ባለፉት ሶስት ቀናት የሆነውን ብቻ እንመልከት… | መሳይ መኮንን

ባለፉት ሶስት ቀናት የሆነውን ብቻ እንመልከት… | መሳይ መኮንን

በጉጂ ዞን ወደ ሻኪሶ ንግድ ባንክ ያመሩ የነበሩ ሁለት ተሽከርካሪዎች በኦነግ ታጣቂዎች በጥይት ተመተው ሶስት ሰዎች ሲገደሉ በአንደኛ መኪና ውስጥ በነበረ ሹፌር ጀግንነት 6ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የኦነግ ካዝና ከመግባት ተርፏል። እዚያው ጉጂ ከአማሮ ኬሌ አዋሳኝ አከባቢዎች የኦነግ ታጣቂዎች ዘረፋ ላይ ተሰማርተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶችን ወስደዋል። የቡናና የሙዝ ማሳዎችን አቃጥለዋል። አራት የኮሬ ተወላጆችን ገድለዋል። የወለጋውን የየዕለት አስከፊ ትራጄዲ ሳይጨምር የኦነግ ዱካ ባረፈባቸው መሬቶች ሰዎች መገደላቸው፡ ሴቶች መደፈራቸው፡ ቤቶች መቃጠላቸው፡ የንግድ ቦታዎች በእሳት መጋየታቸው የተለመደ ክስተት ሆኗል። የመንግስት ትዕግስት የመጽሀፍ ቅዱሱን የትዕግስት ተምሳሌት የሆነውን ኢዮብን ሊያስንቅ ደርሶ ነበር። የሀሙስ ዕለቱ የኦዴፓ መግለጫና ተከትሎ የተወሰደው እርምጃ ባይኖር ኖሮ የመንግስት እሹሩሩ ማለት ሀገርን ዋጋ እያስከፈለ፡ የበለጠ ቀውስ እየፈጠረ መሄዱ የማይቀር ነበር። አሁንም ከዚያ ስጋት ያመለጥን አይመስለኝም።

በዓለም ታሪክ ሁለት ተፋላሚ ወገኖች ከአንድ ሀገር ርዕሰ ከተማ ሆነው ታጣቂዎቻቸን ለጦርነት ትዕዛዝ የሚሰጡባት የመጀመሪያዋ ሀገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም። መንግስት በሚያስተዳድራት ሀገር ውስጥ የአማጺ መሪ መሀል ከተማ ተቀምጦ የጦርነት ነጋሪት የሚጎሰምባት ሀገር ኢትዮጵያ። የኦነጉ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ አራት ኪሎ ቤተመንግስት አፍንጫ ስር ሆነው ለታጣቂዎቻቸው የውጊያ መመሪያ ሲያስተላልፉ መስማት ያስደነግጣል። ኢሌሌ ሆቴል በመንግስት ወጪያቸው እየተሸፈነ፡ መንግስት ላይ ጦርነት የሚከፍቱ የአማጺ መሪ መኖሩን ጊነስ ወርልድ ቡክ ቢሰማ ጮማ መረጃ ይሆንለት ነበር። ኢትዮጵያም ስሟ በጊነስ የሚመዘገብበት የሚያኮራም ባይሆን አንገት የሚያስደፋ ታሪክ ይሆናት ነበር።

የኦነግ ክሽፈት የሚጎላው እዚህ ላይ ነው። ማን ላይ ተቀምጠሽ ማንን ታሚያለሽ እንዲሉ በክብር ጠርቶ፡ አልጋ አዘጋጅቶ የሚያስተኛ ምግብ አቅርቦ የሚያጎርስ ፡ በሰላማዊ መንገድ ታግለህ ለስልጣን መብቃት ትችላለህ ብሎ በሩን በርግዶ የሚከፍትለትን መንግስት ምስጋናው ቢቀር ሰላም መንሳት፡ በጦር መውጋት ምን የሚሉት እብደት ይሆን? ለአርባ ዓመት ፈቅ የማይል የትጥቅ ትግል ውስጥ ሲርመጠመጡ የቆዩት የኦነጉ መሪ የአስመራ ቆይታቸውን በቅርበት ለሚያውቅ ሰው አሁን ላይ የሚፎክሩት ሲሰማ ጥፍር ውስጥ መደብቅ እስኪቀር የሚያሳፍር ተራ ጀብደኝነት ነው። የአስመራን ኡዞ አረቄ እየላፉ፡ የሻዕቢያ መንግስት ባዘጋጀላቸው ቪላ ቤት እየኖሩ፡ በላንድ ክሩዘር መኪና በአስመራ ጎዳናዎች ሲንፏለሉ የቆዩት አቶ ዳውድ ኢብሳ ላለፉት አርባ ዓመታት ምን የሚመዘገብ ድል ሰርተው፡ የትኛው ከአንጀት ጠብ የሚል ውጤት አስመዝግበው ይሆን እንዲህ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩት? እነአብይ ለኦሮሞ ህዝብ እያስገኙ ካሉት አስደናቂ ድል የበለጠ ኦነግ ምን የተሻለ ነገር ሊያመጣ ይሆን ሰይፍ ይዞ የተነሳው? ይህ ለውጥ በኢትዮጵያ ህዝብ የህይወት መስዋዕትነት ባይመጣ ኖሮ አቶ ዳውድ ኢብሳ ለጥ በለው ከተኙበት የአስመራው ፍራሽ የሚቀሰቅሳቸው ምን ታአምር ይመጣ ነበር?

