“ትግርኛ ተናጋሪዎች” ሲባል | መሐመድ አሊ መሐመድ

“ትግርኛ ተናጋሪዎች” ሲባል | መሐመድ አሊ መሐመድ

ይህ እንዴት አነጋጋሪ ሊሆን ይችላል? ባለፉት 27 ዓመታት ሥርዓቱ በትግርኛ ተናጋሪዎች ተፅዕኖ ሥር አልነበረም እንዴ? በየመ/ቤቱ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች የተያዙት በማን ነበር? የአንድ መ/ቤት ኃላፊ የሌላ ብሔር አባል ቢሆንኳ ምክትሉ ሆኖ ወይም ከሥሩ የሚመደብለት ማን ነበር? በመምሪያ ኃላፊዎች የሚታዘዙና የሚገመገሙ ሚኒስትሮች አልነበሩም እንዴ?

እስከ ቅርብ ጊዜ ከመከላከያ ባለሥልጣናት (ጀነራሎችና ኮሎኔሎች) ውስጥ የሌላ ብሔር ተወላጆች ድርሻ ምን ያህል ነበር? ቁልፍ የኃላፊነት/የአዛዥነት ቦታዎች ላይ የነበሩት እነማን ነበሩ? በፌዴራል ፖሊስ መዋቅር ውስጥ የነበረው ስብጥር ምን ይመስል ነበር? በተለይ የደህንነት መ/ቤቱን የወረሩትና የተቆጣጠሩት እነማን ነበሩ? ለመሆኑ በነዚህ የፀጥታና ደህንነት ቁልፍ መዋቅሮች ውስጥ ለመመደብ ሥርዓቱ በሌሎች ላይ እምነት ነበረው?

በዚያ ዘመን ትግርኛ ተናጋሪ ሆኖ መገኘት የሚያኮራና በሌሎችም ዘንድ የሚያስፈራ አልነበረም እንዴ? ትግርኛ ተናጋሪ መሆን ከራስ አልፎ ለተጠጋው ሁሉ ጥላ-ከለላ መሆን የሚያስችል አልነበረም እንዴ? ትግርኛ ተናጋሪ የሆነ ሰው በመንግሥት መ/ቤቶች ውስጥ ገብቶ ማስፈፀም የማይችለው ጉዳይ ነበር እንዴ? በመኖሪያ ሰፈሮችና በሥራ ቦታዎች ትግርኛ ተናጋሪዎችን የማይፈራና ለእነሱ የማይሽቆጠቆጥ ነበርንዴ? ያኔ በብሔር ትግሬ ሆኖ መገኘት የልብ የሚያናግር አልነበረም እንዴ? በሆነ አጋጣሚ ትግርኛ ቋንቋ መናገር የቻሉ የሌሎች ብሔሮች አባላት ሳይቀር ከዋናዎቹ ብሰው ትግሬ መስለው/ሆነው ለመታዬት ሲወጣጠሩ አልነበረም እንዴ?

ዛሬ “ትግርኛ ተናጋሪዎች” መባሉ እንዴት አነጋጋሪ ሊሆን ቻለ? ያኔ ሥልጣኑንም; ሀብቱንም. .. ሲያግበሰብሱ “ትግርኛ ተናጋሪ” መባላቸውን በፀጋና በኩራት አልተቀበሉትም ነበር እንዴ? ሌላው ወገን ስለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተመጣጣኝ ዕድገት ሲጮህ ጆሯቸው ይሰማ ነበር? ያኔ በመከላከያና ደህንነት መ/ቤቶች ውስጥ የነበረው የኃላፊዎችና የአዛዦች ቁጥር ሊመጣጠን እንደሚገባ ሲጠየቅ ሌሎችን አፍ ለማስያዝ ሲረባረቡ አልነበረም እንዴ? ያኔ የትግርኛ ተናጋሪዎች ቁጥር በዛ ሲባል “ሥርዓቱ ህይወትና ደም የገበርንበት ስለሆነ ይገባናል” ብለው ደረታቸውን ነፍተው በኩራትና በድፍረት አልተሟገቱም እንዴ? ዛሬ “ትግርኛ ተናጋሪዎች” መባሉ ለምን ጥቃት መስሎ ታያቸው?

ደግሞስ “ትግርኛ ተናጋሪዎች” መባሉ እንዴት ነው በትግራይ ህዝብ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ተደርጎ የሚታዬው? በሥርዓቱ ውስጥ ቀጥታ ተሳታፊና ልዩ ተጠቃሚ የነበሩት ቁጥራቸው ከመቶ ሺህዎች ያልፋል እንዴ? ከነዚህስ ውስጥ ለሀገር የሚቆረቆሩና ሰብኣዊ ርህራሄ የሚሰማቸው አልነበሩም እንዴ? አሁንስ ቢሆን በሥርዓቱ ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ የነበረው ሁሉ በተጠርጣሪነት የእስር ማዘዣና ማደኛ ወጥቶበታል እንዴ? ጠቅላይ ሚ/ሩ “ይህን ሁሉ በህግ ተጠያቂ እናድርግ ቢባል ማረሚያ ቤት ይቅርና ከተማ ብንገነባም አይበቃንም” ሲሉ አልሰማናቸውም እንዴ?

