ጉዳዩ፤ እውቅ ኢትዮጵያዊያንን እናመስግን፤
ወድ ወገኖቸ:-
የዛሬው ደብዳቤ የምስጋና እናቅርብ ጥሪ ነው። ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ለደግና ለሐቀኛ ሰዎች ማቅረብ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ወግ ማዕረጋችንም ነው። በውጭው ዓለም ምስጋና (thank you) ለመልካም ድርጊት የሚቀርብ የስብዕና መወድስና የማህበራዊ ግንኙነት ማጠናከሪያ ድልድይ ነው። በምስጋና ለሰዎች እርካታና ሀሴትን፤ ለተግባራቸው እውቅናን ያጎናጽፋል።
ስለእውነት እንደ ኢትዮጵያውያን በብዛት ምስጋና የሚያቀርብ ሕዝብ የለም። ምስጋናችንም ከሌሎች የተለየ ባህሪና ይዘት አለው። የእኛ ምስጋና ደረቅ ቃላትን የተላበሰ ብቻ ሳይሆን ምርቃን በፈሪሃ እግዚአብሔር ታጅቦ የሚሰጥ መልካም ስነምግባራችን ሆኖ ለብዙ ሽህ ዘመን በውስጣችን ያለና አብሮን የዘለቀ መገለጫችን ነው።
ውድ ወገኖቸ፤ እንደምታውቁት ሕይወት በመኖርና ባለመኖር መካከል የሚደረግ የሰዎች የመኖር ትግል ውጤት ነው። ሰዎች “የእኛ” በሚሉት አካባቢ በዘልማድ ሃገር ብለው በሚጠሩት ግዑዝ ቦታ ላይ ሰፍረው እስካሉ ድረስ የተደራጀ ማህበረሰባዊ ሕይወት ይኖራሉ። ሃገር ያለህዝብ ሕዝብም ያለሃገር ትርጉም አልባ ናቸው የሚባለውም ለዚህ ነው። ሕዝቦች የተፈጥሮ ሃብታቸውን በጋራ ተጋግዘው፤ ተደራጅተውና ተደጋግፈው ሃገራችን ብለው የሰየሙትን ምድር ይጠቀሙበታል፤ ያስተዳድሩታል፤ ይንከባከብታል። ለአኗኗርና ለአጠቃቀም ያመች ዘንድ ከመሃላቸው መሪና አስተዳዳሪ መርጠው በስርዓት አስተዳዳሪዎችንና መሪዎችን ይሰይማሉ። የራሱን መሪና አስተዳዳሪ መምረጥ የማይችል ማህበረሰብ ደግሞ የተፈጥሮ መብቱን በጉልበተኞች ተነጥቆ ሲሰቃይ ይኖራል።
እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ እኛ ኢትዮጵያውያን ሕይወታችንንና ኑሮአችንን በሰላም፤ በፍቅርና በጤና መግፋት እንወዳለን። ሕይወታችንን በሰመረና በሰከነ መልኩ ለማካሄድ ደፋ ቀና በምንልበት ጊዜ ደግና ክፉ፤ መከራና ደስታ፤ መውደቅና መነሳት፤ ቀውስ፤ ሞት፤ መከራና ሃዘን እየተፈራረቁ ተፈታትነውናል፤ አስጨንቀውናል። ሕዝብ ሲጨነቅ ደግሞ አገር አደጋ ላይ ይወድቃል። በሃገርና በሕዝብ ላይ የሚከሰት አደጋም በተፈጥሮ ወይ በሰው ሰራሽ ምክንያት ይከሰታል። ራስንና ሃገርን ከአደጋ ለመከላከል የቅድሚያ ዝግጅት እናደርጋለን። ዝናብ፤ ብርድ፤ ፀሐይ፤ ርሃብ፤ ወዘተ እንዳያጠቁን ቤት ሰርተን፤ አልባሳት ፈብርከን፤ ምግብ አምርተን፤ መልካም መስተዳደር አቋቁመን አደጋን እንከላከላለን። በሕዝብና በሃገር ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጥፋት መጠን ለመቀነስ ጥረት እናደርጋለን።
ሕዝብና ሃገር የሚያስተዳድር ሁሉ ዋና ዓላማው ሃገርን ከተፈጥሮና ከሰው ሰራሽ አደጋ መታደግ ተቀዳሚ ተግባሩ መሆን የሚገባውም ለዚህ ነው። መስተዳድሩ ይህን በተግባር ለመፈጸም በሚታገልበት ጊዜ ብዙ መውደቅና መነሳት፤ ክሽፈትና ውርደት ይገጥሙታል። በሐቅ፤ በታማኝነት አገርና ሕዝብን ለማገልገል የቆረጠ መስተዳድር በሕዝብ የተወደሰ፤ በዓለም የተከበረና የተደነቀ ይሆናል።
