በዚህ አጭር ፅሁፍ ከኢትዮጵያ ጠቅላላውክፍል አንዱን ከተማ ቦታና አካባቢ (በተለይም አዲስ አበባን) በስም ጠቅሰው ይህ ከተማ የእገሌ ብሄር ነው የዚህ ከተማ ባለቤት እንቶኔ የተባለው ብሄር ነው የተቀራችሁት ኗሪዎች እንጂ ባለቤት አይደላችሁም ይሉት ይሉኝታ ቢስ ፖለቲካና የፖለቲካ ዲስኩር አንድምታውንና የመፈክሩን አስቀያሚ ድንቁርናበጥቂት ነጥቦች ለማስቀመጥ እሞክራለው።
እነሆ ኢትዮጵያ የተባለችው ሃገር ላይ መወለድህና ኢትዮጵያዊ የተባለ ዜግነት ባለቤት መሆንህ አንድ የሚሠጥህ መሠረታዊ ነገር የሃገርህ የእያንዳንዱ ክፍለ ሀገርና ስፍራ ህጋዊ ተፈጥሯዊ ባለቤት መሆንህን ነው።
ኢትዮጵያዊ መሆንሽ ብቻውን የሚያጎናፅፍሽ አንድ መሠረታዊ ነገር የአዲስ አበባ:የጎንደር :የአሩሲ: የጋምቤላና የወልቂጤ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የኢትዮጵያ መሬት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ባለቤት መሆንሽን ነው። የኢትዮጵያ መሬት አየርና ሠማይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ የሃገሩ የትላንት ታሪክና የነገ ተስፋ ጭምር ባለቤት ነው። ለትናንት ደግና ክፉ ትዝታችን ብቻ ሳይሆን ለነገ ተስፋና ስጋታችን ጭምር እኩል ባለቤቶች ነን።
ኢትዮጵያዊ መባላችንና መሆናችን በቅፅበትና ያለምንም ጣልቃ ገብነት (Automatically) የሚያጎናፅፈን አንድ ተራ ነገር ይህ ከላይ የጠቀስኩት የሀገር ባለቤት መሆንን ነው::ደግሞም የኢትዮጵያ እያንዳንዱ ቦታ ባለቤት ስለነበረና ስለሆነነው በአንደኛው የሃገራችን ክፍል ከውጭ የሚመጣ ወራሪ ጠላት ሲነሳ በሁሉም የሀገራችን ክፍል የሚኖረው ዜጋ “ሆ” ብሎ ተነስቶ በነብሡ ተወራርዶ ሀገሩን ሲያስከብር የኖረው። የባድመ ባለቤት ስለነበረ ነው የጋምቤላው :የአፋሩ: የኦሮሞው:የሲዳማው:የጉራጌው:የአማራው ወጣት ባድመ ላይ ነብሡን የገበረው የሃረርና የኦጋዴን ፍፁም ባለቤት ስለነበረ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከዚያድባሬ ጦር ጋር እየተናነቀ ነብሡን አሣልፎ የሠጠው። እንኳን ተወልደን ያደግንበት የአዲስ አበባ ከተማ ይቅርና የአሩሲና የአዲግራት :የጋምቤላና የወልቃይት : የጎንደርና የሠመራ ያለከልካይ ባለቤት ነኝ። እነዚህ ስሞች ላይ እኔ እንደ ኢትዮጵያው ዜጋ ባለቤት ካልሆንኩኝ ወይ እነዚህ ከተማዎች የኢትዮጵያ አካልና ክፍል አይደሉም አልያም እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም።
ኢትዮጵያዊ መሆንና የዚያኑ ቀን የሀገር ባለቤት አለመሆን በተመሳሳይ ግዜና ሁኔታ (simultaneously) አብረው አይሆኑም ። አንዱ ለመሆን የሌላኛውን አለመሆን የምክንያትና የተጠየቅ ህግ የግድ ይለዋል።ይህ የዜግነት መብትና የሀገር ባለቤትነት የፖለቲካ ሣይንስም ይሁን የዜግነት ፅንሰ ሀሳብ መሠረታዊ ሀሁ ነው። እንግዲህ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ። አዲስ አበባም ይሁን የትኛውም የሃገራችን ስፍራ ላይ የሚኖረን ኢትዮጵያዊ “አንተ እዚህ ኗሪ እንጂ ባለቤት አይደለህም።” ብለህ ስታውጅ በመሠረታዊነት እየነጠቅከው ያለኸው የከተማው ባለቤትነቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ጭምር ነው።
እየተናገርኩት ያለሁት ነገር የተራቀቀ ምክንያታዊነትና የሚያስገርም እውቀት አይደለም ተራ የፖለቲካ ሀሁ ነው። የሚያስገርመውና ትንሽም የሚያሳፍረው ይህን ቀላል እውቀትና ዓለማዊ እውነት ሊገነዘቡ ያልቻሉ አልያም ሆን ብለው በዘረኝነት ህሊናቸውን የደፈኑ የጎሳ ፖለቲከኞች መበርከታቸው ነው። ምናልባት የጎሳ ጋሻ ጃግሬዎችና ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ይህንን ግልብና አስቀያሚ መፈክር ለማስተጋባት መጣደፋቸው እጅግ እያስገርም ይሆናል። እጅግ የሚያስገርመው ይህን አይነት ግንዛቤና ሸውራራ መረዳት አንግበው የኢትዮጵያንየነገ ፖለቲካ በማበጀቱ ሂደት ከዋና ተከፋዮች መሀል ከፊት ተጠቃሽ መሆናቸው ነው። ስራ የበዛበት የአብይ አህመድ መንግስትም እንደ እንቦቃቅላ የሚያባብላቸው መሆኑም ለእኛ ለዜጎቹ የሚያስተክዝ ነው።
እነሆ በዜግነት ፖለቲካ ስር ለመሠባሠብ ሁለንተናዊ መብትና ነፃነታችንን ለማስከበር እንዲሁም የሃገር (የኢትዮጵያችን) ባለቤት መሆናችንን በፅንፈኛ ጎሠኞች ላለማስነጠቅ በንቃት የምንተባበርበትና የምንቀናጅበት ዘመን ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው።
ኢትዮጵያችን በክብር ለዘላለም ትኑር!