ትላንት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጦላይ ስለታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች የተናገረውን ነገር በቪኦኤ ስሰማ ወጣቶቹ ታፍሰው እንደታሰሩ “የአዲስ አበባው የጅምላ እስር የህውሃትን ሌጋሲ ማስጠበቅ እንጂ ሕግ አክባሪነት አይሆንም” በሚል የጻፍኩት ወደ አዕምሮ መጣ። እኚህ ፖሊስ አዛዥ አሁንም እያሉን ያሉት የተወሰደው እርምጃ ትክክለኛ እና ሕግን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ነው። እንዲህ እንዲያደርጉ ሥልጣን የሰጣቸውን ሕግ ግን አልገለጹልንም። አሁንም በወያኔ ሕገ-አራዊት ከሆነ አገሪቱ የምትተዳደረው እሳቸው ያሉት ልክ ሊሆን ይችላል። በሕገ-መንግስቱም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ውስጥ በወንጀል የተጠረጠረን ሰው ለአንድ ወር ያህል ፍርድ ቤት ሳታቀርብ፣ ክስ ሳትመሰርት ወታደራዊ ካምፕ ወስደህ አሰቃይ የሚል አንቀጽ የለም። ይህ እጅግ የከፋ የሕግ እና የመብት ጥሰት ነው።
ጸባይ ማረሚያ የሚገቡ ወጣቶች እንኳን በእድሜያቸው የተነሳ በመደበኛ እስር ቤት መታሰር የሌለባቸው ሲሆኑ እሱም የሚወሰነው በፍርድ ቤት ነው። ፖሊስ አሳሪ፣ ፖሊስ ወንጃይ፣ ፖሊስ ዳኛ፣ ፖሊስ ፈራጅ የሆነበት ሥርዓት ያለፈና ያበቃለት መስሎን ነበር። ለማንኛውም ይህ አይነቱ አስነዋሪ ሕገ ወጥ ድርጊት በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ቡራዩ ሰዎችን ባረዱትም፣ ሻሸመኔ ሰው ሰቅለው ባደባባይ ባሰቃዩትም ሆነ በአዋሳ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ድርጊት በፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ሊፈጸም አይገባውም። በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በምን አግባብ መያዝ እና መቆየት እንዳለበት ምንም የማያሻማ እና ትርጉም የማይፈልግ ሕግ አለን። እሱን በሥራ ላይ ማዋል ብቻ ይበቃል።
ለማንኛውም፤
– ዶ/ር አብይ የአዲስ አበባን ወጣቶች ቶሎ ለቀው በእነሱ እግር ባይሆን እነዚህን የፖሊስ ባለሥልጣናት ለሥልጣና እዛው ጦላይ ቢያቆዩዋቸው ይሻላል። እንዲህ አይነት የሕግ ጥሰት ሲፈጸም እያዩ እና እየሰሙ ዝም ማለትዎችም እርሶንም ያስጠይቅዎታል። የመደመር ቀመሩንም ይጎዳዋል።
– መንግስት ሕግ ሲጥስ፣ መብት ሲረግጥ እና አንዳንድ ሥህተት ሲሰራ መንቀፍ እና እንዲስተካከል መጠየቅ መንግስት ማገዝ ነው። የመደመሩም ፋይዳ ይሄው ይመስለኛል። መንግስትን ለምን ወቀሳችሁ እያላችው ያዙኝ ልቀቁኝ የምትሉ ሰዎች ጊዜው ለእንዲህ አይነት ካድሬነት ምቹ ስላልሆነ እባካችሁ ዛሬ እንኳን ትምህርት ውሰዱ። ‘እኔ ወይም ሞት’ የምትለዋ የካድሬዎች መፈክር በዛሬው የአገራችን ፖለቲካ ሥፍራ ያለው አይመስለኝም።
– የለውጡን ኃይልም ሆነ ያለውን መንግስት የራሳችሁ ብቻ አድርጋችሁ የምታስቡ ሰዎችም እባካችሁ ሰከን በሉ። ይሄ መንግስት የአንድ ብሔር አይደለም። ይሄ መንግስት ለተወሰኑ ሰዎች የመጣም አይደለም። ለመደመሩ ጥሪ ምላሽ የሰጠው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዚህ ለውጥ ላይ እኩል ባለመብት፣ እኩል ተቆርቋሪ፣ እኩል ባለድርሻ እና እኩል ኃላፊነት አለበት።
– ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት መንግስት ሰብአዊ መብት ጣሰ ብለን ስንወቅስ ለመንግስት ጥብቅና ይቆሙና ሌላውን ሰው ይሳደቡ፣ ያስፈራሩ እና ያንጓጥጡ የነበሩት ጥቂት የህውሃት ካድሬዎች ነበሩ። ዛሬ የነሱ አፍ ተለጉሞ በምትካቸው ጥቂት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ እና አንዳንዶቹም የኦነግ ደጋፊ ነን ብለው እራሳቸውን የሚገልጹ ሰዎች መንግስትን አትውቀሱ፣ የኦሮሞ ልሂቃን ሲሳሳቱ ተሳሳቱ አትበሉ፣ ይህን ስርዓት የሚተች ጸረ ኦሮሞ ነው የሚሉ እጅግ አስነዋሪ እና መስመሩን የሳተ ነቀፌታዎችን ሲሰነዝሩ እያየን ነው። ጥሩነቱ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ምርጥ እና አርቆ አሳቢ ልጆች ስላሉት በኦሮሞ ሕዝብ ስም መነገድ ለምትፈልጉ ሰዎች ሁኔታው የሚመች አይመስለኝም።
ለማንኛውም ከገባንበት አዘቅት ለመውጣትም ሆነ እንደ ሕዝብ እና እንደ አገር የተጋረጡብንን ፈተናዎች በጋራ ለመመለስ በመከባበር እና በግልጽ በችግሮቻችን ዙሪያ መወያየት መልካም ነው። ሆኖም ግን ለድርድር የማይቀርቡ የሰብአዊ መብት መርሆዎች፣ የሕግ የበላይነት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ የሆኑ እሴቶች ላይ ግን ሁላችንም አብረን በጋራ ዘብ ልንቆም ይገባል።
ቸር ያሰማን