ከኢሕዲን ወዲህ ባሉት ስሞች ብዙም ደስተኛ አለመሆኔን በዚህ አጋጣሚ ብገልጽ ደስ ይለኛል፡፡ ያ ስም ደስ ይለኝ የነበረውም ሕወሓት በሰጠው የሽፋንነት ተልእኮው ሣይሆን ስያሜው ኢትዮጵያን በመያዙ ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ” ሲባል መቼም ስሜትን መኮርኮሩ አይቀርም፡፡
አሁን ባለው ስሙ ደግሞ በጭራሽ አልስማማም፡፡ አማራ ብሎ ዴሞክራሲያዊ ፣ ኦሮሞ ብሎ ዴሞክራሲያዊ፣ ከምባታና ሃዲያ ብሎ ዴሞክራሲያዊ…. የሚታሰብ አይመስለኝም፡፡ ስሙ ራሱ አጋጅ ነው፡፡ በአማራና በኦሮሞ አካባቢዎች ብዙ የሌሎች ጎሣዎች አባላት ስላሉ እነሱን የማያስተናግድ ስያሜ ዴሞክራሲያዊ ነው ብሎ መቀበል ያስቸግራል፡፡ የወቅትን የፖለቲካ ትኩሣት ለማብረድ ወይም የጊዜውን ወረት ለመከተልና የሆነ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ብቻ የሚሆን ነገር ብዙ የጎን ጉዳት አለው፡፡ ዘመኑን የዋጀ ስያሜ ቢኖር ለሁሉም መልካም በሆነ ነበር፡፡ እንደዚህ የመሰሉ አጠራሮችን በመጠየፍ ፖለቲካውን የሚሸሹ ዜጎች ብዙ መሆናቸውን ደግሞ እናስብ፡፡ እንደመግቢያ የምሰጠው አስተያየት ነው፡፡
አዴፓ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ነገሮች እየተቸገረ ያለ ይመስለኛል፡፡ መፍትሔው ምን እንደሆነ እምብዝም ባላውቅም ችግሮቹን መጠቆም ግን አይከብደኝም፡፡ ችግሮችን መረዳት ደግሞ ለመፍትሔው በብዙ ማይል እንደመቅረብ ነው፡፡
የመጀመሪያ ችግር ብዬ የምወስደው የወያኔን የጌትነትና የአዛዥነት ዘመን መርሳት አለመቻል ነው፡፡ ያ የክፉ ዘመን ተፅዕኖ በህልም ይሁን በእውን እየመጣ ይህን ድርጅት ሳያስበረግገው አልቀረም፡፡ አንድ መጥፎ ገጠመኝ (experience) በቀላሉ አይለቅም፡፡ ያቃዣል፤ ያስደነብራል፤ ችግሩ በሌለበት ሳይቀር እንዳለ እየቆጠርን ነፃነታችንን የማናምንበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ወያኔ ትግራይ ውስጥ መሽጎ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የመጨረሻ ጣር ላይ እያለ አዴፓና አንዳንድ አባላቱ ያንን ባለማመን “ሕወሓት ተነስቶ ‹እንዲህ ሊያደርገን ይችላል›” ከሚል ሥጋት ክልሉንና የክልሉን ሰላም በማደፍረስ ረገድ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ይመስሉኛል፡፡ ማሸነፍን እንዳለማመን የመሰለ መጥፎ ነገር የለም፡፡ አቅምን እንዳለማወቅ ያለ ጅል ነገርም የለም፡፡ የአዴፓንና የሕወሓትን ሁለንተናዊ አቅም ማገናዘብ ለሚችል ሰው ይህ የሰማይንና የምድርን ያህል የሚራራቅ የተመጣጥኖ ልዩነት ሲታሰብ በአዴፓ ሞኝነት ማዘን መተከዝ ሲያንስ ነው፡፡ እርግጥ ነው – ለዘመናት በሥነ ልቦና ጦርነት ሲደበደብ ከነበረ ድርጅትና አቅም እንዳይኖረው ታላቅ ዘመቻ ከተካሄደበት ውድብ ብዙ መጠበቅ አይቻል ይሆናል፡፡ በዚያ ድርጅት ውስጥ ያልተማሩና ያልነቁ፣ ከተላላኪነትና ከጉዳይ አስፈጻሚነት ባሻገር ለክልሉ ሕዝብ እንዳያስቡ በአስተሳሰብ የተሸመደመዱ… ቀትረ ቀላል “ሰዎች” በወያኔ ይመደቡ ስለነበር ለዚህ መብቃታችንም ከተዓምር የሚተናነስ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የፈጣሪ ሥራ እንጂ ከሰው አይመስልም፡፡ ያዝልቅልን ብቻ፡፡