ኦነግ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ይታመናል። መንፈስ እስኪሆን የደረሰ፡ በብዙዎች ኦሮሞ ልብ ውስጥ የነጻነት ቀንዲል ተደርጎ የሚታይ ነው። መሪ ያጣው፡ ሙሴ የራቀው ኦነግ ለህዝቡ የነጻነት ርሃብ የሚመጥን አታጋይ አጥቶ መጨረሻው በሰፈርና ጎጥ በተቧደኑ ግለሰቦች ተሸንሽኖ አርፏል። ከኦሮሞ አብራክ የወጡት ለማና አብይ በኦነግ የጨነገፈውን የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ጥማት ከዳር ለማድረስ ታሪካዊ እድል በተፈጠረበት በዚህን ወቅት ባልበላም ጭሬ ልድፋው ዓይነት ትግል ውስጥ የሚንደፋደፈው ኦነግ በመሪዎቹ ተራ ጀብደኝነት አሳፋሪ ታሪክ ትቶ ከሚያልፍበት ምዕራፍ ተጠግቷል።

በተለያየ መልኩ የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጠሪያና በዓላማ ተለይተው የራሳቸውን ድርጅት ከመሰረቱት የቀድሞ የኦነግ አመራሮች ሌላ በአሁኑ ወቅት በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ሶስት ሃይሎች አሉ። በዳውድ ኢብሳ የሚመራውና ከተማው ላይ ጎልቶ የሚታየው ኦነግ፡ በጎበዝ አለቆች የሚታዘዘውና የታጠቀ ሃይል የያዘው ኦነግና እነኮ/ል ገመቹ አያና የሚያንቀሳቅሱት ኦነግ በሚል በሶስት ሃይሎች ተሸንሽኗል። የአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ፖለቲካውን ተቆጣጥሮ ከመንግስት ጋር የሚደራደር ሲሆን የተወሰ ሃይል የማዘዝ አቅም ያለው ነው። ያ ሃይል በቁጥር ከ1ሺህ ብዙም የሚዘል አይደለም። በምስራቅ ወለጋና ጉጂ ባሌ የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ደግሞ የየራሱ የጎበዝ አለቃ ያለው ለዳውድ ኢብሳ በቀጥታ የማይታዘዝ እንደሆነ ይነገራል።

አንድ ሰሞኑን በተሰራጨ ቪዲዮ ላይ በትግል ስሙ ኩምሳ ደሪቤ የሚባል የጎበዝ አለቃ የዳውድ ኢብሳንና የመንግስትን ድርድር ለኦሮሞ ህዝብ አሳፋሪ ክህደት ነው ሲል በመግለጽ በሃይል የኦሮሚያን ነጻ መንግስትነት ለመመስረት የተጀመረው ትግል እንደሚቀጥል ይናገራል። አቅሙን በተመለከተ ብዙም መረጃ የለም። ለዘረፋና ግድያ የሚሆን ቅንጣቢ ሃይል እንደማያጥረው ግን ይገመታል። ሆኖም ከህወሀት በስውር ድጋፍ እያገኘ በመሆኑ አቅሙ እየተጠናከረ ሊመጣ ይችላል። የኮ/ል ገመቹ አያና ኦነግ ደግሞ ጓዙን ጠቅልሎ ጌታቸው አሰፋ እግር ስር የወደቀ ነው። ከኦዴፓ አከባቢ እንደሰማሁት ኮ/ል ገመቹ አያና አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት መቀሌ ነው። በመንግስት ደህንነቶች ራዳር ውስጥ በመሆናቸው እያንዳንዷ እንቅስቃሴያቸው አታመልጥም። ከቀድሞው የኦነግ ሰራዊት የተራረፈ ሃይል ይዞ፡ የህወሀትን ደጅ በመጥናት አቅሙን ለማፈርጠም እየሰራ እንደሆነ ይነገራል።

