እውነተኛው የስብሃትና የበረከት ጭንቀት | የኢትዮጲስ ጋዚጣ ርዕሰ አንቀጽ)

እውነተኛው የስብሃትና የበረከት ጭንቀት | የኢትዮጲስ ጋዚጣ ርዕሰ አንቀጽ)

በሥልጣን ዘመናቸው፣ አቦይ ስብሃትና በረከት ስምዖን ፈፅመው የሚጣጣሙ ሰዎች አልነበሩም፡፡ አብዛኛውን “ወርቃማ ዘመናቸውን” (ከ1983 እስከ መለስ ዜናዊ ህልፈት) በኩርፊያ፣ እርስ በእርስ በመተማማትና በመወናጀል አሳልፈዋል (“ስብሃት ቢኖር አይጠቅምም፣ ባይኖር አይጎዳም” ይሉ ነበር በረከት፡፡)

መቼም ቢሆን ግን፣ በገቢር ተለያይተው አያውቅም፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ሁለቱም አበክረው ለኤርትራ መገንጠል ተከራክረዋል/ታግለዋል፣ የኤርትራ መገንጠልን በሚቃወሙት ላይ ቂም ይዘውም (“ትምክተኞች” የሚሏቸውን)፣ በኢትዮጵያ ነፃ ምርጫ እንዳይኖር፣ ሃሳብ በነፃነት እንዳይገልፅ፣ የሙያ ማህበራት በነፃነት እዳይደራጁ ባለቸው አቅም ሁሉ ተረባርበው ኢትዮያን ለ3 አስርት ዓመታት የከጭቆናና የአፈና ሀገር አድርገውታል፡፡ ሌላው ቢቀር፣ “የፍትህ ሰቆቃ” የሚለው ዘጋቢ ፊልም ለህዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ፣ በንፁሀን ደም ስለተፃፈው ታሪካቸው ፀፀት ተሰምቷቸው ህዝብን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባ ነበር፡፡ ይሄ ግን አልሆነም፡፡ አንዲያውም፣ ከዚያ በተቃራኒ መንገድ ላይ ሆነው፣ በህዝብ ቁስል ላይ እንጨት እየሰደዱና ከፍተኛ ትንኮሳ እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡

እዚህ ጋር፣ ለምን ? ብለን የግድ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ፣ “ህሊና አላቸው ወይ?” የሚለው ጥያቄ አለ፡፡ ሰው ናቸውና፣ ህሊና የላቸውም ሊባል አይችልም፡፡ ህሊናን ግን ሊዳፈን ይችላል፡፡ ህሊናቸው ሳያውቁት የሚዳፈንባቸው አሉ፣ አውቀውም የሚያዳፍኑት አሉ፡፡ በእኛ ግምት፣ በዘር ጥላቻ ልቦናቸው የጨለመው ስብሃትና በረከት፣ ሆን ብለው ያዳፈኑት ናቸው፡፡ ለእነሱ ፀፀት መሸነፍ ነው፣ ድክመት ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን፣ ሁለቱ ግለሰቦች በዘረኝነታቸው ብቻ የሚገለፁ አይደሉም፡፡ በሥልጣን ዘመናቸው “ስኳር ሲልሱ” (በእነሱ አነጋገር) እንደነበር በርካታ ማሰረጃዎች አሉ፡፡

ከእዚህ ማስረጃዎች መካከል፣ ለህዝብ ጎላ ብለው የሚታዩት አሉ፡፡ የሁለቱም ገቢ (በወር ደሞዛቸው እንደሚተዳደሩ ነው የሚናገሩት) እና ኑሮ የሰማይና የምድር ያህል የሚራራቅ ነው፡፡ በትግል ዘመን የነበረውን ባናውቅም፣ ስብሃት፣ ያለፉትን ሶስት አሥርት ዓመታት ያሳለፉት፣ ከሞላ ጎደል፣ አንዳ አንድ የሳወዲ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ሆነው ነው፡፡

