አንድ ጠንካራ አገር አቀፍ ፓርቲ መፍጠር ለምን አቃተን? | መሐመድ...

አንድ ጠንካራ አገር አቀፍ ፓርቲ መፍጠር ለምን አቃተን? | መሐመድ አሊ መሐመድ – ጠበቃና የህግ አማካሪ

ግን እስከመቼ ነው የጠንካራ ተቃዋሚ ያለህ የሚባለው? የሚገርመው ደግሞ ጥያቄው ዛሬም ሆነ ትናንት ጎላ ብሎ የሚቀርበው ከህዝቡ ይልቅ ከገዥው ፓርቲ መሪዎች መሆኑ ነው፡፡ ከ97 ምርጫ ቀደም ብሎ ሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ “አማራጭ ፖሊሲ ይዞ ሊቀርብ የሚችል ጠንካራ ተቃዋሚ የለም” የሚል ስሞታ ሲያቀርቡ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም መጨረሻ በአሜሪካና አገር 15 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሳተፉበት “ህብረት” ተፈጠረ ሲባል እነመለስ “እንዲህ ሰብሰብ ብለው ሲመጡ ለመነጋገርም ይቀለናል” ሲሉ ሰምተን ነበር፡፡ እነሆ ዛሬም ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድም “እባካችሁ ሰብሰብ ብላችሁ ኑ” በማለት እየተማፀኑ ነው፡፡ በርግጥ ዶ/ር አብይ ይህን የሚሉት ከፍፁም ቅንነት በመነጨና የምራቸውን ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይሁንና ተቃዋሚዎች ተሰባስበውና ተጠናክረው መውጣት አለመቻላቸው ገዥውን ፓርቲ የሚያሳስብ ጉዳይ መሆኑ አንዳች ቁጭት ሊፈጥር የሚችል ነው፡፡

በሌላ በኩል ህዝቡ ይህን ጥያቄ ገፋ አድርጎ ሊያቀርብና ተፅዕኖ ሊፈጥር አለመቻሉ ደግሞ አንዳች ግርታን ይፈጥራል፡፡ በበኩሌ በተደራጀ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በነበርኩበት ጊዜ ከህዝቡ በኩል በቀጥታ “ተባበሩ፣ ወይም ተሰባበሩ” ሲባል አልሰማሁም፡፡ ይህን ነገር የሰማሁት በፕ/ር መረራ ጉዲና አንደበት ሲነገር ነው፡፡ ለፕ/ር መረራ ህዝቡ በየትኛው መድረክ ወይም በምን መንገድ እንደነገራቸው አላውቅም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፣ ቁምነገሩ ተቃዋሚዎች አንድ ጠንካራ ህብረት/ግንባር/ውህደት መፍጠር ይችላሉ? ወይስ ከመካከላቸው አንድ ፓርቲ ነጥሮ መውጣት የሚችልበት ሁኔታ አለ? የሚለው ነው፡፡ ለመሆኑ ተቃዋሚዎች በመካከላቸው ያላቸውን ልዩነት አጥብበው ግንባር/ውህደት ለመፍጠር የማያስችላቸው ነገር ምንድነው? የእያንዳንዱ ፓርቲ መሪ “የየራሱን የተፅዕኖ ክልል ፈጥሮና (በደሴቱ) ነግሦ ከመኖር ያለፈ ህልም የለውም” የሚለውን የተለመደ ስላቅ ወደጎን በመተው መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

ለተቃዋሚዎች መበታተን በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ የሚከተሉት የአደረጃጀት ስልት ነው፡፡ የተቃዋሚዎች የአደረጃጀት ልዩነት ከስልትም ባለፈ ስትራቴጂያዊ አንደምታም እንዳለው በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ማለት የአደረጃጀት ስልታችንን መለያዬት አንድ ዓይነት አገራዊ ግብና ራዕይ እንዳይኖረን ማድረጉ አልቀረም፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች በተለያዬ ስልት ተደራጅተው ለአንድ ዓይነት አገራዊ ግብ የምንታገል ሳይሆን እርስ በርስ የምንጠላለፍና የሀገርን ጥቅምና ህልውና ሥጋት ላይ የሚጥል መሆኑ እጅግ አሳሳቢና አነጋጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም ጉዳዩን ከሥር መሠረቱ መመርመርና የመፍትሔ አቅጣጫውንም ለማመልከት መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡

በእኔ እይታ፣ አሁን በሀገራችን ያለው የፓርቲዎች አደረጃጀት የተቃኘው ከ1960ዎቹ ግራ ዘመም የፖለቲካ ፍልስፍና አንፃር ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ በዚያን ወቅት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የተቋቋሙ ፓርቲዎች የብሔር ጭቆናን የሚያቀነቅኑ፣ አሊያም ፀረ-ፊውዳልና ፀረ-ኢምፔሪያሊስት የትግል ሰንደቅን በማንሳት የመደብ ጭቆናን ለማስወገድ የተንቀሳቀሱ ነበሩ፡፡ የትግል ዓላማና ግባቸውም በወቅቱ አንፃራዊ ገዥነት ከነበረው የማርክሲስት-ሌኒኒስት ፍልስፍና አንፃር የተቃኘ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ፓርቲዎቹ የነበራቸው ግራ ዘመም የፖለቲካ አስተሳሰብ የትግልና የአደረጃጀት ስልታቸውን አንድ ሊያደርገው አልቻለም፡፡

ስለሆነም የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ ባህል በሆነባት ሀገራችን ሁለት ፅንፈኛ አስተሳሰቦችና የአደረጃጀት ስልቶች ጎልተው ወጥተዋል፡፡ እነዚህም ብሔር-ተኮርና (ethnic based) አገር አቀፍ (national) ተብለው ሊመደቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከንድፈ-ሀሳብ ትንተናዎቻቸውና ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው መረዳት እንደሚቻለው የሁለቱም አስተሳሰብ አራማጆች (አብዛኞቹ) በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ስትራቴጂያዊ ልዩነት ያላቸው አይመስልም፡፡ አንደኛው አብይ ጉዳይ (በተለይ አሁን ላይ) የሁሉም ወገኖች የመጨረሻ ግብ የኢትዮጵያን አንድነት ማረጋገጥ/ማጠናከር መሆኑን ማመላከታቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ቁም ነገር የኢትዮጵያ ቅርፀ-መንግሥት ፌዴራላዊ መሆን እንዳለበት ተመሳሳይ ግንዛቤና አቋም መውሰዳቸው ነው፡፡ በነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ ግብ ያላቸው ቢመስልም የኢትዮጵያን አንድነት ይበልጥ ሊያጠናክር የሚችለው የትኛው የፓርቲ አደረጃጀትና የፌደራል አወቃቀር ሞዴል ነው; በሚለው ጥያቄ ላይ ያላቸውን ልዩነት ማጥበብ አልቻሉም፡፡ ይህ ልዩነት ጎልቶ የሚታየው በገዥውና ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚው ጎራ ውስጥም ጭምር ነው፡፡

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሁሉ፣ ከፓርቲ አደረጃጀትና፣ ብሎም ከፌዴራል አወቃቀር ጋር በተያያዘ ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት መነሻ/ምንጭ ከታሪካዊ ዳራ ምልከታ ጋር አያይዘው ያዩታል፡፡ በኢትዮጵያ በንጉሳዊ ምዕክልና ዘመን የነበረውን የጭቆና ባህሪ በሚመለከት ሁለት ዓይነት የታሪክ ግንዛቤና ምልከታዎች እንደሚንፀባረቁ ይታወቃል፡፡ አንደኛው ወገን በኢትዮጵያ የብሔር ጭቆና እንደነበር ሲያምን ሌላው ወገን ደግሞ አጠቃላይ የመደብ ጭቆና እንጅ በየትኛውም ብሔር ላይ ያነጣጠረና የተለየ ጭቆና አልነበረም የሚል ክርክር ያቀርባል፡፡ ይህ የታሪክ ምልከታና ግንዛቤ በችግሩ አፈታትና ችግሩን ለመፍታትም ሊኖር በሚገባው የአደረጃጀት ስልት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖና ልዩነት ፈጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ የብሔር ጭቆና እንደነበር የሚያምኑት ወገኖች የኢትዮጵያን አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት የብሔር-ተኮር አደረጃጀትን አስፈላጊነት ሲያሰምሩበት የነበረው ጭቆና መደባዊ ባህሪ እንደነበረው የሚገነዘቡት ወገኖች ደግሞ ሕብረ-ብሔራዊ አደረጃጀትን ተመራጭ ስልት አድርገው ያቀርባሉ፡፡

