ይድረስ፦
– ለአቶ ታከለ ኡማ
(የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ)
– ለአቶ ታዬ ደንደአ
(የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ)
ክቡራን፣
በመጀመሪያ ውድ የሥራ ጊዜያችሁን ሰውታችሁ ልታነቡኝ ጊዜ ከወሰዳችሁ በጣም አመሰግናለሁ። ጊዜያችሁን ለመሻማት የወሰንኩት ምናልባት በሥራ መጨናነቅ ያላስተዋላችሁት ሐቅ ካለ በማመላከት የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ተመኝቼ መሆኑን እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ።
በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶች በገፍ እና በግፍ ለእስር ተዳርገዋል። ብዙዎቹ ፍርድ ቤት እንኳን ለመቅረብ ወግ አልበቁም። በዚህ ሒደት ውስጥ ሰብአዊ ክብርም፣ የሕግ የበላይነት እና የለውጥ ተስፋ አንድ ላይ ተጨፍልቀዋል። “ይህ ለምን ሆነ?” ያልን እንደሆነ “የጥላቻ አርበኞች” የእርስበርስ ብሽሽቅ ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን።
ፖለቲካችን መጠላለፍ የበዛበት፣ ሴረኛ፣ ጎጠኛ እና ጨቋኝነት ላይ መሠረቱን የጣለ፣ እንዲሁም ባላዋቂነት፣ በእልኸኝነት እና ቸልተኝነት ባሕል ላይ የተገነባ መሆኑን፥ ባለፉት ዓመታት ስለፍትሕ እና ርትዕ በጮህኩባቸው ጊዜያት ተረድቻለሁ። በፖለቲካ ባሕላችን እንደተረዳሁት አንድ ጉዳይ ብዙ ስለተጮኸበት የተሳሳተ ወይም ዝም ስለተባለ ትክክል እንዳልሆነ ተረድቻለሁ። እናንተ ግን ከአንድ ወገን ጩኸቱም፣ ከሌላ ወገን ዝምታውም ወጥታችሁ ፍትሐዊ እርምጃ እንድትወስዱ እፈልጋለሁ።
ክቡራን፣
ከባለሥልጣናት ሁሉ ሁለታችሁን መርጬ የጻፍኩላችሁ ያለ ምክንያት አይደለም። ከላይ ባጭሩ ለመጥቀስ የሞከርኩት ሴራ እና መጠላለፍ ማለት ምን እንደሆነ በቅጡ ትረዱታላችሁ ብዬ በመገመት ነው።
የተከበሩ ምክትል ከንቲባው የመጡበት መንገድ ምንም እንኳን የተለመደውን ሕጋዊ ሒደት እና አሠራር የተከተለ ባይሆንም፥ ኢትዮጵያ ካለችበት የለውጥ እንቅስቃሴ አንፃር በትዕግስት ሊታለፍ የሚችል ነው ብዬ አምናለሁ፤ እንዲህ አብጠርጥረን ከተመለከትን የሚተርፍ ባለሥልጣን የለምና። እርስዎም ይህንን ቅሬታ ተመልክተው በተለይ ለተገፉት እና ለድሀ አዲስ አበቤዎች አጋርነትዎን ለማሳየት መሞከርዎ በአዎንታዊነት ሊመዘግብልዎት ይገባል ብዬ አምናለሁ። ይሁን እንጂ ሁሉን ነገር በጎጥ አስተሳሰብ ብቻ እና ብቻ ሊተረጉሙ የሚፈልጉ ሰዎች (“የጥላቻ አርበኞች” ብላቸው እመርጣለሁ) የተሠሩ ጥፋቶችን ሁሉ ከዘውግ ማንነትዎ ጋር በማገናኘት አላስፈላጊ ዘመቻዎችን በማካሔድ ስሜትዎን ጎድተውት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። ምናልባት የአዲስ አበባ ወጣቶች በገፍ እና በግፍ መታሰር ያገባኛል በሚል ስሜት ምንም ሳይናገሩላቸው የቀሩት በእዚህ ምክንያቶች ይሆን እንዴ እያልኩ እሰጋለሁ።
