ጉዳዩ:- ሕዝቤ ሆይ ጠላትህን እወቅ፤ አለቃህን ተከተል፤ ዓላማህን ተመልከት፤ ሰልፍህን አሳምረህ ዝመት፤
ወድ ወገኖቸ:-
በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሕወሃት/ኢሕአዴግ በታራሚዎች ላይ ያደረሰውን ሰቆቃ፤ የፈፀመውን ግፍ፤ ከስብእና የወረደ ወንጀል ዓይተን ጉድ ብለናል። ሁሉም አዘነ፤ ተከዘ፤ አለቀሰ፤ እከህደከ ሰይጣን መሃረነ ክርስቶስ አሰኘ። ጉዱ የተሰማው ከጉዳትኞችና ከሕያው እርምተኞች አንደበት በመሆኑ ዕውነትነቱንና ቅቡልነቱን የመጠራጠር አመክንዮ የለም። ለዚህ አይደል ማን ያውራ “የነበረ” ማን ያርዳ “የቀበረ” የሚባለው። ድርጊቱ አስደንጋጭ ከመሆኑ በላይ ሕገ አራዊት ምን ያህል አውሬና ጭራቅ ሆኖ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የደም መሬት አርጎ ፪፯ ዓመት ሲአንገላታንና ሲአሰቃየን እንደኖረ አስረድቶናል። በዚህ ሁሉ ያስተዋል ነው ቢኖር የወገኖቻችንን የሞራልና የመንፈስ ጥንካሬ ነው። ተጎጅዎች ለሚወዷት ሃገራቸው ሲሉ ጭራቆችን ይቅር ለማለት መዘጋጀታቸውን ስናይ ልባችን ተነክቷል።
ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች በወገን ላይ ይህን ያህል ያሰጨከናቸው ምክንይቱ ምን ይሆን። ለዚህ መልስ ማግኘት የሚቻል አይሆንም። ከሆነም መልሱ መምጣት ያለበት ከአድራጊዎች ነው። የመላምት መልስ ግን ይኖረናል። ምንአልባት ፍርሃት፤ ማንአለብኝነት፤ ጥጋብ፤ ጥላቻ፤ እልህና ትዕቢት ተዳምረው ስላቃዧቸው ይሆናል። ፍርሃት ያስጨክናል፤ ጥላቻ ከስብእና ውጪ ያደርጋል፤ ማንአለብኝነትና ጥጋብ ግብዝ አርጎ ማስተዋል ይነሳል። እንዚህ በአንድ አእምሮ ውስጥ ሲሰባሰቡ ሰውን አውሬ ያደርጉታል። ጭራቅና፤ አልጠግብ ብይ ብቻ ሳይሆን ከሰውነት በህርይ እውጥተው እሪውስ ያደርጉታል.። የሆነውም ይሄው ነው።
ሌላው ትልቁ ጥያቄ እኛ ይህ ሁሉ መከራ በቤታችንና በሃገራችን ሲፈፀም እየት ነበርን የሚል ይሆናል። ለ፵ ዓመታት የጭራቆችን እኩይ ተግባር ስንናገር፤ ስንጽፍና ስናስረዳ ኖረናል። ለብዙዎቻችን አዲስ መስሎ ታየ እንጅ ችግሩ የነበረ ነው። ሰሚ ባለመኖሩ ግን አዲስ ሆኖብናል። ቀደም ብለን ነቅተን ቢሆን አሁን የሰማናቻውና ያየናቸው ባላስደነገጡን፤ ባልተናደድንና ባልተቆጨን ነበር። እነዚህ ሰዎች ያደርጉትን እንዲአደርጉ አይተን እንዳላየን፤ ሰምተን እንዳልሰማን ዝምታን፤ ፍርሃትን፤ ቸልተኝነትን፤ ምንአገባኝን በመሃላችን አንግሰን ቆየን። የኔን ቤት እስካላንኳኳ ድረስ በሚል ዝምታንመረጥን። ተወደደም ተጠላም በተዛዋሪ ለሰዎቹ እኩይ ተግባር ተባባሪዎች ነበርን። በዴሞክራሲ ዝምታ ስምምነት ነው የሚባለው ለዚህ ሳይሆን ይቀራል። ዝምታ ወርቅ ቢሆንም በአንፃሩ ዝምታ ለውሾም ያልበጃት መሆኑን እረሳን። እውነታው ግን ሕወሃት በገንዘብና በመሳሪያ ሃይል ታጅቦ የእኛ ጀሮ ዳባልበስ ተጨምሮበት ስንገዛ ቆየን። እኩይ ተግባሩን ሳንረዳ ታዘነዋል፤ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለውጥ አምጪና ፈጣሪ አድርገን ስለነዋል።