ሕብረ-ብሔር የአደረጃጀት ስልትን የሚከተሉ ወገኖች፣ ብሔር ተኮር (ethnic based) አደራጃጀት በብሔረሰቦች መካከል አጉል ፉክክር፣ መቃቃር፣ ፍጥጫና ግጭትን በመፍጠር ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን (Ethiopian nationalism) በማዳከም የሀገርን አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በነዚህ ወገኖች እይታ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ እምነትቶችና እሴቶች ያሏቸው ብሔሮች/ብሔረሰቦች ቢኖሩም፣ በአንድነት እንዲሰለፉ ግድ የሚሏቸው በርካታ የጋራ ጉዳዮች አሏቸው፡፡ ልዩነቶቻቸው አንደተጠበቁ ሆነው ለአንድ አገራዊ ዓላማና ግብ እንዳይሰለፉ የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ ከዚህ መሠረታዊ እምነት በመነሳት ሕብረ-ብሔራዊ የአደረጃጀት ስልትን የተሻለ አማራጭ አድርገው ያቀርባሉ፡፡

ይሁንና ካለፈ ታሪካችን በመነሳት ህብረ-ብሔራዊ የአደረጃጀት ስልትን የጠቅላይ/አግላይ አስተሳሰብ ቅጥያ አድርገው የሚያቀርቡ ወገኖች በሀገራችን እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ ሥልጣን የሚያዘው የዘር ግንድ ተቆጥሮ እንደነበር ይተርካሉ፡፡ በርግጥ በነገሥታቱ ዘመን፣ በተለይ በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ ሰለሞናዊ የዘር ሐረግ ካልተመዘዘ በስተቀር ሥልጣን የሚረጋ የማይመስላቸው ወገኖች እንደነበሩ አይካድም፡፡ የ1966ቱ አብዮት በዚህ አስተሳሰብ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ቢመስልም በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመነ-መንግሥት አስተሳሰቡ መልኩን ቀይሮ ትንሳኤውን አብስሯል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘመን፣ ሁሉም ብሔሮች/ብሔረሰቦች በመንግሥት የሥልጣን መዋቅር (power structure) ውስጥ ተመጣጣኝ ድርሻና ሚና ሊኖራቸው ባለመቻሉ የፓለቲካ አደረጃጀት ስልትና ትግሉ ቀጣዩን ባለተራ ማዬት በሚቻልበት መነፅር የተቃኘ ሆኗል፡፡

ህወሓትን ማዕከል ያደረገው ሥርዓት በተለይ #ነፍጠኛ$ በሚለው ወገን ላይ ያለው አተያይና ትንተና በሌሎች ወገኖች የፖለቲካ አረዳድና አስተሳሰብ ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ገና ወደ ጫካ ሲገባ #ነፍጠኛ$ ¾T>K¨<” ¨Ñ” “መልሶ ማንሰራራት በማይችልበት ሁኔታ አከርካሪውን መስበር” የሚል “ፀረ-ህዝብ” ዓላማ ያነገበው ህወሓት በበላይነት የተቆጣጠረውን የመንግሥት ሥልጣን በመጠቀም ሌሎች ወገኖችም በፀረ “ነፍጠኛ$ ትግሉ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ሕብረ-ብሔራዊ የአደረጃጀት አማራጭ በጥርጣሬና በሥጋት እንዲታይ አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋቋ ነን የሚሉ ወገኖችም “ኢትዮጵያዊነት ከእኛ ወዲያ ላሳር” በሚል የሚያሳዩት አጉል መታበይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠረ መሆኑም አይካድም፡፡ ይህን የአመለካከት ችግር ሰብሮ መውጣት ራሱን የቻለ ትግል የሚጠይቅ ሲሆን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ማንም የተለየ/የተሻለ ተቆርቋሪነትና ጥቅም (special vested interest) ሊኖረው የሚችልበት አመንክንዮ (logic) ሊኖር እንደማይችል መተማመን ካልተቻለ እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲን መፍጠር በቀላሉ የሚቻል አይሆንም፡፡ በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎችም ልዩነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው የኢትዮጵያ ጉዳይ እኩል እንደሚመለከተውና እንደሚያገባው የምር አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው፣ ጉራጌው፣ ሶማሌው፣ አፋሩ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ሲዳማውና ሌላውም እንዲሁም ክርስቲያኑ፣ ሙስሊሙ … ወዘተ ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ በእኩልነት እንደሚታይና እኩል እንደሆነ ሊሰማው ይገባል፡፡

