አልነጋም ገና ነው! /አገሬ አዲስ/

አልነጋም ገና ነው! /አገሬ አዲስ/

የጸሓይ ብርሃን ባለበት ሁሉ ጨለማ አይኖርም።ድቅድቅ ያለ ጨለማን አሽንፎ የሚወጣ የንጋት ብርሃን ጭላንጭል ወይም ወጋገን  የብሩህ ቀን ተስፋ አብሳሪ ነው።ሆኖም ግን ሌሊቱ ሙሉ በሙሉ በጸሃይ ብርሃን ካልተተካና ጨለማው ካልተወገደ ብሩህ ቀን ወጣ ማለት አይቻልም።

የጨለማው መኖር የሰው ልጅ የብርሃንን ጥቅም እንዲያውቅና ጨለማን ተገን አድርጎ የሚመጣውን አደጋና  የአውሬ ጥቃት ለመከላከል ሲል ጨለማን ለማሶገድ መፍትሔ እንዲፈልግ አስገድዶታል።ለፍልስፍና ማህጸኑ ችግር መኖሩ እንደሆነ ፈረንጆችም “necessity is the mother of invention” ብለው ገልጸውታል።ስለሆነም ባለፈበት ደረጃ ችቦን፣ሻማን፣ኩራዝን፣ፋኖስን፣ የኤሌክትሪክ መብራትን፣ ለመፍጠር ችሏል።የኤሌክትሪክ መፈጠር ጨለማን ለማባረር ብቻ ሳይሆን ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሃይል ምንጭ ሆኗል። ይህ እድገት በኤኮኖሚውና በማህበረሰቡ ኑሮና አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ አይካድም።

በተመሳሳይ ደረጃ የዓለም ሕዝብ  የጨለማ ስርዓት ውጤት በሆኑት ፣የድህነት፣የዃላቀርነት ኑሮ ሰለባ ሆኗል።በዘራፊ ፣በአረመኔና ጨካኝ መሪዎች መዳፍ ሲሰቃይ ኖሯል፤አሁንም ደረጃው ቢለያይም እዬኖረ ነው።ከዚያ ለመላቀቅ ትግል ሲያደርግ እንደኖረ፣አሁንም በማድረግ ላይ ይገኛል።የኢትዮጵያ ሕዝብም በዚህ ሂደት ውስጥ አልፏል፤ እያለፈም ነው።በትግሉ ሂደት ተስፋ ሰጭ ድሎች ፍንጥቅ ብል ይወጣሉ፤ወጥተዋልም።

በትግሉ የተሳካላቸው አገሮች ሕዝባቸው ከጨለማ ስርዓት ወጥቶ ለመልካም አስተዳደርና ለተሻለ ኑሮ ሲበቃ ለዚያ ያልታደሉት ግን አሁንም ከነበሩበት የጨለማ ስርዓት አልተላቀቁም።ይበልጥ የሚያሳዝነው ግን በጨለማ ስርዓት ስር ሲዳክሩ የነበሩት አገሮች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በማዬት በሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች ላይ ለሰፈነው የጨለማ ስርዓት አጋዦችና ደጋፊዎች መሆናቸውና የሕዝቡን ትግል ለመቅጨት ከስርዓቱ ጎን መሰለፋቸው ነው።

የበዝባዦችና የጨቋኞች አንድነት በሰፈነበት የትግል ሜዳ ላይ ለአገራቸው ነጻነትና ለተሻለ ኑሮ፣   ለመብታቸው ከሚታገሉት በኩል ድክመት በመኖሩ ብዙ ጊዜ  የሚያደርጉት ትግልና ሙከራ ከሚፈልጉት ግብ ላይ አላደረሳቸውም።የሰፈነውን ችግር ለማሶገድ ጠላትና ወዳጅን  ለይቶ ያለማወቅ፣ ቁርጠኛነት አለመኖር፣ የዓላማ ስልትና ግብን ያለማወቅ ድክመት እንዲሁም የራስን ጥቅምና ዝና የማስቀደሙ አባዜ ለውድቀት ዳርጓቸዋል።በተጨማሪም  ትግላቸው በአስመሳይ አጋሮች እዬተጠለፈ በነበረበት አሮንቋ ውስጥ እንዲቆይ መደረጉ በተደጋጋሚ ተከስቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ዘመናት የሰፈኑበትን የጨለማ ስርዓቶች  በተለይም ላለፉት 28 ዓመታት የተጫነበትን የዘረኝነት ስርዓት የወለደውን  የግፍ ቀንበር ለመስበር ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ እምቢባይነቱን በአደባባይ መስዋእት እየከፈለ አሳይቷል።በዚህ የሕዝብ እምቢባይነት ሳቢያ የስርዓቱ አካል የሆኑትም ሳይቀሩ ለሕዝቡ ጥያቄ ጆሯቸውን ሰጥተው ብቻ ሳይሆን የለውጡ አንቀሳቃሾች ሆነዋል።በዚህ የለውጥ ሂደት አንዳንድ የሚያበረታቱ እርምጃዎችንም ወስደዋል።ይህ እርምጃ ጨለማን ለማሶገድ ፍንጥቅ ብሎ እንደሚወጣው የብርሃን ጨረር መታዬት ቢኖርበትም አቅም አጥቶ በጨለማው ጉልበት እንዳይዋጥ የለውጡ ፈላጊ ሃይል የየበኩሉን ችቦ ለኩሶ የፈነጠቀውን የለውጥ ጨረር ማገዝ ይኖርበታል።