ሌላው ችግር የክልሉን አመራር ከወያኔ ሥውርና ግልጽ አባላት ተፅዕኖ ማውጣት አለመቻሉ ነው፡፡ እንደምንሰማው ወያኔ ለብዙ ዓመታት ባሳደረው ተፅዕኖ ምክንያት አዴፓ ውስጥ አለትውልዳቸው – የጨዋታ ህጉን በመጣስ ማለቴ ነው – ሠርገው የገቡ የወያኔ አባላት – ለምሣሌ ገነት ገ/እግዚአብሔር የተባለችው – ድርጅቱን ቀይደው አዴፓ በተለይ ለአማራውና በአጠቃላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ እንዳይሠራ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ እግሩን የታሰረ ከብት እንደልቡ አይራመድም፤ እንደልቡ ሣር አይግጥም፡፡ አዴፓም እንደዚሁ በወያኔ ቅሪቶች የተተበተበ ይመስለኛል፡፡
ይህ ድርጅት ከወያኔ ተፅዕኖ ቢወጣ ተዓምር መሥራት የሚችሉ የክልሉ ተወላጆች በዓለም ዙሪያ ሞልተዋል፡፡ ዕድሉ ከተፈጠረ ከውጭም ከውስጥም ብዙ የተማረ ኃይል አለ – በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ድንቅ ተግባራትን መሥራት የሚችሉ፡፡ አሁን የተያዘው ግን የፍራቻና የጥርጣሬ ፖለቲካ በመሆኑ ማንም ሊደፍርና አስተዋፅዖውን ሊያበረክት አልቻለም፡፡ በዚህ ረገድ ሌሎች ክልሎች በተለይም ኦሮሚያና ሶማሊያን የመሳሰሉ የተሻሉ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እንደምገምተው አማራን አማርኛ ቋንቋ ራሱ ሳይጎዳው አልቀረም፡፡ አማርኛ የቻለ ሁሉ አማራ ነኝ ብሎ እየተጠጋ የራሱን አጀንዳ ስለሚያራምድ የአማራ ድርጅቶች መሪዎች ከዚህ አንጻር ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚገጥማቸው መገመት አይከብድም፡፡ አማራ ሰፊ ነው፤ አማራ አካታች ነው፤ አማራ “የኛ” እንጂ “የኔ” የሚለው ነገር የለም፤ ካለም በጣም ጥቂት ነው፡፡ ይህ ክፉኛ ጎድቶታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር እንዴት እንደሚወገድም አላውቅም፡፡ ካልታሰበበት ደግሞ አማራን እንደጎዳው ይቀጥላል፡፡
ስለዚህ አዴፓ በአስቸኳይ ራሱን እንዲያጠራ የተቻለውን ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ “የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ወያኔ እንዲመለስ ዕድል ከተሰጠው ኢትዮጵያም ሆነች አማራው አለቀለት፡፡ ቢቻል ይህን የማያዋጣ ጊዜያዊ የጨዋታ ካርድ – የጎሣ ወይም የዘር ፖለቲካ – አሽቀንጥሮ በመጣል ወደሰውነት ደረጃ መሸጋገር ለሁሉም ችግሮች ዋናው መፍትሔ በሆነ ነበር፡፡
