/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/:- ይህ የተገለፀው የሶማሊያ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ ሀገሪቱን ከኤርትራና ኢትዮጵያ ጋር ለማዋሀድ ድብቅ ስምምነት ፈፅመዋል ሲሉ ባቀረቡት ክስ ነው።
አንድ መቶ የሚደርሱ የሶማሊያ ፓርላማ አባላት ፕሬዝዳንቱ ከሃገሪቱ ሕገ መንግሥት በተቃራኒ ከአካባቢው ሃገራት ጋር ስምምነት ፈጥረዋል ፤ በተለይም ሶማሊያን ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር ለማዋሃድ ምስጢራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል ሲሉ ክስ አስገብተዋል ። ይህንንም ተከትሎ በተባበሩት መንግስታት በሚደገፈው የሶማሊያ መንግሥት ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ተፈጥሯል።
በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሃገራቱ መካከል የነበረውን በጠላትነት የመፈራረጅ ሁኔታ ባልተለመደ መልኩ በአጭር ጊዜ በማስወገድ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች ወዳጅነታቸውን በማጠናከር ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጋቸው ይታወቃል። ከባህረ ሠላጤው ሀገሮች፤ በተለይም ከሳዑዲና ቃታር የፖለቲካ ውዝግብ ጋር በተያያዘ መሪዎቹ ከሳዑዲና ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር የፈጠሩት ግንኙነት ከሳሽ የፓርላማው አባላትን ሳያስከፋቸው እንዳልቀረም አንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች እየገለፁ ይገኛሉ።
እኚሁ ጥያቄ ያቀረቡ የህዝብ ተወካዮች፤ ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያ ጋር በወደብ አጠቃቀምና በንግድ ግንኙነት ዙሪያም አግባብ የሌለው ስምምነት አድርገዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል ። ይህንን የፓርላማ አባላት ጥያቄ አፈ ጉባዔው ቢቀበሉትም ለፓርላማው ውይይትና ውሳኔ ይቀርብ እነደሆነ ግን የታወቀ ነገር የለም።
ቀደም ያሉት የሶማሊያ አስተዳደሮች በፕሬዝዳንቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል በሚፈጠሩ ያለመግባባቶች ሲታወኩ የከረሙ ቢሆኑም አብዱላሂ ፋርማጆ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ግን ሶማሊያ አንፃራዊ ፖለቲካዊ መረጋጋትን አግኝታ መቆየቷ ይታወቃል።
አንዳንድ አስተያየት ሰጨዎች የአብይ መንግስትን አቅም ለማሳጣት የሚንቀሳቀሰው የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የብሔር ግጨት በመቀስቀስ ሁከት በማበራከት ያደረገው ውስጣዊ እንቅስቃሴ ሲከሽፍ በጎረቤት ሀገራት የጀምረው ውዝግብ ውጤት ነው: ይላሉ::