የትግራይ ክልል ሰልፍ፤ የነጻነት ወይስ የአፈና መገለጫ? | ያሬድ ኃይለማርያም

የትግራይ ክልል ሰልፍ፤ የነጻነት ወይስ የአፈና መገለጫ? | ያሬድ ኃይለማርያም

ትላንት በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተደረገው ታላቅ ሰልፍ ባላፉት አርባ አመታት ውስጥ በደርግ እና በኢህአዴግ አዘጋጅነት ይደረጉ ከነበሩት የድጋፍ ሰልፎች በምን ይለያል? የተካሄደው ሰልፍ ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚካሄዱ ሰልፎች የነጻነት መገለጫ ወይስ ነጻ ያልወጣ ሕዝብ ጩኸት?

ባለፉት አሥርት አመታት ውስጥ በቀበሌ አስተባባሪነት ይጠሩ በነበሩ የአደባባይ ሰልፎች ላይ ሴቶች ነጠላቸውን እያጣፉ እና አንዳንዴም የክት ልብሳቸውን ለብሰው ወንዶችም እንዲሁ ሰልፋቸውን አሳምረው እና መፈክር ተሸክመው ከጓድ መንግስቱ ጋር ወደፊት እያሉ ድጋፍ ያልሰጡና እጃቸውን ወደ ላይ ያልቀሰሩ ስንት ናቸው? በወያኔም ዘመን እንዲሁ የቀበሌ ጥቅማ ጥቅም እንዳይቀርበት ልማታዊ ተሰላፊ ሆኖ አደባባዮችን ያጨናንቅ የነበረው ሰው ቁጥር ስንት ነበር? ማንበብ የማይችሉ ሰዎች ጭምር ያላነበቡትን ወይም ያልገባቸውን መፈክር ሳይቀር ተሸከመው ሰልፍ ይወጡ አልነበረም ወይ? በአንባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ የሚደረጉ የመንግስት የድጋፍ ሰልፎች የሕዝብን ዽምጽ ይወክላሉ ወይ?

የ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ እና ማግስት የታዩ ሰልፎች ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ከምርጫው በፊት ሚያዚያ አንድ ወያኔን ደግፎ የወጣውና አዲስ አበባን ያጥለቀለቀ ሰልፈኛ በማግስቱ ተቃዋሚዎችን ደግፎ ወቶ ምድር አልጠበበችውም ወይ? ከምርጫው ማግስት ደግሞ የተቃዋሚ አመራሮች ከታሰሩ በኋላ በመላ አገሪቱ ቅንጅትን ለማውገዝ፣ ወያኔ የፈጸመውን ግድያ እና ሸፍጥ ለመደበቅ በተጠራው ሰልፍ ላይ ለራሱ ለተቃዋሚው ኃይል ድምጽ የሰጠው ሰው ሳይቀር በሚሊዮኖች ወጥቶ በየከተማው ታሳሪዎቹን እና ሟቾችን አላወገዘም ወይ?

እነዚህን ጥያቄዎች እንዳነሳ ያስገደደኝ ትላንት በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎችን ተከትሎ በማህበራዊ ድህረ ገጾች እና በተለያዩ ሚዲያዎች የተንጸባረቀው የሌላው ሕዝብ ቁጣ ነው። ጋዜጠኞች፣ መሁራን እና የማህበረ ድረገጽ ተሳታፊዎች በሰልፉ ዙሪያ የሰጡትን አብዛኛዎቹን አስተያየቶች ለመከታተል ችያለሁ።

አብዛኛዎቹ የተስማሙበት እና የድጋፍ ሰልፉን የተነተኑበት መንገድ ህውሃት የፈለገው አይነት ቢሆንም ብዙዎቻችንን አስደንግጧል። ህውሃት በትላንቱ ሰልፍ ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ግልጽ ነው። የክልሉ ባለሥልጣናት ደጋግመው ሲነግሩን እንደቆዩት ሁሉ ህውሃት እና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው፤ የሚለየው የለም የሚል መልዕክት ነው። ከሌላው ሕዝብ ለትላንቱ ሰልፍ የተሰጠው ምላሽ ከሞላ ጎደል የሚያሳየው ይህ የህውሃት መሰሪ ተልዕኮ የተሳካ መሆኑን ነው።