የቅርቡን ሰባ ዓመታት ስናይ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ አገዛዞችና መስተዳድሮች ተፈራርቀዋል። በነገስታት፤ በወታደርና በሽፍቶች ተገዝተናል። በዚህ ጊዜ በጎም መጥፎም ሁኔታዎች ደርሰዋል። እንደ ሕዝብ ብዙ የግፍ፤ የሰቆቃና የጭቆና አገዛዝ ዘመኖችን አስተናግደናል። በመጥፎ ገዢዎችና አስተዳዳሪዎች ምክንያት ሃገርና ሕዝብ ለጥፋትና ለመፍረስ ጫፍ የደረሱበት ወቅት እንደነበር እናውቃለን። ይሁንና በጨቋኝና ዘራፊ ስርዓቶች ውስጥ ብዙ ደግና ጠንካራ ግለሰቦች አይተናል። እነዚህ መልካም ሰዎች ግን ከብልሹ አስተዳደር ጋር በመስራታቸው ብቻ በጅምላ ተወቅሰዋል፤ ተወግዘዋል፤ ተፈርጀው ተወግረዋል። “ለኃጥአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል” ይሏል ይህ ነው። ኢትዮጵያውያን ከዚህ አስተሳሰብና የጅምላ ፍረጃ ወጥተን ስንዴውን ከገለባው ለይተን ለማውጣት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በብልሹ አስተዳድር ውስጥ ለሕዝብና ለሀቅ የቆሙ ሰዎች ነበሩን፤ አሉንም። እነዚህ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ ግፍና ዘረፋው ከምንገምተው በባሰ ሁኔታ ይሆን እንደነበር መረዳት ይኖርብናል። ለሃገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች በመኖራቸው ኢትዮጵያ ከጨቋኞች፤ ከግፈኞች፤ ከዘራፊዎች ተርፋ ከትውልድ ወደ ትውልድ ስትተላለፍ ቆይታ ለእኛ የመድረሷ ምስጢርም ይህ ነው።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ብዙ በጎ ነገሮች የተሰሩ ቢሆንም ብዙ ጭቆና፤ ብዙ ጢሰኛና ገባር ነበር። የጥፋቱ ደረጃና መጠን መረን እንዳይለቅ በአገዛዙ ውስጥ ሆነው የመከላከልና ጥፋቱን የመቀነስ ስራ የፈጸሙ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ ሃገሪቱ ለክፋ አደጋ ትጋለጥ ነበር። ለምሳሌ አክሊሉ ሃብተወልድን የመሰለ አስተዋይ ዲፕሎማት፤ ጄንራል ጃጋ ማኬሎንና ጄንራል መንግስቱ ነዋይን የመሰሉ የጦር መሪዎች እና አቶ ግርማሜ ነዋይን የመሰለ አስተዋይ አስተዳዳሪና መሪ፤ አቡነ ጴጥሮስን የመሰለ የሃይማኖት አባት በመኖራቸው ኢትዮጵያና ሕዝቧ ከብዙ ጥፋት ሊተርፉ ችለዋል። እነዚህን ብርቅ ኢትዮጵያዊያን ደግመን ደጋግመን ልናመሰግናቸው ይገባል።
በደርግ ዘመን ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፤ ግድያና አፈና፤ የአስተዳደር ብልሹነት ለ17 ዓመታት ተካሂዷል። ግልጽ የሆነ ዘረኝነት፤ አድላዊነት፤ ዘረፋና ሙሰኝነት ባይኖርም አስተዳደሩግፍና ጭቆናን አስተናግዷል። በዚህ የተነሳ ደርግንና ርዕዮተዓለሙን በጅምላ ተቃውመናል። ግን በደርግ ውስጥ ተሰግስገው ይሰሩ የነበሩ ለሃገርና ለህዝብ የሰሩ፤ መልካም ስነምግባር የተላበሱ ሐቀኛ የጦር መኮንኖች፤ ምሁራን፤ ዲፕሎማቶችና ፖለቲከኞች ነበሩ። እነዚህ መልካም ሰዎች ውስጥ ውስጡን ባደረጉት ጥበብ የተላበሰ ተቃውሞና መከላከል በማድረጋቸው ሃገሪቱን ከባሰ ጥፋት ታድገዋታል። ኮለኔል አጥናፉ አባተ፤ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ፤ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊወርጊስና ጄነራል አማን አምዶምን የመሳሰሉ መኮንኖች እስከ ሕይወት መስዋእትነት ያደረሰ ተቃውሞና ምክር ለመንግስታቸው ሲሰጡ እንደነበር ይታወቃል። በሲቭል አመራሩም እንደ ተስፋየ ዲንቃንና ተኮላ ደጀኔን የመሳሰሉ ለእውነት፤ ለሃገርና ለሕዝብ ጎን በመቆማቸው ሃገሪቱን ከብዙ ጥፋት ታድገዋታል። እነዚህን ብርቅ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ልናመሰግናቸው ይገባል።