በገንዘብ ተጠቅመዋል ከማለት ይልቅ፣ ተጫወተዋበታል ቢባል ይቀላል፡፡ መንግሥታቸው ቢያንስ በእሳቸው የዕድሜ ዘመን ምንም ይሆናል ብለው ስላላሰቡም፣ ቅምጥል ኑሯቸውን ከህዝብ ለመሸሸግ ቅንጣት የምታክል ሙከራም አላደረጉም፡፡ በዚህ የቅምጥል ዘመናቸው፣ አብዛኛውን ጊዜቸውን ከፖለቲካ ይልቅ ለዝነጣ አውለውታል፡፡ አሁን ወደ ፖለቲካው ሙሉ በሙሉ ዞር ለማለት የከጀሉት፣ ገንዘቡ ቢኖራቸውም፣ ዘና ብለው የሚዘንጡበት ዘመን ስለቀረባቸው መሆኑ ነው፡፡

የበረከት ስምዖን አካሄድ ግን፣ ከአዛውንቱ የሕወሓት መሥራች በጣም የተለየ ነወ፡፡ ፊት ለፊት የሚታይ ነገር እንዳይኖር ተጠንቅቀዋል፡፡ እንደ ስብሃት ግን፣ ልጃቸውን ወጭ ሀገር ልከው (“ስኮላር” እየተባለ) አስተምረዋል፡፡ “ብዙ ገንዘብ የሚያወጣ ዕቃ ያለቀረጥ ወደ ሀገር ቤት ካለስገባሁ” ብለው የጉምሩክ ባለሥልጣናት ጋር እንደተጋጩ እማኞች አሉ፡፡ ከወትሮው ጥንቃቂያቸው ትንሽ ዘነፍ ብለውም፣ መፅሃፍ አሳተመው፣ በስፖንሰር ስም የጎረፈላቸው ገንዘብ በአደባባይ የተፈፀመ ሙስና እደነበር ብዙ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ይህም ድፍረት፣ ኢህአዴግ እስከወዲኛው ምንም አይሆንም በሚል የተፈፀመ ነው፡፡

አሁን ግን፣ የመለኮት ኃይል ምስጋና ይግባውና፣ ዘመኑ ሳይታሰብ ተለወጧል፡፡ የፍትህ ጥያቄም እየተሰተጋባ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም፣ ደቡብ አፍሪቃን ያለገጠመ ችግር ፊት ለፊቷ ተጋርጦ ትገኛለች፡፡ በደቡብ አፍሪቃ ተሞክሮ፣ የብሄራዊ ይቅርታና የእርቅ ሂደት በፖለቲካ ወንጀሎች ላይ ብቻ ተተክሎ የተተገበረ ነው፡፡ በአፓርታድ ዘመን በደቡብ አፍሪቃ መንግስት የነበረው ናሽናል ፓርቲ፣ የዘረኝነት እንጂ የሙስና ሥርዓት አልገነባም ነበር፡፡ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ያቆመው ሥርዓት ግን፣ ከዘረኝነትና ከጭቆናም አልፎ፣ የዘረፋ ሥርዓት (kleptocracy) እደነበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎላ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

ታዲያ፣ ለዘረፋስ የሚሰጥ ይቅርታ አለ ወይ? ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙኃኑ ለዘረፋ ይቅርታ መሰጠት የለበትም ወደሚለው አዘንብሏል፡፡ እነ ስብሃትና በረከትን እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ይመስላል፡፡ የመቀሌው ጩኸታቸው ይህ ጉዳይ የወለደው ጭንቀት ነው፡፡ የጩኸቱ ፖለቲካዊ ይዘት (ትክክልም ሆነም አልሆነም) እናሳ ነው፡፡ ከታሰሩ፣ “በፖለቲካ እንጂ በሙስና አይደለም” የሚባልበትን እርሾ ለመቀመም እየታገሉ ናቸው፡፡

ፖለቲካው በዚህም ሄደ በዚያ ግን፣ ስብሃትም ሆኑ በረከት፣ ፖለቲካን አለአግባብ የሚበለፅግበት መሳሪያ አድርገውታል፡፡ ይህን ሀቅ ወደ ኋላ ሄደው መፋቅ አይችሉም፡፡ ይህ እድፍ ደግሞ፣ ስለ ሀገር ለማናገር የሚያበቃቸውን የሞራል ቁመና አሳጥቷቸዋል፡፡ ባዶ ጩኸት፣ እጃቸውን በሌብነት ካላቆሸሹ ሰዎች እኩል እያደረጋቸውም፡፡

LEAVE A REPLY