ሦስተኛው ችግር አማራ ሆነው ሲያበቁ ለወያኔ በባንዳነት የሚያገለግሉ ዜጎች መብዛትና መንገድ እየዘጉ አላፈናፍን ማለት ነው፡፡ ይህ ችግር ከዱሮ ጀምሮ በግልጽ የሚስተዋል ነው፡፡ ገነት ዘውዴን የመሰሉ አማራንና ኢትዮጵያን ባወጡ የሸጡ ተማሩ የተባሉ አጋሰሦች ባሉባት ምድር ሌላውና ብዙም ያልተማረው ሰው ለሆዱ እየተገዛና ለፍርፋሪ ሥልጣን እያደረ ወገኑንና አገሩን ቢሸጥ ብዙም አይፈረድበትም፡፡ ጭንቅላት ተራቁቶ ሆድ በነገሠባት ኢትዮጵያ ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ያልታዘብነው ጉድ የለም፡፡ “ሆድ እንኳንስ በስተጀርባችን አልሆነ” የሚባለው ለዚህ ነው – ገፍትሮ ገደል ይከተን ነበርና፡፡ “ሆዳም ፍቅር አያውቅም” መባሉም ትክክል ነው፡፡ ሆዳም እንኳንስ ሀገርን ቤተሰቡን ይሸጣል፡፡
በመጨረሻ የማነሳው ትልቅ ችግር በአማራ ላይ ጥፋት የሠሩ የአዴፓ አባላትና ባለሥልጣናት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ አለምነው መኮንንን የመሰሉ የወያኔ ምስለኔዎችንና እንደራሴዎችን ይዞ ድርጅቱ የትም አይደርስም፡፡ አማራን የሚሳደብ ሰው ለአማራ ነፃነት ሊታገል አይችልም፤ ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ይህን ሰውዬ ቢቻል ለፍርድ ማቅረብ ያ ባይቻል ደግሞ ከድርጅት ማሰናበት ሲገባ እሹሩሩ እያሉ መለማመጥና ማባበል ወያኔን ተሸክሞ እንደመኖር ይቆጠራል፡፡ ለአብነት እነካሣ ተ/ብርሃን አማራን ወክለው ወያኔን እንዲያገለግሉ ከተደረገ ለውጡ የይምሰል እንጂ የእውነት አይሆንም፤ ብአዴን አማራ ባልሆኑ የወያኔ ምልምሎች እየተመራ አማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ምን ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ከዚህ አስቀያሚ ሂደት ገና ስላልወጣን የወቅቱ መሪር ግንዛቤያችን ነው – ልማቱና ዕድገቱ ይቅርና ማለቴ ነው፡፡ ካሣ የሚባለው ሰውዬ ባለፈው እነዶ/ር ዐቢይ ወደ አሜሪካ ሲያቀኑ መድረክ ላይ ምን ይሠራ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ያን ልዕለ-ቋንቋዊ(paralinguistic) ሁኔታውን መረዳት ያልቻለ ሰው በአንደበትም በግልጽ ቢነገረው አይገባውም፡፡ እነዐቢይ ከሕዝብ ጋር ሲወያዩና ሲተቃቀፉ እርሱ እነሱን ከመጤፍ ባለመቁጠር ስልክ ሲያወራና ሲጎረጉር እንደነበር ፊልሙን አውጥቶ ማረጋገጥ ይቻላል – ቅጭም ብሎ ማንንም ባለመፍራት፡፡ የፊት ገጽታውም የሚያስረዳው በአካል መገኘቱን እንጂ በመንፈስ ከወያኔ ጋር መቀሌ ውስጥ መመሸጉን ነበር፡፡ የለውጡ ኃይል ይህን ተራ ነገር እንኳን መገንዘብ አልቻለም – ይገርመኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው የወያኔ ተፅዕኖ (በአዴፓ በኩልና አዴፓን ተመርኩዞ) ገና ያልተነካ መሆኑን ነው፡፡ ወያኔ በህልም እንኳን እየመጣ ገና ብዙ ሳያሰቃየን አይቀርም፡፡ አሁንማ ተክሏቸው በሄደው የፖለቲካ ዕቁባቶቹና ቅምጦቹ በገሃድ እያየነው ነው፡፡ እኛም እንፈራቸዋለን፡፡ ቁስላችን አልጠገገማ!