ብርሃኑን ለማዳፈን  ጨለምተኞች የሚያደርጉትን ጥረት መቋቋምና በለውጡ ስም መለስተኛ ጥገና በማድረግ  የዘረኞች የጨለማ ስርዓት እንዳያንሰራራ ቆቅ ሆኖ መጠበቅ ተገቢ ነው።ካንሰር በሽታ ከስሩ ካልተወገደ ቢነካኩት ለመስፋፋት መንገድ መጥረግ ይሆናል።በበሽታው የተጎዳውም በመጀመሪያው ህክምና  ድኛለሁ ብሎ ተስፋ ማድረግ አይኖርበትም።

አሁን በኢትዮጵያ አገራችን የሚነፍሰው የለውጥ ንፋስና የሚወሰደው እርምጃ የሚፈለገው ለውጥ አካልና የመጀመሪያ መንደርደሪያ እንጂ የለውጡ መጨረሻ ሆኖ መታዬት የለበትም።ገና ብዙ ይቀራል።አሁንም የጎሳ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ከቦታቸው አልተወገዱም።አሁንም የዘረኞች ስርዓት ባሰፈነው የማፈናቀል ሂደት ሰው እዬተፈናቀለ ነው።በከተማም አስተዳደር ውስጥ የተንሰራፋው የጎሰኝነትና  የሙስና አሠራር በጉቦ ወይም    ከአቅሙ በላይ የሆነ ፎቅ እንዲሠራ በማስገደድ  መሥራት  ያልቻለው ብዙ ሕዝብ የኖረበትን የግዥና የውርስ ቦታውን እየተነጠቀ ቤት አልባ ሆኗል።ሌላውም ከሚተዳደርበት የግል ሥራው እየተፈናቀለ ሥራ አጥ ሆኗል።እንደመዥገር ተጣብቀው ለሚመጠምጡት የቀበሌና የክልል እስተዳደር ባለስልጣኖች ተጋልጦ መከራውን ሲያይ ኖሯል፣አሁንም እያዬ ነው።በአገር ደረጃም የአገር ሃብትና ንብረት ባለሥልጣኑ  እንደፈለጉ የሚያዙበትና የሚዘርፉት የግል ሃብት ሆኗል።አሁን በመካሄድ ላይ ያለው የመንግሥት ዘመቻ በዚህ ላይ ያተኮረ ቢመስልም ዘለቄታ እንዲኖረውና ውጤታማ እንዲሆን በጥቂት እርምጃዎች ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርና ተንገጫግጮ እንዳይቆም  የሕዝቡን ድጋፍና ተሳትፎ ይጠይቃል።ሕዝቡ የእርምጃው አድናቂና ደጋፊ ከመሆን ባሻገር የእርምጃው አካል በመሆን በየቀበሌው የሙስና አስተናጋጅ የሆኑትን ሁሉ ከነማስረጃው  ለመንግሥት አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል።