ከላይ ከተጠቅሱት መንግሥታት በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ እጅግ አስከፊ የሆነ መስተዳድር የታየው ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ነው። መመሪያና ሕገ መንግስት ቀርጾ ኢትዮጵያን ከምድረገጽ ሊያጠፋ የተነሳ እንደ ህወሃት/ኢሕአዴግ ያለ የሽፍታ መንግስት በታሪክ ታይቶ አይታወቅም። በረዥሙ የፊውዳልና የአምባገነን አገዛዝ ታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ፤ በታሪክ ያልተሰማና ሊናገሩትም የሚከብድ ከሕዝባችን እምነትና ባህል ውጪ የሆነ የአፈናና የግድያ መዋቅር ዘርግቶ፤ በንጹሃን ዜጎች ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት የፈጽም፣ ሴቶችን የደፍር፣ ጥፍር ያስነቅል፣ ብልትና ጡት የሰለበ፣ በጎሳና በሃይማኖት ሕዝብ ያፋጀ፣ የገንዛ ሃገሩን መሬት ቆርሶ ለባዕድ የሰጠ፣ የመንግስትና የህዝብ ሃብትና ንብረት እየዘረፈ ባህር ማዶ የደበቀና ያሸሽ መንግስት ኖሯት አያውቅም። ወደፊትም የዚህ ዓይነት ወሮበላ መንግሥት ይገጥማታል ተብሎ አይታሰብም።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ነውረኛው መንግሥት የባሰ ሰቆቃና ግፍ እንዳይፈጽም በአስተዳደሩ ውስጥ ሆነው ከፍተኛ ስራ የሰሩ ሃገርና ህዝብ ወዳድ የሆኑ ብዙ ባለስልጣናት፣ አስተዳዳሪዎች፣ የጦር መኮንኖችና ዲፕሎማቶች መኖራቸውን ስናውቅ ደስታ ይሰማናል። በሰራዊቱ ውስጥ የነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን፣ ጀነራል ሰዓረ መኮንን፣ ጀነራል አሳምነው፤ በሲቭል አስተዳደሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ ገዱ አንደርጋቸው፣ አቶ ደመቀና ዶ/ር ዓምባቸው፣ እት ኤርምያስ ለገሰ ፣ ወዘተ የመሰሉ በእሳትና በረመጥ ውስጥ ሆነው ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ክብርና አንድነት የታገሉ እናገኛለን።
በዲፕሎማሲው ዓለም እንደ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎን የመሰሉ ሐቀኛ፤ ደፋር፤ ቆራጥና አገር ወዳዶችን አይተናል። እኒህ ሰው በስልጣን ላይ እያሉ የሕውሃት/ኢህአዴግን፤ የተቀናጀ ሃገርና ሕዝብ የመዝረፍ ሴራና ጸያፍ ተግባር በኦፊሴልና በህቡዕ የታገሉ ሐቀኛ የኢትዮጵያ አርበኛ ናቸው። አምባሳደር ሱሌማንን የመሰለ ሰው በአገዛዙ ውስጥ በመኖሩ ኢትዮጵያችን እንደ ሶማሊያ፤ ርዋንዳና ሶርያ ከመሆን አትርፈዋታል። ምስጋና ይግባቸውና በትግላቸውና በሐቀኝነታቸው ኢትዮጵያን አቆይተውናል። ስለሆነም ለአምባሳደር ሱሌማን ሁላችንም ላቅያለ ልባዊ ምስጋና ልናቀርብላቸው ይገባል። እረዥም ዕድሜ ከሙሉ ጤና ጋር እንዲሰጣቸው ፈጣሪን እንለምነዋለን።
ነን ሶቤ
ታህሳስ 12, 2018