አቶ ታዬ ደንደአ ዳግም መስመር ስተዋል /በመሳይ መኮንን/

አቶ ታዬ ደንደአ ዳግም መስመር ስተዋል /በመሳይ መኮንን/

አቶ ታዬ ዳግም መስመር ስተዋል። ለተቀመጡበት ወንበር የሚመጥን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ ተነክረዋል። እልህ ሲተናነቃቸው ፌስቡክ ከፍተው እንዳለ እንደወረደ ይዘረግፉታል። ትላንት የረገሙትን ወገንተኝነት ዛሬ እሳቸው ያቀነቅኑት ጀምረዋል። ትላንት የተጠየፉትን ኢፍትሀዊነት ቋንቋ ሳይቀይሩ እንዳለ ገልብጠው እያሳዩን ነው። ጊዜው የእኛ ነው በሚሉ የብሄር አቀንቃኞች ዜማ መደነስን መርጠዋል። ማዳላት አይበጅም እያሉ በማዳላት ተጠምደዋል። እሻጥርን እያወገዙ በአሻጥር የተንቆጠቆጠ የፖለቲካ መስመር ላይ ሽምጥ እየጋለቡ ነው። በግማሽ መላጣ ሆነው ጎፈሬውን እያብጠለጠሉት ነው። ‘ህገወጥነት’ ብለው የሚከሱትን አካል በህገወጥ መስመር ለማረም ወገባቸውን ታጥቀው ተነስተዋል። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት የመንግስትን ትልቁን ሃላፊነት ተሸክመው ነው። ያውም ፍትህን በእኩልነት ያሰፍናል ተብሎ በሚጠበቅ የሃላፊነት ወንበር ላይ ተቀምጠው።

አቶ ታዬ በዚሁ መቀጠል የሚገባቸው አይመስለኝም። ስሜታቸውን መቆጣጠር ካቃታቸው፡ ነጻ ግለሰብ ሆነው እንደፈለጋቸው ሀሳባቸውን የሚያስተላልፉበትን፡ አቋማቸውን የሚያንጸባርቁበትን፡ ወገኔ ለሚሉት አካል የሚቆሙለትን ሌላ መንገድና ቦታ ቢፈልጉ ለእሳቸውም፡ ለጤናቸውም፡ ለድርጅታቸውም፡ ለመንግስታቸውም የሚበጅ ይሆናል። ከተቀመጡበት ወንበር እኩልነትን እንጠብቃለን። ከጨበጡት ሃላፊነት ሚዛናዊ ፍርድ እንሻለን። ተራ ብሽሽቅ ውስጥ ተነክረው፡ የቃላት ጦርነት ላይ መጠመዳቸውን ያቁሙት። ቢያንስ ለወንበራቸው ክብር ዘብ ይሁኑ።

አንድ ተጨማሪ ወንድማዊ ምክር። እንዲህ እልህ ሲተናንቅዎት ከፌስ ቡክ አከባቢ ይራቁ። ሰውነትዎን ላላ አድርገው፡ ቀዝቃዛ ውሃ ፈልገው ትንሽ ጎንጨት ይበሉ። እርስዎ ዘንድ ያለው አይበገሬነት ሌላውም ጋር መኖሩን እንደማይዘነጉ ተስፋ አደርጋለሁ። የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለም። ጊዜው የእኛ ነው የሚለው ጋርዮሻዊ አስተሳሰብ ብዙ ርቀት አይወስድም። የህወሀት ባለሟሎች የትዕቢት ተራራ እንዴት እንደተናደ ከእርስዎ የተሰወረ አይመስለኝም። ትዕቢት የሰነፎች ጊዜያዊ ጉልበት ነው።

ቤተመንግስት የሚገኘው የለውጥ ሃይል በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ደረጃ የሚተላለፉ መልዕክቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግ ዘንድ ይጠበቃል። ዜጎችን በእኩል አይን መመልከት የሚገባቸው የመንግስት ሃላፊዎች ደምና አጥንት እየቆጠሩ ፍርድ የሚሰጡ ከሆነ ውጤቱ ለሁላችንም አይበጅም። የህወሀት መሪዎችም እኮ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ያወገዝናቸው፡ የታገልናቸው፡ እኩል ስለማያዩን ነበር። ውድቀታቸውን በጸሎትና በእልህ አስጨራሽ ትግል እንዲመጣ የናፈቅነው እኮ የበላይና የበታች መሆንን ተጠይፈን፡ አንገሽግሾን ነው።

ስሜታቸውን በማይቆጣጠሩ፡ ከሀሳብ ይልቅ ዘርና ብሄር እየጠሩ የሚሰብኩ፡ የሚፈርዱ መሪዎችን አደብ ማስገዛት የመንግስት ሃላፊነት ነው።

LEAVE A REPLY