የዘረኛው የኢሕአዴግ ስርዓት የፈጠራቸው ባለሥልጣኖች የፈጸሙትና የሚፈጽሙት ሌላው ወንጀል የተከናወነው በፖለቲካው ዙሪያ ነው።በዚህ መስክ ጥያቄ ያቀረቡና የተቃወሙ ብዙ ዜጎች ባለሥልጣኖቹ ባቋቋሟቸው የግል እስርቤቶች ሳይቀር ህይወታቸው ጠፍቷል፣ብዙዎችም የደረሱበት አይታወቅም። በሽህ የሚቆጠሩ አካላቸው ጎድሏል፣በእስር ቤት ተሰቃይተዋል፣ተሰደዋል።አሁን የሚካሄደው ዘመቻ በዚህ በኩል ወንጀል በፈጸሙት ላይ ጎልቶ የሚታይ ሥራ አልሠራም።በወንጀል የሚጠረጠሩት አሁንም በነጻነት የሚፈልጉትን ከማድረግ አልተቆጠቡም።ለሚፈጽሙት ወንጀል ሽፋንና ተገን የሆናቸው የኢሕአዴግ መዋቅርና  ሕገመንግሥቱ ነው።እነዚህ ሁለቱ መሳሪያዎች እስካልተወገዱ ድረስ በወንጀለኞቹ ላይ እርምጃ ይወሰዳል፣ እውነተኛ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው። አሁን በሙሰኞችና በዘራፊዎች  ላይ ከሚወሰደው  እርምጃ ጎን ለጎን  የፖለቲካ ወንጀል በፈጸሙ ባለሥልጣኖችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰባቸው ይገባል።ስለሆነም የለውጡ ሂደት መልክ እንዲይዝና በእርግጠኛነት እንዲቀጥል ከተፈለገ ኢሕአዴግ በተባለው ድርጅትና በፈጠረው የክልል  አስተዳደር በተሰገሰጉትወንጀለኞች  ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰድና ሕገመንግሥት የተባለውንም ሕገአራዊት መለወጥ ያስፈልጋል።ሕዝብ እንደ እስረኛ ታግቶ እንዲኖር የተቋቋመው የክልል አስተዳደር ተወግዶ  በነጻ በፈለገበት ቦታ ሠርቶ የመኖር መብቱ የማይደፈርበት ፣የፖለቲካው፣የኤኮኖሚውና የማህበረሰብአዊ ጉዳዬች ወሳኝና ተካፋይ የሚሆንበት፣የክፍላተሃገር  አስተዳደር መፍጠርና ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ  አገራዊ መዋቅር ማስፈን አንዱና ዋናው መፍትሔ ነው።

የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት ሲታሰብና ሲጀመር ጸረ ዴሞክራሲ በሆኑት ሥርዓቶች ውስጥ ባገለገሉት ላይ ዴሞክራሲያዊ የፍትሕ አሠራርና  የሕግ የበላይነት በተግባር ሲተረጎም እንጂ በእርቅና ይቅርታ ስም ተሸፋፍኖ በመደመር መርህ ማለፉ ለመጭው ትውልድ የሚሰጠው ትምህርት አይኖርም።ቢያንስ ቢያንስ ጥፋትን አምኖ ሕዝብን ይቅርታ መጠዬቅ ቁስል እንዳያመረቅዝ ለዘለቄታ ማገገም ይረዳል። ትውልድም ይማርበታል።ያ ካልሆነ  ሥልጣን ይዞ እዬገደሉ፣እየዘረፉ በሰላም መኖር ባህል ይሆናል።