ያዲያቆነ ሴይጣን እና ህውሃት አንድ አይነት ናቸው። አንዱ ሳያቀስ፤ ሌላውም የወየነበትን ተልዕኮ እውን ሳያደርግ እንቅልፍ የሚተኙ አይደሉም። ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት መላውን የኢትዮጵያን ግዛት እና መቶ ሚሊዮን የሚጠጋውን ሕዝብ በጥርነፋ መዋቅሩ እና ባፈረጠመው ጡንቻው ሰጥ ለጥ አድርጎ ይገዛ የነበረው ህውሃት ያንን ሁሉ ኃይሉን አሰባስቦ መቀሌ ላይ ከመሸገ ሰነባብቷል። የህውሃት አቅም የተዳከመው በመሃሉ አገር ፖለቲካ እንጂ እሱ እንደ ካምፕ በመሸገበት ትግራይ ውስጥ አይደለም።

ሕውሃት መቀሌ ሲከትም ዲሞክራት ሆነ ካላላችሁኝ በስተቀር ድርጅቱ ያንኑ የጭካኔ በትሩን እንደያዘ ትግራይን ዙሪያዋን በእሳት አጥሮ የሱ እና የሱ ብቻ ደሴት አድርጓታል። የክልሉ ባለሥልጣናት በአደባባይ እየተናገሩ ያሉትም ይህንኑ ነው። ያለ እነሱ ፈቃድ የፌደራል መንግስቱ እንኳ ወደ ክልሉ ዝር እንዳይል በደብረጺዮን በኩል ባለፈው ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስጠንቅቋል። በአፈና አደረጃጀታቸው የረቀቁት የህውኃት የደንነት ሰዎችን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ኮሽ ባለ ቁጥር እየተወነጨፈ የተገኘውን ሁሉ አናት አናቱን ይመታ የነበረው የአጋዚ ሰራዊትም እዛው ትግራይ ውስጥ መመሸጉ መዘንጋት የለበትም።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ተበታትኖ የነበረውን የህውሃት አቅም በክልሉ ውስጥ እንዲሰባሰብ እና እንዲፈረጥም አድርጎታል። ይህ የተጠናከረ የህውሃት አቅም ለጊዜው ሁለት ነገሮችን ማድረግ ያስችለዋል። አንዱ የትግራይ ሕዝብ ከመቼውም በከፋ መልኩ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከምሁር እስከ ደቂቅ አፍንጫውን ተይዞ ከህውሃት ጎን እንዲቆም ማድረግ። ሁለተኛው ደግሞ ትልቋን ኢትዮጵያ ማስተዳደር ባይችልም ማተራመስ የሚያስችል አቅም ፈጥሮለታል። የወደፊቱን እያደር እናየዋለን።

ዛሬ ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ በኤርትራ ሕዝብ እና በኢሳያስ አፎርቂ መንግስት መካከል ያለው አይነት መልክ የያዘ ይመስላል። ኤርትራ ውስጥ ኢሳያስን መቃወም አይቻልም። ምርጫው ሁለት ነው። አርፎ የግፍ እንቆቆን መጋት፤ አለያም መሰደድ። ዛሬ ትግራይ ውስጥ ህውሃት የሚነግድባቸውን የማጭበርበሪያ ካርዶች መንካት ወይም መቃወም አይቻልም። የተመዘዙት የፖለቲካ ካርዶች ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሊያጋጩ የሚችሉ እና ቅድመ ዝግጅት ተደርጎባቸው ሕዝብ አደጋ ተነጣጥሮብኛል ብሎ እንዲያስብ ተደርገው የተፈበረኩ ናቸው። በመሆኑም እዛ ላሉ ተቃዋሚዎችም ጭምር አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስላል።

ድፍን ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲያንቀጠቅጥ የነበረ ፈላጭ ቆራጭ የሆነ አንባገነናዊ እና ሙሰኛ ድርጅት በትንሿ ትግራይ ክልል ላይ ተንሰራፍቶ ጉብ ብሏል። እኛ ከዚህ ሥርዓት ለመላቀቅ 27 ዓመታት ከፈጀብን ትግራዊያንስ ወደፊት ምን ያህል ዘመን ይወስድባቸው ይሆን? ብቻቸውንስ ይህን ሥርዓት የመጋፈጥ አቅም አላቸው ወይ? የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የፌደራል መንግስቱስ ክልሉን ከዚህ ሥርዓት ነጻ ለማውጣት እና ሕዝቡም የነጻነት አየር እንዲተነፍስ ለማድረግ ኃላፊነት የለባቸውም ወይ? ወይስ የትግራይ ጉዳይ ለተጋሩዎች ብቻ የሚተው ነው?

