/Ethiopia Nege News/:- በተለይ የኦነግ አመራሮችን በመቀበል ሂደትን ተከትሎ በቡራዩ አካባቢ በተፈፀመ ዘግናኝ ግድያና ጉዳት ምክንያት 1204 የሚሆኑ የአዲስ አበባ አካባቢ ወጣቶች በጦላይ የጦር ማሰልጠኛ ተቋም ለአንድ ወር ታጉረው የሰነበቱ ሲሆን በመጪው ሀሙስ እንደሚለቀቁ ፖሊስ አስታውቋል።
ያለ ህጋዊ ፈቃድና በጅምላ በተደረገው እስር ወደ ጦላይ የተላኩት ወጣቶች የቤተሰብ መጠየቅ ክልከላን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸመባቸው የተገለፀ ሲሆን ያለፈቃዳቸው የሚሰጣቸውን ስልጠና በመቃወም በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን የተቃውሞ ዘመቻው ተጠናክሮ መሰንበቱ አይዘነጋም።
ፖሊስ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጣቸው የተጣረሱ መግለጫዎች የታሳሪዎቹን ጥፋት ለመግለጽ እንደተቸገረ የሚያስረዳ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች በጅምላ የታጎሩት እስረኞች ቢለቀቁም ተጠያቂነትና ግልጽነትን ማረጋገጥ እንደሚገባና የዶ/ር አብይ አስተዳደር ምላሽ ሊሰጥበት የሚያስፈልግ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ያስረዳሉ።
የማህበራዊ ሚዲያው ዘመቻ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ለማነጋገር ወደ ጀርመን የሚያደርጉት ጉዞ ላይ ተቀባይነታቸውን ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባ የተመለከተ ሲሆን በመጪው ሐሙስ የእስረኞቹ ፍቺም ከዘመቻው ጋር ሊያያዝ እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።