በተጨማሪም መታለፍ የሌለበት ጉዳይ አድር ባዮች የሚያደርጉት የመገለባበጥ ባህልም እንዳይቀጥል ማድረግ የለውጡ አካል መሆን አለበት።አገርና ሕዝብ ሲበደል ወንጀለኛውን  በመደገፍ እራሳቸውን ለጥቅም የሸጡና የዜግነትና ሰብአዊ ድርሻቸውን ያልተወጡ ወገኖችን ካደረባቸው አጉል እራስ ወዳድነት መንፈስ እንዲላቀቁ ማድረግ አንዱ የባህል ዘመቻ አካል ሊሆን ይገባል።ቢያንስ ቢያንስ አካፋ አካፋ መባል አለበት።ያ ካልሆነ የአገርና የሕዝብን ጥቅምና ክብር ለመሸጥ የማይመለሱ አድርባዮችን ማበረታታት ይሆናል።በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩትን የስርዓቱን ተባባሪዎችና አድርባዮች ማጋለጥ የለውጥ ፈላጊው ክፍል አንዱ ተግባር መሆን ይኖርበታል።አሁን እንደሚታዬው ከሆነ ትናንትና የኢሕአዴግና የወያኔ ስርዓት ደጋፊ ሆነው ተቃዋሚውን ሲሰልሉና በየኤምባሲው ሲልከሰከሱ የነበሩት አሁን ቆባቸውን ለውጠው የለውጡ እረዳቶች መስለው የማጭበርበር ድራማ በመሥራት ላይ ናቸው።ይህንን መሳይ  ይሉኝታ ቢስነት በይቅርታና በመደመር ስም ማለፍ  ለውጡን ስርነቀል አያደርገውም።እንደውም ለውጡ እንዲቀለበስ ዕድል መስጠት ይሆናል። የግዴታ የአስተሳሰብና የባሕል ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሌላው አሁን በመታዬት ላይ ያለው ስህተት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጨለማ ስርዓት  ለመላቀቅ የሚያደርገውን ሁለገብ ትግል በኤኮኖሚ ጥያቄ ብቻ እያዩ  ለመፍታት መሞከር የሚደረገው አካሄድ ነው።የፖለቲካውንም ሆነ የኤኮኖሚውንም  ለውጥ ለማምጣት ሕዝቡንና አገሪቱን ከውጭ ተጽእኖ የሚያላቅቅና በራስ የመተማመንን አቅም የሚገነባ  ፖሊሲ መከተል ያስፈልጋል።”ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንደሚባለው የሕዝቡን ጥያቄ በልቶ የማደርና የሆድ ጥያቄ አድርጎ በማቅረብ  ደሃ ሕዝብ ሥራ ይዞ ገዝቶ የሚበላበት ገንዘብ እስካገኘ ድረስ ከዬትም ይምጣ ከዬትም፣የዃላዃላ ምን ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ሳያጤኑ፣ለጊዜያዊ ድጋፍና ዝና ሲሉ የአገርን ብሔራዊ ሃብትና ክብር እንዲሁም የከተማ ቦታና የገጠር እርሻ መሬት ውሉ በግልጽ ባልታወቀ መንገድ  ለውጭ አገር ባለሃብቶች አሳልፎ መስጠት ሊወጡት የማይችሉትን ከፍተኛ ችግር በአገር ላይ  መጋበዝ ይሆናል።”በሬ ሆይ ገደሉን አይተህ ሳሩን”እንደሚባለው ሊመጣ የሚችለውን መዘዝ በቅድሚያ ማሰቡ ተገቢ ነው።ዛሬ የተገባው ስምምነት ከጊዜ በዃላ ጣጣ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ ብልህነት ነው።ግልጽነት በሌለውና ሕዝብ በማያውቀውና  ባልፈቀደው መንገድ የሚደረግ የቢሊዮን ዶላር ብድርና ኢንቨስትመንት ውል የትሪሊዮን ዕዳ ይወልዳል።ከዛም በላይ የብዙ ሕዝብ ህይወት ለሚጠፋበት ወረራና ግጭት በር ይከፍታል።አሁን በዓለም ላይ የሚካሄደው ግብግብ የደሃ አገሮችን መሬትና ሃብት በኢንቬስትመንት ስም መቀራመት ነው።ከዱሮው ቀጥተኛ  የጦር ወረራ ይልቅ ለዚያ የሚረዱ ቡድኖች ስልጣን ላይ እንዲወጡ ማድረግ የዕቅዱ መጀመሪያ ነው።አገራችንን አናስደፍርም በሚሉት መንግሥታት ላይ ከውስጥና ከውጭ  ጠላት እንዲነሳባቸው የማድረጉም ሴራ በግልጽ ታይቷል።በተለይም የአፍሪካ ቀንድ የተባለው አካባቢ  ለዚህ አይነቱ የዘመናችን የጥቅም  ድምጽ አልባ ጦርነት የተጋለጠ ሆኗል። ግብግቡ ከቀጠለ ወደ ግልጽ ጦርነት የማምራቱ አደጋ ከፍተኛ ነው።

የተጀመረው የለውጥ ጭላንጭል የመጨረሻው ፌርማታ ሆኖ መታዬት አይኖርበትም።“የነጋ መስሏት ከበረት የወጣች አህያ ሄዳ ሄዳ ከጅብ ጉያ” እንደሚባለው እንዳይሆን ያሰጋል። ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣የዘረኞች የጨለማ ስርዓት እንዲወገድ   የሁላችንም ትብብር ይጨመርበት።አለቀ ደቀቀ ብለን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ አይኖርብንም።ኢሕአዴግ እንደድመት እራሱን በራሱ በልቶ ይጨርሳል፤አልጋ ባልጋ ለውጥ ይመጣል ብሎ ከመጠበቅ  የጎሰኞች ስርዓት በሕዝቡ ትግል ተደምስሶ ስርነቀልና  ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  እስኪሰፍን፣አገራችን ከውጭ ሃይሎች የፖለቲካና የኤኮኖሚ ጥገኝነት እስክትወጣ  ድረስ  ትግላችን  መቀጠል ይኖርበታል። አልነጋም ገና ነው!

LEAVE A REPLY