በአንድ አገር ውስጥ፤ በተለይም በፌደራል አወቃቀር በሚመራ ሥርዓት የአንድ የክልል መንግሥት በሕዝብ ላይ ያሻውን ሲያደርግ የፌደራል መንግስቱም ሆነ ሌሎች ክልሎች ዝም ነው ወይ የሚሉት? ድርጊቱን ከማውገዝ ጀምሮ ያሉትን ሕጋዊና አስተዳደራዊ መንገዶች ተጠቅሞ የክልሉን ሕዝብ መታደግ እና ሥርዓቱንም ማረቅ አይገባም ወይ?

ብዙዎች በሃሳቤ ላይስማሙ ይችላሉ፤ ለእኔ ግን ትላንት ከትግራይ የተለያዩ ከተሞች የተሰሙት ድምጾች መልዕክታቸው በሰሉፉ ላይ በግልጽ ከታየው እና በመፈክር ከተሰማው የተለየ ነው። በሰልፉ ላይ የተንጸባረቁት የሕውሃት ድምጾች ናቸው። አንባገነኖች ሁሌም የሚናገሩት በሚገዙት፣ በሚያሰቃዩት እና ባፈኑት ሕዝብ አንደበት ነው። ሕዝብ በርሃብ እየተቆላ እድሜ ላጠገበኝ መንግስት ይላል፣ በዱላ እየተነረተ እና በሰንሰለት ተቀፍድዶም በያመቱ የነጻነት ቀን እያለ በአደባባይ እየጨፈረ ያከብራል፣ አንጀቱ ውስጥ ውስጡን እያረረ ጸሃዩ መንግስታችን ብሎ ይመርቃል፣ ከሰው ተራ ወጥቶ እና ተዋርዶ እየኖረም ለገዢዎቹ ድምጹን አውጥቶ እድሜ ሲለምን ይደመጣል።

ትላንት ከትግራይ ከተሞች የተሰሙት ድምጾች ለእኔ የድረሱልን ጩኸት ይመስለኛል። እንዲያዳቆነው ሰይጣን ህውሃትም ትልሙን ከገፋበት የትግራይ ሕዝብ እጣፈንታው ያሳስበዋል። አንዳንድ የክልሉ ምሁራንም አጥብቀው ህውሃትን እየመከሩ ያሉት ጫካ ሆኖ የተለመውን እውን እንዲያደርግ ነው። እነዚህ ምሁራን ከኤርትራ ክሽፈት ለመማር ከማንም በተሻለ እነሱ ቅርብ ነበሩ። ግን የአዕምሯቸው መደፈን ወይም በሌላ ምክንያት ይህን ሊያዩት አልቻሉም። ከዚህ እኩይ ተልዕኮ በመለስም የክልሉ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሸክሞ፣ አጎልምሶ፣ አሞስኖ እና አጠብድሎ የለቀቀውን የሃያ ሰባት አመት ጎልማሳ አንባገነን ሥርዓት ብቻውን ለመሸከም ተገዷል። ሸክሙም ገና በጊዜ አጥንቶችን እያሽመደመደው እንዳለ የትላንቱ ሰልፍ ጥሩ ማሳያ ነው። ለእኔ የድረሱልን እና የጣር ድምጽ ነው የተሰማኝ።

አሁንም የትግራይ ሕዝብ ሌቦችን ይደግፋል፣ የህውሃት ምሽግ ነው፣ ተባባሪ ነው፤ ወዘተ የሚሉት ጩኸቶች አይሰሙኝም። ይልቁንስ የሚገርመኝ 17 ዓመት ድርግን እና 27 ዓመት ወያኔን ተሸክሞ የኖረ ሰው ከሱ ባልተናነሰ፤ ምናልባትም በከፋ አፈና ውስጥ የሚገኝን ሕዝብ ሥነልቦና እንዴት መረዳት እና ህመሙን መጋራት ይቸገራል የሚለው ነው። ድህነት ሽርፍራፊ ሳንቲሚ ሲገኝ ቶሎ ሊረሳ ይችላል፤ በአፋኝ ሥርዓት ውስጥ የደረሰ ቁስል እና የሥነልቦና ጉዳት ግን እንዲህ ቶሎ የሚረሳ አይመስለኝም ነበር።

ለማንማውም በአዲስ አበባ፣ በናዝሬት፣ በባህርዳር፣ በድሬዳዋ፣ በጋንቤላ፣ በአዋሳ እና ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የፈነጠቀው የነጻነት ፀሃይ መቀሌም ላይ ፈንጥቆ ለማየት ያብቃን።

በቸር እንሰንብት!

LEAVE A REPLY