ሶስቱም ኦነጎች ባይሰማሙም በግብር አንድ ናቸው። ጸረ ኢትዮጵያ ናቸው። ከተሳካላቸው የኦሮሚያን ክልል ነጻ ሀገር ማድረግ ነው ህልማቸው። የጋራ መዳረሻቸው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የምትመሰረት ሀገር ማየት ነው። ከደረሱ በኋላ እነሱም አንድ ላይ ስለመቀጠላቸው እርግጠኛ አይደሉም። የዘር ፖለቲካ ሲጀመር ያሰክራል፡ ሲያልቅ ተያይዞ ያጠፋል። የኦነግ ስንጥቅጣቂዎች መጨረሻ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመቱ የሚከብድ አይደለም። አሁን ያሉት በየትኛውም የኦነግ ስንጣቂ ድርጅት ውስጥ የሚገኙት መሪዎች የኦሮሞን ህዝብ የሚመጥን ተልዕኮና ግብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይታመንም።

የዳውድ ኢብሳን ኦነግ ብንወስደው የወለጋ ተወላጆች የተቆጣጠሩት፡ ከዚያም አልፈው ወደ መንደር የዘለቁ የአንድ ሰፈር ልጆች የሚመሩት ነው። በትላንቱ መግለጫቸው አቶ ዳውድ ኢብሳ የብ/ጄ ከማል ገልቹን የኦሮሚያ ደህንነት ቢሮ ሃላፊ መሆንን አጥብቀው የኮነኑት ለምንድን ነው? እነብ/ጄ ሃይሉ ጎንፋና ኮ/ል አበበ ገረሱ ከዳውድ ኢብሳ ኦነግ ለምን ተለዩ? መልሱ ሚስጥር ወይም የማይደረስበት አይደለም። ቀላል ነው። ኦነግ ከወለጋ ተወላጆች በቀር ሌላውን ጠራርጎ አባሯል፡፡ አንዳንዶቹ ላይ የሞት ፍርድ ብያኔ አስተላልፏል። የአርሲና የሸዋ ኦሮሞዎችን ከኦነግ ውስጥ ያጸዱት አቶ ዳውድ ኢብሳ አብሮ አደጎቻቸውን ይዘው የኦነግን ታፔላ ጭነው አስመራ ላይ ቀርተው ነበር። በእሳቸው የተገፉትና በኢትዮጵያ አንድነት ስር የኦሮሞን ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል አዲስ ዓላማ ይዘው ብቅ ያሉት እነ ከማል ገልቹ ዛሬ ቁልፍ ቦታዎችን መያዛቸው ለአቶ ዳውድ ከመርዶም የከበደ ዜና ሆኖባቸዋል። ያላቸው ምርጫ መረበሽ ነው። ማወክ ነው። ይሀው እንቅልፍ አጥተው፡ በትጋት እየሰሩበት ነው።

አቶ ዳውድ የሚመሩት ኦነግ ጥርስ የለውም። በኦሮሞ ህዝብ ስም ስለሚምልና ስሙንም ስለያዘ እንጂ ለውጡ ሳይመጣ ትንሽ ጊዜ ቢቆይ ኖሮ በህይወት አይገኝም ነበር። ከአስመራ ሌላ የመንቀሳቀሻ መሬት ያጣው ኦነግ እነአብይ ደርሰው ከመጥፋት አዳኑት እንጂ እንደዳይኖሰር ‘’ነበር’’ ተብሎ በታሪክ ውስጥ ብቻ የሚቀር ድርጅት በሆነ ነበር። ዛሬ ከሞት አንቅተው፡ እስትንፋስ በዘሩለት የኦዴፓ መሪዎች ላይ ጉድጓድ እየማሰ መሆኑ ድርጅቱ ከስህተቱ የማይማር ከንቱ መሆኑን የሚያሳይ ነው። መስራቾቹና አንጋፋዎቹ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሆኑት እነሌንጮ ለታ የለውጡ አጥርና ዘብ ሆነው በተሰለፉበት ዘመን፡ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ከባይተዋርነት አውጥተው ወደ መሃል በማምጣት ታሪካዊ ድርሻቸውን እየተወጡ የሚገኙት እነዶ/ር መረራ ጉዲና አወንታዊ ሚናቸውን በቀጠሉበት በዚህ ሁነኛ የታሪክ ምዕራፍ ወቅት እነዳውድ ከእንቅልፋቸው ያነቃቸውን የለማን ቡድን ጠልፎ ለመጣል መነሳታቸው ግራ የሚያጋባ ነው። ከእንግዲህ ለኦሮሞ ህዝብ ከእነለማ መስመር የተሻለ ይገኝ ይሆን?

