/ኢትዮጵያነገዜና/፡- በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ባለፉት አራት ወራት በተፈጠሩ ችግሮች 29 ሲቪል ነዋሪዎች፣ 12 የፖሊስ አባላት መገደላቸውንና 2 ሺህ ክላሽንኮቭን ጨምሮ ከሶስት ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስት መዘረፉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አለማየሁ እጅጉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጠሩ ችግሮችን በውይይትና በሰከነ መንገድ በሰላመዊ ሁኔታ ለመፍታት ለለፉት ስድስት ወራት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም የከፋ ዋጋ ማስከፈሉን ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ወራት ብቻ በክልሉ በተፈጠሩ ችግሮች 29 ንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋቱን የገለጹት ከሚሽነሩ 2 የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ ስራ ላይ የተሰማሩ የዞን መምሪያ ሃላፊዎችን ጨምሮ 12 የፖሊስ አባላት ህይወት ማለፉንም ገልፀዋል።
በምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ እንዲሁም በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች አካባቢዎች አንዳንድ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት እንዲያቆሙ መደረጉንም ነው ኮሚሸነሩ የተናገሩት።
በቄለም ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ 2 ሺህ 72 ክላሽንኮቭ መሳሪያዎች ከፖሊስ ተዘርፈዋል ያሉት ኮምሽነሩ፤ በምዕራብ ወለጋ ከመንግስት ካዝና ከ3 ሚሊየን ብር በላይ መዘረፉንም ለዜና ማሰራጫዎች ገለጸዋል።
የተጠቀሱት ንብረቶች የግለሰብ ንብረቶችን የማይጨምሩ ሲሆን፥ በርካታ የግለሰብ ንብረቶች መዘረፋቸውም ኮሚሽነር ጄነራሉ አስረድተዋል።
ለነኝህ ችግሮች ዋነኛ ተጠያቂ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎች መሆናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፥ በአዲስ አበባም የኦነግ አማራሮች በሚያደርጉት ውይይት የሰላማዊ ትግል ለማድረግ ስምምነት ላይ እንደደረሱ የሚገልጹ ቢሆንም ታጣቂዎቹ የዜጎችን መብት አደጋ ላይ መጣላቸውን ነው በአጽንኦት ገለጸዋል።
የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ከክልሉ መንግስት ጋር በሚያደርጓቸው ውይይቶች ቃል የገቧቸውን መሰረታዊ ስምምነቶች እየተተገበሩ እንዳልሆነም አስረድተዋል።
በዚህም የሰወች ህይወት እንደሚያልፍ፣ ንብረት እንደሚወድም እና መንገዶች እየተዘጉ መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ የሚናገሩት።
የኦሮምያ ፖሊስ ኮሚሽን በዜጎች ደህንነት ላይ አደጋ የጣሉ ኃይሎችን ለመፋለም ቁርጠኛ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል። የተለያዩ በቡድን የተደራጁ ሃይላት በስልጠናና በማህበረሰቡ ላይ በቀጥታ ጥቃት በማድረስ ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውንም ዘገባዎች አስረድተዋል።