በመሃላችን የተዋጣለት መለያየትን ፈጥረው አርስበርሳችን እባሉን። በሕወሃት ላይ በነበረን አመለካከት ምክንያት ህብረተሰባችን ተለያይቷል፤ ጓደኛሞች ተጣልተዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ሕዝባችን ተሰዷል፤ ባህላችን ተበርዟል፤ አንድነት ዘቅጦ ጎሰኝነት ነግሷል፤ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ሆኗል። ሁሉም ጫፍ ደርሶ አገር ለመበተን፤ ሕዝብ ለመተላለቅ ዳር ደርሶም ነበር። በዚህ ልዩነታችን ሕወሃት ተጠቃሚ ሆና ቆይቷል። እንደልቡ ገሏል፤ አስሯል፤ ዘርፏል፤ የህብረተሰባችንን ወግ መዓረግ አፍርሷል፤ሃይማኖታችንን አርክሷል፤ ሕገ አራዊትን በምድራችን አንግሷል።
ይሄ ሁሉ ለፀፀት ካልሆነ በቀር የፈሰሰውን አያቀናም፤ የወደመውን አይጠግንም፤ የሞተውን አይመልስም። ባለፈው ድርጊት መፀፀት ም መፍትሔ አይሆንም። ፀፀት መልስ የለውም። መልሱ የስድስት ሚሊዮን ይሁዳዎች እልቂት ፈጽሞ አይደገምም (never again) እንደተባለው በወግኖቻችን ላይ ህወሃት/ኢሕአዴግ ያደረሰው ሰቆቃ፤ ግፍ፤ ዘረፋ፤ ስቃይና መከራ መደገም የለበትም ብለን በአንድ ድምፅ መነሳት ስንችል ነው። ዘግይተንም ቢሆን የሕወሃትን እፉኝት ባሕሪና ተግባር አውቀናል። ዳግመኛ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም።
በተለይ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ስለሐቅ ጥብቅና መቆም ይጠበቅብናል። የጎሳ ፈድራሊዝም እንደማይሰራ እያወቅን አሁንም ስለተግባራዊነቱ ጥሩምባ መንፋታችንን እናቁም። የሕወሃት ዓጀንዳ ዘርን ከዘር ማፋጀት መሆኑን እስካሁን ያልተረዳ የፖለቲካ መሪና ልሂቅ ካለ በፖለቲካ ቅዠት ውስጥ ያለ ወይም የስልጣን ጥመኛ ብቻ ነው። የብሔር ፖለቲካ ስላንገሸገሸን በቃን ማለት ብቻ አይደለም ከሕገ መንግስቱም ይወገድ የማለት ድፍረት ይኑረን። አንዴ ሲአታለሉን ዝም አልን፤ ሁለተኛ ሲአታልሉን እምምም ብለን አለፍን፤ ሶስተኛ እንዲአታልሉን አንፍቀድላቸው። ይህን ከፈቅድን ጅሎች እኛ እንጂ እነርሱ አይሆኑም። ምከረው ምከረው ካልሆነ መከራ ይምከረው አይደል የምንለው። የ፪፯ ዓመት መከራ ካልመከረን፤ ካላስተማረን ከዚህ የበለጠ መከራ ምን ቢሆን እንማራለን። ከዚህ የባሰ አይመጣም ከመጣም እኛ ለመማር ዝግጁ የምንሆን አይመስልም።
