/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/:- በዘርፈ ብዙ የአሰራርና የሌብነት እንከኖች እየተከሰሰ የሚገኘውን ሜቴክን እንዲመሩ የተሾሙት ዶ/ር በቀለ ቡላዶ እየደረሰባቸው ባለው ከባድ ጫናና ማሥፈራሪያ ምክንያት ከኃላፊነታቸው ለቅቀዋል። ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ተክተው የሜቴክ ዳይሬክተር ሆነው የነበሩት ዶ/ር በቀለ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ያቀረቡትን የሥራ መልቀቂያ ተከትሎ ነው ተብሏል።
ዶ/ር በቀለ በሜቴክ ክስ የተጠረጠሩ ግለሠቦች መያዝ ከጀመሩ ወዲህ ከፍተኛ የሚባል ጫና እየተደረገባቸው፣ በቤተሰቦቻቸው ላይ ጭምር ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስ እንደነበር ተጠቁሟል። በምትካቸውም ምክትል ዳይሬክተሩ ብርጋዴር ጄኔራል አህመድ ሃምዛ መሾማቸው ታውቋል።
ብርጋዴል ጄኔራል አህመድ ሃምዛ ኢንሳን ከመሰረቱት መኮንኖች አንዱ ሲሆኑ ለብዙ ጊዜ የኢንሳ ሀላፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ላይዘን ኦፊስ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ም/ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል፡፡
ብርጋዴል ጄኔራል አህመድ ሃምዛ ከአምባሳደር ሱሌይማን ዴዴፎ ጋር በመሆን በቅርቡ የሜቴክን ጉድ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