አቢይ ያለው አማራጭ አንድና አንድ ነው፤ በኦሮሚያ ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ …...

አቢይ ያለው አማራጭ አንድና አንድ ነው፤ በኦሮሚያ ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ … | ቬሮኒካ መላኩ

ዶ/ር አቢይ አህመድና የሚመራው መንግስት ፈረንጆቹ ” ኢንጁሪ ታይም ” የሚሉት የባከኑ ሰአቶች ውስጥ ይገኛል። በተጨማሪ ደቂቃዎችና በባከነ ሰአት እየተጫወተ ነው። ቲም ለማና ኦሮሚያ ክልል “ነጋቲ ቡላ” ተባብለው ተሰነባብተዋል። አቢይና ለማ ኦሮሚያን ካለደረሰኝ ለኦነግ አስረክበዋል።


ከመቶ ሀያ አመታት በፊት ፔትሮስ ጊዮርጊስ ለራስ አሉላ የፃፈውን ደብዳቤ አቢይ አህመድ ከእኔ ፔጅ አንብቦ ይማርበት ዘንድ እጠቅሳለሁኝ …… ፔትሮስ ጊዮርጊስ በዘመኑ ከነበሩ ምሁሮች አንዱ ነበር ። ፔትሮስ እንደዚህ ይላል…

<< …… ቁንቁን ከትል ሁሉ ያንሳል። ነገር ግን ታላቁን ግንድ በልቶ አድርቆ ይጥለዋል።ዛፍ ሳያድግ በእግር ጣት ይነጫል። ካደገ በኋላ ግን ብዙ መጋዝና መጥረቢያ ያስፈልገዋል። እንደዚሁ የአሞራ ግልገል ክንፉ ሳያድግ የስድስት አመት ልጅ ከዛፍ አውርዶ ሲጫወትበት ይውላል፣ ክንፉ ካደገ በኋላ ግን ከሰው እጅ ስጋ ነጥቆ እስከ አየር ይወጣልና የሚያገኘው የለም። እንደዚሁም እነዚህ ናቸውና ለአገርዎ ፣ለግዛትዎ ፣ለጠጅዎ ፣ለጮማዎ ከሁሉም ይልቅ ለታላቅ ክብርዎ ይሞክሩ።>> በማለት ፔትሮስ ጠላትን በእንጭጩ ስለመቅጨት አሉላ አባ ነጋን ይመክራል።።

ማንኛውም መንግስት ለሉአላዊነቱና ለግዛቱ ቀናኢ ካልሆነ መንግስት አይባልም። ውሻ እንኳን ድንበሩን በሽንቱ ያሰምራል። ደመነፍሳዊ ያልተፃፈ ውሻዊ ህጉን ያከብራል፣ ያስከብራል። ድንበሩን ደርምሶ ህጉን ጥሶ ከገባ ልኧላዊነቱን በሹል ጥርሱ በሀይል ያስከብራል።

የአቢይ አህመድ መንግስት አደጋ ውስጥ ገብቷል። አደጋው የመጣበት ኦነግ ከሚባለው ከኦሮሞ የፖለቲካ ሀይል ነው። ይህ የኦሮሞ ሀይል የማይታረምና ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ነው። አንዱን እግሩን በሌላው ጠልፎ ለመጣል በከፍተኛ ስፒድ እየመረሸ ነው። አቢይ ያለው አማራጭ አንድና አንድ ነው ። በኦሮሚያ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ህግና ስርአትን ማስከበር። ይሄን ካላደረገ ከሚመጣው ፖለቲካዊ ውሽንፍር የሚድን አይመስለኝም።

LEAVE A REPLY