እንደ ሕውሃትና እንደ ጎሳ ፖለቲከኞች ቢሆን ኖሮ ኢትዮዮጵያ እስካሁን በቦታው አትኖርም ነበር። ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም የሚለው ሕዝባችን ሲበዛ ደግ ነው። ደግነቱን በሚገባ የተረዳው ፈጣሪ ይህችን ሃገርና ህዝብ ከብዙ መዓትና መቅሰፍት ታድጓታል። ከሃያሉ ቀጥሎ የሕዝባችን መልካም ስነምግባር፤ ይቅር ባይነትና በፈሪሃ እግዚአብሔር መታነጽ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር እንድትቀጥል አስችሏል። የእግዚአብሔር የድንቅ ስራ ማሳያ ዶር ዓብይን የመሰለ መሲህ ሲልክልን መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም።
ከሰባት ወር በፊት የመጡት ሙሴ በአጭር ጊዜ የወሰዷቸው ኢትዮጵያን የማዳን ስራ እጅግ የሚደነቅ ነው። ሁላችንም ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ እያልን ሁሌ እንጮሃለን። ዓብይ ዴሞክራሲን ለማስፈን ያላሰለሰ ጥረት በአድርገዋል። በብዙ ምሳሌና ተግባርም እያስመሰከሩ ይገኛል። እርሳቸው በከፈቱት የዴሞክራሲ ጭላንጭል በሕወሃት ዘመን ያጣነውን ነፃነት እየተጎናጸፍን እንገኛለን። ለምሳሌ በቅርቡ ወይዘሪት ህሊና የምትባል ወጣት ገጣሚ ያሰማችንን ግጥም አይተንና አድምጠን ተደምመናል። የቆንጅት ህሊናግጥም በዓይነቱ እጅግ የተለየና ወቅቱን የዋጀ ብቻ ሳይሆን ሰምና ወርቁ የተራቀቀ፤ መልዕክቱ ግልጽና የሁሉንም ቤት ያንኳኳ ነው። አቀራረቧ ውበትን መልካም ስብእናን አላብሶ ከተዋጣለት ትወና ጋር መድረክ ላይ የቀረበ ነበር። የመናገርና የሃሳብ ነፃነት ሲኖር የተደበቀ የሕዝብ ችሎታና እምቅ እውቀት ይፋ ይሆናል። ከስምንት ወር በፊት የነበረው የፖለቲካ ሁኔታቢቆይ ኖሮ እንኳን ግጥሟን ወጣቷንም ላናውቃት እንችል ነበር። ችሎታዋና ዕውቀቷም የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ ይቀር ነበር። በነፃነት ጊዜ ዕውቀቷ ለሕዝቧ ሁሉ ተረጨ፤ አስተማረ፤ አነቃቃ፤ ለሁላችንም ምሳሌ ሆነ። መብራቱ ከጋኑ ወጦ ለሁላችንም አበራ፤ ብርሃን ሰጠ። ይህን ግጥሟን በወያኔ ዘመን ተናግራ ቢሆን ወይ ትታስራለች፤ ወይ ወደ አረብ ሃገር ትሰደዳለች ወይ ደግሞ ጭካኔው ከበዛ ትገደላለች። ይህን ቀላል ምሳሌ የምናወሳበት ምክንያት ዓቢይ ላጎናጸፈን የዴሞክራሲ መብትና ነፃነት ማሳያ ይሆን ዘንድ ነው። ነፃ ሆነን እንደተወለድን ሁሉ ነፃ ሆነን ለመኖር እንታገል። ስለሆነም ቪቫ ለዴሞክራሲ፤ ቪቫ ለሃሳብ ነፃነት፤ ቪቫ ለስነጽሑፍና ለትወና፤ ቪቫ ለኣቢይ ለውጥና ጥረት።
ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ ማድረግ የሚገባቸውን እያደረጉ ነው። እኛ ደግሞ በስሜት፤ ንዴትና ቁጭት ተገፋፍተን በዓቢይ ላይ ከፍተኛ ጫናና ግፊት እያደረግንባቸው እንገኛለን። አገር መምራት በተለይም ፖለቲካዊ፤ አኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ሁኔታው ውስብስብ ብሎ ቀውስ ውስጥ የምትታመስን ሃገር ማስተዳደር ቀላል እንዳልሆነ መረዳት አለብን። የአቢይ አካሄድና አሰራር መረዳት ያስፈልጋል። እርሳቸው በትእግስት፤ በሕግና ስርዓት፤ በፍቅርና በዘዴ ለማስተዳደር ድፍት ቀና የሚሉ መሪ ናቸው። እንደምንሰማውና እራሳቸውም እንዳሉት በቀን የሶስት ስዓት እረፍት ብቻ እንዳላቸው ይታወቃል። ብዚዎቻችን ሶማሊያ ክልል ገብተው በመከላከያ ሃይል እንዳረጋጉት ለምን ትግራይ ክልል በሃይል ገብተው የህወሃት ወንጀለኞችን አስረው ለሕግ አያቀርቡም እያልን በመገናኛ ብዙሃን፤ በማህበራዊ ድረ ገጾች፤ በግልና በቤተሰብ ውይይቶች እንጫጫለን። እውነት ይህን ሃሳብ ለዶክተር ዓብይ ማቅረብ እሳቸውን ማሳነስ አይሆንብንም። ካለፉት ስምንት ወራት ተግባራቸው፤ ንግግራቸውና አስተሳሰባቸው እኛ የምንለውን ሃሳብ ያጡታል ብሎ መናገር እሳቸውን አለማወቅ ነው።ጠ/ሚ ዓብይ የእኛን ዘዴና ምክር እንደ ቅድሚያ አማራጭ አርገው የወሰዱት አይመስልም። ሃይል የመጨረሻውና አስቀያሚው የመፍትሔ አማራጭ እንደሆነ የሚአምኑ ናቸው።
እውነት ከሆነ ደግሞ ከአንድ አስተዋይ፤ አገር ወዳድ መሪ የሚጠበቅ ስለሆነ ልንደግፋቸው ይገባል እንጅ ጭንቀት ላይ ልንጥላቸው አይገባም። እውነት ተደመርን ከሆነ በሳቸው ላይ ጫና ከማረግ ይልቅ ለሃሳባቸው ይሁንታ ሰጠን እናግዛቸው። በየአቅጣጫው የሚደረገው የጎሳ መቆራቆስ እያወገዝን ችግሩ ከዚህ ከዚያም እንዳይፈጠር ለሕዝባችን ትምህርት፤ ቅስቀሳ ማድረግ ይጠበቅብናል። እንዳየነውና እንደምንገምተው ዓብይ ፱፮ በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አላቸው። በዚህ ከተማመን የሳቸውን መልካም ስራ የሚአደናቅፍ ፤ የሚአኮስስ፤ በአመራራቸው ላይ አላስፈላጊ ጫና ማድረግ አይጠበቅብንም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት ያልተደመረው ህውሃት ነው። ትኩረታችን በዚህ ላይ ይሁን። በዓብይ ላይ ጫና ስናበዛ የሕወሃት እኩይ ተግባር ጉልበት ያገኛል። የህወሃት ችግር እስኪፈታ አሰላለፋችን በጋራ ጠላታችን ሕወሃት ላይ ያነጣጥር (eyes on the ball)። ሕወሃት የዘረፈውን ሃብት ተጠቅሞ ሕዝባችንን ለማጫረስ፤ አገሪቱን ለመበተን፤ አለያም የሰቆቃ አገዛዙን መልሶ ለማስፈን በመራወጥ ላይ ይገኛል። በየቦታው የሚፈጠር ግጭት፤ ግድያ፤ መፈናቀል ሁሉ የሚጠቅመው ያልተደመረውን ካምፕ ነው። ሕወሃት ቀውሱን እንደ ጊዜ መግዣ ተጠቅሞበታል፤ እንደገና የማንሰራራት ሕልሙን አቆጥቁጦለታል። ስለዚህ ባልታወጀ ጦርነት ላይ ነን። ጦርነት ደግሞ የራሱ ሕግ አለው። ይሄውም ወገንህን ለይ፤ ተመልከት አላማህን፤ ተከተል አለቃህን አዝምት ሰራዊትህን የሚል። ይህን ስናደርግ በርግጠኝነት አሸናፊ ሆነን እንዘልቃለን። አሁንም ከጠ/ሚ ዓብይ አገዛዝ ጋር ወደፊት።
ነን ሶቤ?
አቢቹ ነጋ
ታህሳስ ፪፻፩፰