በአማራው አካባቢም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የሚታየው የሙስና አዙሪትም ክፉኛ እየተፈታተነን ነውና ይህም መፍትሔ ይፈለግለት፡፡ ለሙስና ከሚጋልጡ ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ ለሀገር ደንታ ቢስ መሆንና ከሃይማኖት መውጣት እንዲሁም ከባህልና ወግ አውታሮች መቆራረጥ መሆናቸው ታውቆ አስፈላው የእርምት እርምጃ ይወሰድ፡፡ ይህም ሲሆን ከጳጳስ እስከ ዲያቆን፤ ከኢማም እስከ ደረሳ ድረስ ሁላችንም ጠፍተናልና ወደየኅሊናችን ተመልሰን እርስ በርስ የምንፈቃቀድበትና የምንተዛዘንበት ሁኔታ ይፈጠር፡፡ ባጭሩ “ዜጎች ከአመንዣኪ እንስሳነት ወደ አሳቢ ሰውነት የሚሸጋገሩበት ሁኔታ ይመቻች” እያልኩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚዲያዎች ሚና ቀላል አይደለምና እነሱም ተግተው ይሥሩበት፡፡
አንድ የመጨረሻ ዳላይለማዊ አጭር ትርክት ላስታውስ፡፡ የቡድሂዝም እምነት መነኮሳት ሴት መንካትም ሆነ ማነጋገር አብሮ መቆም በሃይማኖቱ አይፈቀድላቸውም፡፡ አንድ ቀን መነኮሳቱ ወደ ሩቅ ሀገር ይሄዱ ነበር፡፡ መንገዳቸው ላይ ትልቅ ወንዝ ነበረ፡፡ ወንዙ በጎርፍ ተሞልቶ አገኙት፡፡ እዚያ ወንዝ ዳር አንዲት ሴት የሚያሻግራት አጥታ ቆማ በፍርሀት እየተንቀጠቀጠች ነበር፡፡ ሁሉም መነኮሳት ህጋቸውን ፈርተው ትተዋት ሲሻገሩ አንዱ ግን አፈፍ አድርጎ ተሸክሞ ወንዙን አሻገራት፡፡ መነኮሳቱ ብዙ ከተጓዙ በኋላ አንደኛው መነኩሴ “አንተ! ህጋችንን ጥሰህ እንዴት ያቺን ሴት ትሸከማለህ” ብሎ ያሻገራትን መነኩሴ ይጠይቀዋል፡፡ እርሱም ይመልስና “አሃ! እኔ አንድ ጊዜ ተሸክሜ ነው ያሻገርኳት፡፡ አንተ ግን እስካሁን እንደተሸከምካት አለህ፡፡” ይለዋል፡፡
አዎ፣ እውነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን በትንሹ ለ27 ዓመታት ተሸክሞ ሲሰቃይ ቆዬ፡፡ አዴፓና አንዳንድ የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ግን እስካሁንም ወያኔን እንደተሸከሙ አሉ፡፡ ይህ ነገር በሚገባ ይታሰበብበት – ልጭና ጎፈሬ ሆኖ ማጌጥ የለም፡፡ አቶ ገዱና መሰሎቻቸው ካስፈለገም የዝግ ስብሰባ በማካሄድ ውስጣቸውን ሳይመሽ በጊዜ ያጥሩ – ካላጠሩና ባያጠሩ የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች እነሱ ራሳቸው ናቸው፡፡ መብላት ጀምሮ የሚተው ጅብ የለምና ሁሉም ለራሱ ሲል በወቅቱ የሚጠበቅበትን ተግባር ያከናውን – ሌላ ሌላው ይደረስበታል፤ ኅልውናህን ሊያጠፋ እበርህ ላይ ያለን ጠላት ትተህ ሥልጣንንና እህል ውኃን በመሰለ ተራ ነገር ልትጨቃጨቅ አይገባም፡፡ ወያኔ ከትግሬም ልዩ ትግሬዎችን ከዐድዋ ብቻ እየጠራች ለብቻቸው እየሰበሰበች ቁርጠኛ ውሳኔዎችን በመወሰን ነው ዓላማዋን ስታሳካ የኖረችው፡፡ ሀገርንና ሕዝብን ለማዳን ፍራቻም ሆነ ይሉኝታ አያስፈልግም፡፡ የተድበከበከ ጉዞ ለክሽፈት ይዳርጋልና በዚህ አሁን ባለው መልክ መንቀራፈፍ ስለማያዋጣ በአስቸኳይ ይቁም፡፡ እነ ብ/ጄኔራል አሣምነው ጽጌንና እነኮ/ል ደመቀ ዘውዱን በአግባቡ ተጠቀሙባቸው – ሌሎችም በብዛት አሉ፤ አስጠጓቸው – አታርቋቸው፡፡ ይህን የምታደርጉትም ለጽድቅ ሣይሆን እነሱም ከእናንተ እኩል በሀገራቸው ጉዳይ ስለሚያገባቸው ነው፡፡ እነሱን አለማመን ወይም በነሱ ሥራ ጣልቃ እየገቡ ደንቃራ መሆን ለወያኔ ትንሣኤ ከመታገል አይለይምና ሕዝቡም ወጣቱም በዚህ ረገድ ለውጡን እንደዐይኑ ብሌን ነቅቶ ይጠብቅ፡፡ የክልሉን ፀጥታ በሚመለከት ሌት ተቀን ይሠራ፡፡ ወያኔዎች በግድ እነሱ በአካል አይመጡም፡፡ በገንዘብ የሚገዙ ሆዳም አማሮችን በመጠቀም ለውጡን ሊያከሽፉ ወይም በተፈለገው ፍጥነትና አቅጣጫ እንዳይጓዝ ሊያደርጉ ይችላሉና መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ይህ ለውጥ አንዴ ከሀዲዱ ከወጣ ሁላችንም ተያይዘን ከመጥፋት በስተቀር ማንም አይተርፍም፤ አያተርፍምም፡፡
ማዕከላዊ መንግሥቱም ይህን እንዳሻቸው የሚዘባነኑበትን የገንዘብ ምንጭና የሰው ኃይል ማድረቅ አለበት፡፡ ተገቢው እርምጃ በተገቢው ወቅት ከተወሰደ ሀገራችንም እኛም እየተረጋጋን እንሄዳለን፡፡ በየጓዳው የሚሠሩትን ብር ለማስቆምም በባለሙያ የታገዘ ሥራ ይሠራ፡፡ ብርን መለወጥ አስፈላጊም ከሆነ ይለወጥ፡፡ የወያኔ ቱባ ባለሥልጣናት የብር ማተሚያ ማሽን እንዳላቸውና ለዚህም ሞራለ-ቢሶቹ ቻይናዎች እንደሚረዷቸው ይነገራልና ከዚህ ወሳኝ ሁኔታ አንጻር የለውጡ ኃይል ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል፡፡ በርግጥም በየቦታው ከሚያዘውና ገና እንደሚያዝ ከሚጠበቀው ወይም ከተደበቀው የገንዘብ መጠን አኳያ ስንገምት ይህን ያህል የብር ኖትና የገንዘብ መጠን ብሔራዊ ባንክ ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰብ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ሰዎች ለ27 ዓመታት በምን ተጠምደው እንደቆዩ አሁን አሁን እየገባን ነው – ሰውን በማሰቃየት፣ በመግደልና ገንዘብ በመሥራት፡፡ ምን ዓይነት አለመታደል ነው!
ከፍ ሲል ያልኩትን ሁሉ የምለው ለሀገራቸው ሲሉ በለውጡ ጎራ ተሰባስበው ቤተሰባቸውንና ሕይወታቸውን ጭምር አደጋ ላይ በመጣል የሚታገሉልኝን ሁሉ ከልብ በማመስገንና ጥረታቸውም እንዲሳካ በመመኘት ጭምር ነው፡፡
yinegal3@gmail.com