በተመሳሳይ ደግሞ አቶ ታዬ ደንደአ እንዳይደገም በምንፈልገው ስርዓት የመጠላለፍ ፖለቲካ ሰለባ ሆነው ካንዴም ሁለት ሦስቴ ለእስር በመዳረግዎ የኢፍትሐዊነትን አስቀያሚነት ከእርስዎ የበለጠ የሚረዳው ይኖራል ብዬ አላምንም። ለዚህም ነው የእርስዎን የመንግሥት ሥልጣን ማግኘት የለውጡ አንድ ማሳያ አድርጌ የወሰድኩት። ይሁን እንጂ፣ አዲስ አበቤዎች የቡራዩውን የግፍ ግድያ/ጥቃት አውግዘው ሰልፍ በወጡበት ቀን ጥቂት የጥላቻ አርበኞች የተናገሯቸውን አስቀያሚ ነገሮች ይዘው ፌስቡክ ላይ የጻፉት ነገር አስደንግጦኝ ነበር። ይሁን እንጂ እርስዎን በዚህ የአፍ ወለምታ ብቻ ተመሥርቼ ልፈርጅዎት አልፈልግም። ነገር ግን የአዲስ አበባው አፈሳ ከእርስዎ ንግግር በኋላ የመጣ በመሆኑ ንግግርዎን እና እስሩን ነጥዬ መመልከት አልቻልኩም።
የጥላቻ አርበኞች የሚገኙት ከአዲስ አበቤዎቹ መካከል ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በቡራዩ የደረሰውን አሰቃቂ ጥፋት ለመሸፋፈን በአዲስ አበቤዎች ላይ ለማሳበብ ብዙ ፕሮፓጋንዳ የሠሩ ሌሎች የጥፋት አርበኞችም መኖራቸው ይታወቃል። ነገር ግን የእነርሱን የሴራ ትንተና ተከትሎ የጅምላ እስር እና ፍርድ መስጠት አግባብ አይደለም፤ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ካሉ ያለምንም ጥያቄ በርትዓዊ የሕግ አግባብ መዳኘት አለባቸው። ቅሬታዬ ያለ ሕግ አግባብ ስለሚፈፀመው ግፍ ነው።
ክቡራን፣
እናንተ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደመሆናችሁ ከስሜታችሁ መነ፡ጠል፣ ሆደ ሰፊ መሆን እና ለሕግ የበላይነት ታማኝ መሆናችሁን በተቻለ መጠን ማሳየት አለባችሁ ብዬ አምናለሁ። ክቡር ምክትል ከንቲባው ለከተማዎ ነዋሪዎች ወገንተኝነትዎን፣ አቶ ታዬ ደንደአም ለፍትሕ እና ርትዕ ተቆርቋሪ መሆንዎን ማስመስከር አለብዎ ብዬ አምናለሁ።
ወጣቶቹ የታሰሩበት ሒደት በየቡና ቤቱ እና በየመንገዱ ያመሹ ሰዎችን በመልቀም እንደሆነ በማጠያየቅ ተረድቻለሁ። ከታፈሱት ውስጥ ሥራ ያላቸው ብዙዎቹ ሲፈቱ ሥራ አጦቹ ግን እንዲቆዩ እና ወደ ጦላይ “ለማረሚያ ሥልጠና” እንደተጋዙ ተረድቻለሁ። ሥራ አጥነታቸው የነርሱ ጥፋት አይደለም፤ የአገራዊ ችግራችን የጣለባቸው ዕዳ ነው። ድጋሚ ሊቀጡበት አይገባም። በዚያ ላይ ያጠፉት ጥፋት ቢኖር ለሕግ እንደሚቀርቡ እናውቃለን፤ ፍርድ ቤት ያልቀረቡት ጥፋታቸው የአመለካካት በመሆኑ ነው። እንገነባዋለን ብለን የምንመኘው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማንወዳቸውንም የማይወዱንንም ሰዎች አመለካከት ማክበር ይጨምራል አይደል? የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንኳን ሳይታወጅ ወጣቶችን አግበስብሶ ማሰር፣ የታሰሩትን በሰብአዊ መብቶች ጥሰታቸው ወደሚታወቁ ወታደራዊ ካምፖች ማጋዝ ምን ዓይነት ውጤት ይኖረዋል? ሰብአዊነት ሲዋረድ፣ የሕግ የበላይነት በሰዎች የበላይነት ሲረገጥ እንዲሁም የለውጡ ተስፋ ቀስ በቀስ ሲሸረሸር የማስቆም አቅሙና ሥልጣኑ ባይኖራችሁ እንኳን እንዴት አንድ ነገር መናገር አቃታችሁ?
ክቡራን ሆይ፣
ጽሑፌን የምቋጨው በአንድ ማሳሰቢያ ነው። ሥልጣናችሁ የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተወሰደውን ኢፍትሐዊ እርምጃ ማስቆም ወይም ለጠፋው ጥፋት ከሣ ማስገኘት አይችል ይሆናል። ነገር ግን ቢያንስ ተቃውሟችሁን በቃላት በመግለጽ አጋርነታችሁን ብታሳዩ ስለ እናንተ እና ስለወደፊቱ ብዙ ነገር እንደሚናገር ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።
በፍቃዱ ኃይሉ
አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣
የኢትዮጵያ ዜጋ