በአንፃሩ ሕብረ-ብሔራዊ ስያሜ ያላቸው ፓርቲዎ በተወሰኑ ወገኖች ብቻ የሚዘወሩ ከሆነ ሥርዓቱ የፈጠረውን ጥርጣሬና ሥጋት ይበልጥ ሊያጎላው እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡ በርግጥ በሕብረ-ብሔራዊ አደረጃጀት ዙሪያ አሉታዊ አስተሳሰብ በነገሰበት ዘመን ሌሎችን በቀላሉ አሳምኖ በቀላሉ ማቀፍና ማሳተፍ የሚቻልበት ዕድል እጅግ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ፣ በዚህ ረገድ (የአንድ አካባቢ ሰዎች የተሰባሰቡበት ተብሎ) ሲታማ የነበረው መኢአድ በ97 ምርጫ ዋዜማ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በትግራይ አካባቢዎች ህዝብን በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ያሳየውን አንፃራዊ ስኬት ከላይ የቀረበውን ክርክር ውድቅ ለማድረግ እንደአብነት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን፣ በተጠቀሱት አካባቢዎች የተደረገው እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወገኖችን፣ በተለይም የፖለቲካ ልሂቃንን (poltical elites) ያቀፈና ያሳተፈ ነበር ለማለት አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ ፓርቲዎች ከአንዳንድ ብሔረሰቦች/የቋንቋ ማህበረሰቦች የወጡ ታዋቂ ሰዎችን በማምጣት በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለማስቀመጥ ቢሞክሩም ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ አብነቶችን ጠቅሶ መናገር ይቻላል፡፡ ምናልባትም ለኢትዮጵያ አንድነት ቀናኢ ከመሆን በመነጨ ሕብረ-ብሔራዊ ስያሜ የያዙ ፓርቲዎች አደረጃጀታቸው ከጅምሩ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ባለመሆኑ ኢትዮጵውያንን ዳር እስከዳር ማንቀሳቀስና ተፈላጊውን ግብ ማሳካት እንዳልቻሉ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ለማደራጀት ሲታሰብ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎትና ጥቅም ሊወክሉ የሚችሉ ሰዎችን ማሳተፍና በሁሉም ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አያከራክርም፡፡

በርግጥ፣ አሁን በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተለያዬ የብሔርና የእምነት ማንነት ያላቸውን ሰዎች በቀላሉ ተማምነው ለጋራ ዓላማ መሰለፍ የሚችሉበት መንገድ ጠባብና አስቸጋሪ መሆኑ ከላይም ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው/ችግሮቻቸው ዙሪያ ተግባብተውና ተማምነው ለጋራ ጥቅሞቻቸው መሰለፍ የማይችሉ ከሆነ የሕብረ-ብሔራዊ አደረጃጀት ፋይዳ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ ይህም ሆኖ በተሸናፊነት መንፈስ ወደ ብሔር-ተኮር አደረጃጀት የመንደርደርን ቀላል አማራጭ መውሰድ እንደ ትግል የሚታይ ሳይሆን ከፋፋዮች በቀደዱት ቦይ መፍሰስና የእነሱን ዓላማ ማሳካትና ራዕያቸውን በቀላሉ ዕውን ለማድረግ እንደመተባበር የሚቆጥር ነው፡፡ ይልቁንም ትግሉ ሊሆን የሚገባው፣ ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት፣ የጋራ አጀንዳና ራዕይ በመቅረፅ፣ ሊሳኩ የሚችሉ አገራዊ ግቦችን በማስቀመጥ ምልዓተ-ህዝቡን በአንድነት ማንቀሳቀስ መቻል ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊነት ፍፁም ቀናኢ በመሆንና ሁሉንም ወገን ሊያሰባስቡ የሚችሉ አጀንዳዎችን መቅረፅ እስከተቻለ ድረስ እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ መፍጠርና ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር ማንቀሳቀስ የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በዚህ መንገድ ሀገራዊ አንድነትና የጋራ ህልማችንን እውን ማድረግ እንደምንችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

እንደመውጫ፣

ከላይ የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአደረጃጀት ስልት በመለስ አንድ ጠንካራ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመፍጠር እንቅፋት የሆኑብን ወይም ውስንነቶቻችን (constraints & limitations) ምንድናቸው? በትግላችን ማሳካት የምንፈልጋቸው አገራዊ ግቦች ምንድናቸው? እንዴት ሊሳኩ ይችላሉ? የእኛ የአደረጃጀት ስልትና ድርጅታዊ አቅምስ ያስቀመጥናቸውን አገራዊ ግቦች ማሳካት የሚያስችል ነው ወይ? ሊያጋጥሙን የሚችሉ ችግሮችንስ ለይተንና ዘርዝረን እናውቃቸዋለን ወይ? አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታውና የኃይል አሰላለፉስ ምን ይመስላል? በዚህ ውስጥ የእኛ ቦታና የትግል ስትራቴጂ ምንድነው? በነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሌላ ጊዜ የምንቆዝም ይሆናል፡፡

LEAVE A REPLY