነት የሚፈጸም አምባገነናዊ ተግባር ነው።

የአንድነት ኃይሎችም ቢሆኑ የሚፈልጉት ከዚህ የተለየ አይመስለኝም። ቀደም ብሎ በነበረው የክፍለሀገር አደረጃጀት ስም ተደራጅተው የሚታገሉትም ከዚህ ውጭ የሆነ እይታ ይኖራቸዋል ብየ አላስብም። ጎጃም ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የጋራ ሀገራችንን በመገንባቱ ተግባር ብቁ ተሳትፎ ማድረግ አለበት። ሁሉም ራሱን ለማስተዳደር የሚያስችለውን አሰራር መዘርጋት ከተቻለ በውክልና የሚፈጸም ጭቆና ይጠፋል ማለት ባይሆንም ከዴሞክራሲ መብቶች ውስጥ ለአንዷ ነጥብ ምላሽ የሚሰጥ በጎ ተግባር መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። በሌላ በኩል በዘር የማሰብን ጎጂ ባህል የሚያጠፋ ፍቱን መድሀኒት እንደሚሆንም አያጠራጥርም።

ቀደም ብለው በቀድሞ ክ/ሀገራት ስሞች የተደራጁት ሰዎች በቋንቋ ላይ በተመሰረተው ፌደራሊዝም ምክንያት የተነጠቁትን የሕዝባቸውን ክብር ለማስመለስ መታገል ይኖርባቸዋል። የጎንደር ህብረት፣ የሸዋ ህብረት፣ የወሎ ህብረት፣ የጎጃም ህብረት ቢያንስ ከእኔ እይታ ቀድመው ማየት በቻሉ ሰዎች የተመሰረቱ ናቸው። ጎጃም አማራ ብቻ እንዳልሆነ ሁሉ ጎንደርም፣ ሸዋም ሆነ ወሎ አማራ ብቻ አይደሉም። በውስጣቸው ያለውን ሕዝብ አሰባስበው በአንድነት ለማስቀጠል ከዚህ የተሻለ አደረጃጀት የሚኖር አይመስለኝም። የጎጃም ክልል ይመስረት ስል ዘረኛ መሆኔ ሳይሆን ዘረኝነትን መዋጋቴ ነው፤ መጥበቤ ሳይሆን መስፋቴ ነው።

የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ጩኸታችንን እንዲሰማ እንፈልጋለን። ጎጃም ከተጫነበት የጭቆና ቀንበር ነጻ ሆኖ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ይፈልጋል። ለቅማንትና ለሲዳማ ሕዝብ ጆሮ የሰጠ መንግሥት ለጎጃም “ጆሮ ዳባ ልበስ1” ሊል አይገባም። ዴሞክራሲያዊት ሀገር የምትመሰረተው የአንድን አካባቢ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በሌላ ኃይል እንዲወሰን በማድረግ አይደለም።

የጎጃም ልጆች በጎጃሜነት ተደራጅተን ድምጻችንን ማሰማት ይኖርብናል።

የጎጃም ክልል ይመስረት!

LEAVE A REPLY