ለህወሀት የኦነግ ካርድ በጥሩ ጊዜ የተመዘዘ ሆኖለታል። መቀሌ ላይ ፍራሽ ጎዝጉዘው ለቅሶ የተቀመጡት መሪዎቹ በኦነግ የሰሞኑ ፊጥ ፊጥ ማለት ተጸናንተው የከዳቸው ወዝ ለጊዜውም ቢሆን ተመልሶላቸዋል። የኦነግ እንቡር እንቡር ማለት ለህወሀቶች ሰርግና ምላሽ ነው። በመለስ ዜናዊ አስተምህሮት ተኮትኩተው ያደጉትና ፌስቡኩን የወረሩት የህወሀት ሰራዊቶች ከኦነግ በላይ ኦነግ ሆነው ከበሮ እየደለቁ ነው። አብዲ ዒሌ ሶማሌ ክልልን ሲያምስና በመጨረሻው ሰዓት ሲንደፋደፍ ህወሀቶች ሰማይ እየቧጠጡ አየር እየቀዘፉ ‘’ህገመንግስት ተጣሰ’’ ጩሀትን ሲያቀልጡ እንደነበር እናስታውሳለን። አብዲ ዒሌ ከርቸሌ ሲወርድ ደግሞ ተራው የኦነግን ባንዲራ ማውለብለብ ሆኗል። ሰሞኑን የኦነግ ጉዳይ ለህወሀቶች ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እየተራገበ ነው። በኦሮሞ ስም ሰልፍ እስከመጥራት ደርሰዋል። አጋጣሚው እንዳያመልጣቸው በሚችሉት ሁሉ እየተፍጨረጨሩ ነው። የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊ እንደተናገሩት በኦነግ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ወታደር ሆነው ተሰልፈዋል። አጃኢብ ነው።
የህወሀቶች ሩጫ ሩቅ አይዘልቅም። የአሜሪካን ዱላ እየተወለወለ ነው። ኢንተርፖል ፋይሉን እየፈተሸ ነው። የአብይ አስተዳድርም በሁለቱም ስለት የሆነ የፍትህ ቢላዋ ይዞ ተነስቷል። ህወሀቶች ከኦነግ ጀርባ ሆኖ ኢትዮጵያን የሚያምሱበት የተንኮልና የሴራ እንቅስቃሴአቸው የሚገታበት ጊዜ ከበራፋቸው ብዙም አይርቅም። ከሶማሌ ክልል ከእነሰንኮፋቸው የተነቀሉት፡ ከአፋርም የመርዝ እጃቸው የተቆረጠባቸው፡ በጋምቤላና ቤንሻንጉል አከርካሪያቸውን ለመስበር እየተወሰደባቸው ባለው እርምጃ ቆሌአቸው የተገፈፈባቸው ህወሀቶች የመጨረሻ እድላቸውን በኦነግ እየሞከሩት ነው።

የጊዜ ጉዳይ ነው። ኦዴፓና የኢትዮጵያ መንግስት ከመግለጫ ያለፈውንና መሬት ወርዶ በተግባር እየታየ ያለውን ሀገር የማረጋጋት እርምጃ በድል ሲያጠናቅቁ የህወሀትና የኦነግ ያልተቀደሰ ጋብቻ ይፈርሳል። ህወሀትም ያን ተከትሎ ለመጨረሻው ቀብሩ ይዘጋጃል። የሁለቱ ጸረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ጋብቻ ፈታኝ ቢሆንም መፍረሱ የማይቀር ነው። እሳት በማጥፋት የተጠመደው የዶ/ር አብይ መንግስት የህወሀትን አከርካሪ ሰብሮ፡ ኦነግን ምሱን አቅምሶ ወደ ኢኮኖሚውና ዲሞክራሲ ግንባታው ፊቱን እንዲያዞር ከምንም በላይ የህዝብ ድጋፍ የሚፈልግበት ወቅት ላይ ነው።

LEAVE A REPLY