ስለሆነም ይጠየቃሉ የተባለው እጅግ ያገጠጠ የሙስናና የሰብኣዊ መብት ጥሰት ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩት አይደሉም እንዴ? እነዚህ በቁጥር ስንት ይሆናሉ? እነሱ ጥቂቶቹ ሰፊውን የትግራይ ህዝብ ናቸው እንዴ? ወይስ የትግራይ ህዝብ በሥሜ ሀገር ዝረፉ/መዝብሩ; በወገን ላይ ይህን ሁሉ ጭካኔ የተሞላበት; አረመኔያዊና ዘግናኝ ግፍና በደል ፈፅሙ ብሎ ወክሏቸዋል? የትግራይ ህዝብ ከዚህ ምንድነው የሚያተርፈው? ለምንድነው ሮጠው ከትግራይ ህዝብ ጉያ የሚወሸቁት? ቢሆንም “አይጥ በበላ ዳዋ” አይመታም።

ደግሞ ዘራፊና ገራፊዎቹ ትግርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ናቸው የሚል መደምደሚያ የለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉንም ነገር አብጠርጥሮ ያውቃል። ከአማራው; ከኦሮሞው; ከደቡቡ; ከሶማሌው; ከሐረሪው. .. ወዘተ ገራፊዎችና ቅጥር ነፍሰ-ገዳዮች እንደነበሩኮ የአደባባይ ምስጢር ነው። በርግጥ የሌሎቹ ድርሻ የተላላኪነት; የታዥነትና. .. ገፋ ሲልም የገራፊነት (የጆርናታ ሥራ) እንደነበር ይታወቃል። ቢሆንም በጥፋታቸው ልክ መጠየቃቸው አይቀሬ ነው። ወንጀሉን የፈፀምነው በበላይ አለቆቻችን ስለታዘዝን ነበር የሚል መከራከሪያ ከተጠያቂነት ነፃ ሊያወጣ አይችልም። አማራ ወይም ኦሮሞ ወይም ደቡብ. .. ወዘተ ስለሆነ የሚጮህለት የለም። ይኸማ ነውርና አሳፋሪ ነው። እስካሁንም እንዲህ ያለ ጩኸት ከሌላው አካባቢ አልሰማንም።

የሌላው አካባቢ ህዝብ አጥፊዎችን አሳልፎ ለመስጠት ችግር የለበትም። ለምሣሌ አማራው እነ አዲሱ ለገሰ; እነካሳ ተ/ብርሃን; እነህላዌ ዮሴፍ; እነበረከት ስምኦን; እነጌታቸው አምባዬ. .. ወዘተ ይጠየቁ ቢባል “ሥራችሁ ያውጣችሁ” ነው የሚላቸው። የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የጎዱ; የሀገርን አንጡራ ሀብት የዘረፉና እንዲዘረፍ ያደረጉ; ለመስማትም የሚዘገንን ግፍና በደል የፈፀሙ; ወይም እንዲፈፀም የተባበሩ; ወይም ሲፈፀም ያልተከላከሉ. .. ይልቁንም የአፈናና የግፍ አገዛዝን ለማስፈንና ዕድሜ ለማራዘም ሲታትሩ የነበሩ “በሥራቸው ይጠየቁ” ቢባል የአማራ ክልል ህዝብ እነሱን የሚደብቅበት ቦታ አይኖረውም። እነሱም ወደ አማራ ክልል እግራቸውን አያነሱም።

ምናልባትም ተሰባስበው መደበቂያቸው ትግራይ ክልል ሊሆን ይችላል። ግን ለምን? የትግራይ ህዝብ ዘራፊዎችንና ግፈኞችን የሚደብቅበት ምክንያት ምንድነው? የትግራይ ህዝብ በሀገሩ አንጡራ ሀብት ላይ የተፈፀመው ዐይን ያወጣ ዘረፋ; በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የተፈፀመው ግፍና በደል አይሰማውም እንዴ? የትግራይ ህዝብ ሀገር ሲዘረፍና በወገኖቹ ላይ አረመኔያዊ የጭካኔ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ሊሰማው የሚችል ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለው ጨዋ ህዝብ አይደለም እንዴ? እስከመቼ ነው የትግራይን ህዝብ በፕሮፓጋንዳ ጩኸት አደንቁሮ በሥሙ መነገድ የሚቻለው? እስከመቼ ነው ጥቂቶች በትግራይ ህዝብ ዘላቂ ጥቅምና ህልውና ቁማር የሚጫወቱት? ጥቂት ዘራፊዎችና ግፈኞች “ትግርኛ ተናጋሪዎች” መባላቸው እንዴት በሰፊው የትግራይ ህዝብ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል? ይህን አደገኛ አጀንዳ በማራገብስ የትግራይን ህዝብ ወዴትና/ወደምንድን ነው መግፋት የሚፈለገው?

እናም ጥቂት Activist ተብዬዎች እስቲ አረጋጉት!?

ሲጀመር ወንጀለኞች ከህዝብ ተለይተው መታዬት አለባቸው።

ሲቀጥል “ትግርኛ ተናጋሪዎች” የተባሉት ጥቂት ግፈኞች ናቸው።

ሲደመር ሰፊውን የትግራይ ህዝብ አይመለከትም።

ይኸው ነው!!!

LEAVE A REPLY