ትላንት በወሳኝ ቤተሰባዊ ጉዳይ የተነሳ የትግራይን ሰልፍ በአለፍ አገደም ነበር ሳየው የነበረው። ሰልፉ በዘጠኝ የትግራይ ከተሞች የተካሄደ መሆኑን ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን እና ከኢህአዴግ ደረ ገጽ ላይ አንብቤያለሁ። የሰልፉ አላማ ተብሎ ያነበብኩት፤ አንደኛ ”በሁሉ አካባቢ ያሉ ወንጀለኞች ይጠየቁ” ይላል፤ ይሄንን ጥያቄ ስመለከት የገባኝ አንድ ነገር የቀድሞዋ ኢሃዴግ የፕሮፖጋንዳ ስልት የሆነው ውሸትን ደጋግመህ ተናገረው እውነት ይሆናል የሚለው በትግራይ ህዝብ ላይ እንዴት እንደሰራ ነው። የህውሃት አክቲቪስቶች እና ያዙኝ ልቀቁኝ ባዮች ከጀነራል ክንፈ ዳኘው እስር በኋላ፤ አቶ ጌታቸው አሰፋም እንደማይቀርላቸው ያወቁ ግዜ ‘ይሄ ነገር በዚሁ ከቀጠለ ያለ ሌባ እና ገራፊ ልንቀር ነው’ ብለው የሰጉ ይመስል ዘመቻው ትግሬ ላይ ብቻ ነው ብለው ሌቦቻቸው ደጋግመው ሲከላከሉ ነበር። እውነቱን ባለፈው ንብረታቸው የታገደ 413 ሰዎች ዝርዝር በማየት መረዳት ይቻላል። (የብሄር ብሄረሰቦች ዝርዝር በሌቦቹ ዝርዝር ውስጥ አለ) ነገር ግን የህውሃት (የትግራይ) አክቲቪስቶች ደጋግመው ደጋግመው እስሩ ትግራይ ላይ ያነጣጠረ ነው በማለት ተርታውን ህዝብ እንዳሳመኑት እና እንዳሳሳቱት ማየት ይቻላል።
ሌላው የሰልፉ አላማ ተብሎ ያየሁት”ወንጀለኞች በፍርድ ቤት እንጂ በሌላ አካል መዳኘት የለባቸውም” የሚል ነው። ይሄ ያቺን የሜቴክ ዶክመንተሪ ፊልም ለማውገዝ ይመስለኛል። ይሄ ሃሳብ ትክክል ነው ቢባል እንኳ የመለስን ፎቶግራፍ በትልቁ ይዞ የወጣ ሰልፈኛ ይሄንን ማውገዙ አስደናቂ ይሆናል። የዶክመንተሪ ፊልም አባትን እያደነቁ ለዛውም የርሳቸው ዶክመንተሪዎች ደግሞ ቆርጦ ቀጥል እና በቅጥፈት የተሞሉ ዶክመንተሪዎች እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተጋልጠው አይተናቸዋል። ዛሬ እነ ሜቴክ ላይ የተሰራው ዶክመንተሪን ማውገዝ ህዝቡስ ህዝብ ነው አስተባባሪዎቹን ግን ትዝብት ላይ ይጥላል።
ሌላኛው በሰልፉ ላይ ተንጸባረቀ የተባለው ”የራያ ህዝብ ጥያቄ የልማት እንጂ የማንነት ጥያቄ አይደለም…” የሚል እንደሆነ አይቻለሁ። ይሄንን በሚመለከት የማንነት ጥያቄ አለን የሚሉ ሰዎች አሉ፤ እነዛን ሰዎች ማንም ተነስቶ ጥያቄያችሁ የማንነት አይደለም የልማት ነው… ጥያቄያችሁ እንትን ሳይሆን እንትን ነው… ሊልላቸው አይገባም ነውርም ነው። ለራያ የማንነት ጥያቄ መቀሌ እና አብይ አዲ ላይ ሰልፍ ወጥቶ ራያዎች የማንነት ጥያቄ የላቸውም ማለት ቀርቶ እዛው ራይዬውም ብሆን ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ ገሚሱ የማንነት ጥያቄ ሊኖረው ሌላው ደግሞ ላይኖረው ይችላል። በጅምላ ሰልፍ በመውጣት አንዱ የአንዱን ጥያቄ ማስቀየር ከቻለማ ነገ ሁላችን ወጥተን ”የትላንቱ የትግራይ ሰልፍ ጥያቄ የሌቦቻችንን እሰሩልን ጥያቄ ነው” ብለን ከሌቦቻችሁ ጋር እናቀያይማችሁ ነበር!
ሌላው በአለፍ አገደም እንዳየሁት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ተብሎ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ተሰልፈው አይቻለሁ… ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ እግዜር ይወቀው መቼም ‘ሳልሳዊ ወያኔን’ ለመፍጠር ጫካ እንገባለን እያሉ አይደለም… ያ በዚህኛው ዘመን ፈጽሞ እንደማያወጣ ይሄንን ሰልፍ የጠሩት ሰዎች ካላወቁ ምንም አያውቁም ማለት ነው!
ከዚህ በተረፈ በዚህ ሰልፍ አንድ የገባኝ ነገር፤ ይሄንን ህዝብ በስሜት ቆስቆስ አድርገህ በተለይም ጠላት አበጅተህለት ሊገሉህ ነው ሊያጠፉህ ነው ብለህ ሰበክ ሰበክ ካደረከው በቀላሉ ሆ ብሎ ይነሳልሃል። ትዕይንተ ህዝብ ግን የነገሩን ትክክልነት አያስረዳም። ”ኢየሱስ ይሰቀል በርባን ይፈታ” ይሉ የነበሩት ሰልፈኞችም በጣም ብዙ ነበሩ!
ትግራይ ሆይ አብደው የሚያሳብዱሽን አትስሚያቸው!