ዱሮ አዲስ አበባ ላይ በየሰፈሩ የተደራጁ የጸብ ቡድኖች ነበሩ። ቦንባርድ፣ ፍለጠው ቁረጠው፣ ወዘተ… እነዚህ የሰፈር ቡድኖች ጊዜ እየጠበቁ አንዱ ብድን ከሌላው ጋር በጥቃቅን ጉዳዮች በሚነሱ ጸቦች የሰው ህይወት እስኪያልፍ ድረስ ተናርተው፣ ተፈነካክተው፣ በጮቤ ተዋግተው ይለያዩ ነበር። ጸቡም ሆነ በቡድኖቹ መካከል ያለው ቅራኔ ምንም የተለ አላማ የለውም። ሁሉም የሰፈሩ አንበሳ መሆኑን ለማሳየት እንጂ። በተጣሉት ቡድኖች መካከል እርቅ እስኪወርድ ድረስ የአንዱ ቡድን አባል በሌላው ቡድን ሰፈር ዝር አይልም።
አንዳንድ ጊዜ ጸባቸው በአነስተኛ ሸጉጦች ጭምር ይታገዝ ስለነበር መረር ያሉ ጉዳቶችም ይደርሱ ነበር። እነኚህ ቡድኖች በደርግ እና በወያኔ የሽግግር ወቅት የአካባቢዎቻቸው ንጉሶች ሆነው ነበር። ግርግር ለምን ይመቻል እንደሚባለው። በኋላ ግን ወያኔ ሁሉም ቡድኖች ላይ በከፈተችው የተቀናጀ ዘመቻ የእነዚህ የሰፈር ጉልበተኞች እድሜ ማክተሚያ ሆነ። ሁሉም በአንድ ወቅት ከሰሙ። ወያኔ የሁሉም ሰፈር ጉልቤ ሆና ሃያ ሰባት አመት ያሻትን እየደበደበች፣ እያሰረች፣ እየገደለች የኢትዮጵያ ቦንባርድ እና ፍለጠው ቁረጠው ሆና ኖረች።
የዛሬውን ሽግግርም እንዲሁ የፍለጠው ቁረጠው ዘመን ሊያደርጉት የተነሱ ቡድኖች መኖራቸውን በይፋ እየታየ ነው። የዛሬዎቹን ለየት የሚያደርጋቸው በሕግ በተመዘገቡ እና እውቅና በተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስም የተመዘገቡ መሆናቸው ነው። በየክልሉ አካባቢው የኛ ነው፣ ይህ ሃሳብ በኛ ክልል ማራማድ አትችልም፣ ይህን የምታስብ ከሆነ እኛ ክልል እንዳትመጣ እያሉ የሚያስፈራሩ እና ከዛም አልፈው በክልላቸው ውስጥ ያገኙትን የተቀናቃኝ ፓርቲ አመራር ወይም አባል በዱላ ተሰብስበው የሚነርቱ ፖለቲከኛ መሳይ ተደባዳቢዎች ተፈጥረዋል።
ከቅርቡ ልነሳና ገጣሚ; አክቲቪስትና የህግ ባለሙያ/ጠበቃ መንግስቱ ዘገየ #MengistuZegeye ደሴ፤ ሃይቅ አካባቢ በሚገኙ የአብን አባላት በቡድን ሆነው ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመበት መሆኑን ትላንት ገልጿል። ደብዳቢዎቹ እነ ማን እንደሆኑ እና የአብን አባላት መሆናቸውንም በደንብ አስረግጦ ገልጿል። ጉዳዩንም ለፖሊስ አሳውቆ ሰዎቹ እየተፈለጉ መሆኑን በድህረ ገጹ ላይ ጠቅሷል። ይህ አይነቱ ድርጊት ሲፈጸም የመጀመሪያው አይደለም። እንዲሁ የተደራጁ ሰዎች በአማራ ክልል በደብረ ታቦር ከተማ በአርበኞች ግንቦት 7 ጽ/ቤት ላይ ጥቃት እና ዝርፊያ ሰንዝረዋል። ጥቃቱ የሌባ ድርጊት እንዳይባል የድርጅቱን አርማዎች እና ባንዲራም አቃጥለው ነው የሄዱት። ሌባ ከድርጅት አርማ ጋር ምን ጸብ አለው። ስለዚህ የተደራጃ የፓርቲዎች ጸብ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው።
በተመሳሳይ አርበኞች ግንቦት 7ን ጨምሮ ሌሎች ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች በተለያዩ ክልሎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው መስራት እንዳልቻሉ በአደባባይ እየገለጹ ነው። በአርሲ እና በጅማ አካባቢ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ተደብድበው፣ ንብረቶቻቸው ተዘርፎ ከአካባቢው መባረራቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል።
እንግዲህ እያንዳንዱ የጎጥ ድርጅት እንደ አዲስ አበባ የዱሮ ተደባዳቢ ቡድኖች ክልሉን የራሱ መፈንጫ ብቻ ካደረገው እንዴት ምርጫ ለማካሄድ ይቻላል? የአብን አመራሮች ከና በጠዋቱ ለታማኝ በየነ #Tamagnebeyene እግሩ ቦሌ ሲረግጥ እኛ ሰፈር የምትመጣው ይህን ይህን ለማለት ከሆነ ድርሽ እንዳትል የሚል መልዕክት በሊቀመንበሩ በኩል አስተላለፉ የሚለው ዜና እንደተሰማ የፓርቲው አካሄድ እየተንሻፈፈ መሆኑን ለመረዳት ቀላል ነበር። ይህ የሰዎችን ሃሳብ የሚገድብ አይነት አገላለጽ በፓርቲ አመራር ደረጃ ከተነገረ ወደታች ወረድ ሲል የጡንቻ ነገር ሊከተል ይችላል የሚል ስጋት ነበረኝ። በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለው አለመግባባትም ሆነ ጡዘት ብዙም አይመለከተኝም። አያሳስበኝምም። ነገር ግን ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸውን በአደባባይ እና ፊት ለፊት ቁጭ በለው ከመሟገት ይልቅ በደጋፊዎቻቸው በኩል አንዱ ሌላውን ማሳደድ ከጀመረግ ግን ፖለቲካ አዲዎስ።
በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ ችግሮች ጎልተው እየታዩ ነው። የኦሮሞ ድርጅቶች ካልሆኑ በቀር በክልሉ ውስጥ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ሕዝብን ሊያወያዩ አልቻሉም። ክልሉ የእኛ እና የእኛ ብቻ ነው ብለው የሚፎክሩ ብቻ ሳይሆን ዱላ የሚመዙ የመንደር ብሄረተኞች ጎልተው እየታዩ ነው።
በተቃራኒው እነኚሁ ክልሎቻቸውን እንደ አገር አጥርው ለመያዝ ሌላውን አላስጠጋ ያሉ ድርጅቶች ምርጫው ቶሎ እና በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ይካሄድልን እያሉ ነው። ይቺ ተራ የፖለቲካ ሸር ነች። የመወዳደሪያ ቀጠናው ውስጥ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ እና ሕዝብን እንዳያደራጁ እያደረጉ፣ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች እየደበደቡ እና ነብረቶቻቸውን እየዘረፉ ምርጫው ይካሄድ ብሎ ማላዘን ተራ ብልጠት ነው።
ምርጫ ሰላማዊ የሆነ የመወዳደሪያ መድረክ ነው። ምርጫ የሃሳብ ልዕልና መገለጫ ነው። ምርጫ ሃሳቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበት መድረክ ነው። ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃሳብ ጥራትና ብቃት የሚታይበት የአማራጭ ፖሊሲዎች ገበያ ነው። ምርጫ ሕዝብ ያሻውን በነጻነት የሚሾምበት እና የማይፈልገውንም ድርጅት ድምጽ በመንፈግ የሚያገልበት መድረክ ነው። ፓርቲዎች ወደ ቡጢ እና እርስ በርስ መዘላለፍ ላይ ካተኮሩ ምርጫ የሚታሰብ አይሆንም።
በጎሳ በተከፋፈለ አገር እና በጎሳ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አሸን ባሉበት አገር ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ሁሌም ሁለት ፈተናዎች ከፊቱ አሉ። አንደኛው፤ ሁሉም የጎሳ ድርጅት የእኔ የሚለው የራሱ አካባቢ ስላለው ያንን ሥፍራ ወይም ክልል ከሌሎች የጎሳ ወይም ህብረ ብሄራዊ ድርጅቶች ነጻ ቀጠና ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች ይወስዳሉ። ሁለተኛው ችግር ደግሞ አብዛኛው የመደራጃ ሃሳብ እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ በታሪክም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ደረሱበት የሚሏቸው ብሶቶች ናቸው። ስለዚህ ብሶት የወለዳቸው የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ባሉበት አገር አንዱ እና ትልቁ ፈተና የተፎካካሪ ሃሳቦች እጥረት ነው። ተፈካካሪ የሆነ የፖለቲካ ሃሳብ ሳይሆን ለውይይት የሚቀርበው ተፎካካሪ የሆነ የብሶት ክምር ነው። ኦሮሞው የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የደረሰውን በደል ሲተረትር፣ አማራው በአማራው ላይ የደረሰውን በደል ሲተረትር፣ ትግሬው በትግሬው ላይ፣ ውራጌው በውራጌው ላይ፣ አፋሩ በአፋሩ ላይ፣ ወላይታው በወላይታው ላይ የደረሰው በደል ሲተረትሩና ሲዘረዝሩ ነው የሚሰማው። የብሶት ዝርዝር የፖለቲካ ሃሳብ (political ideology) ሊሆን አይችልም።
ምናልባት ይህን የመጀመሪያውን ምርጫ በግርግር እና በብሶት ክምሮች ታጅበን ልናልፈው እንችል ይሆናል። እውነተኛ የፖለቲካ ፉክክር ለማድረግ ግን ከብሶት የዘለለ የፖለቲካ ማቀንቀኛ ሃሳብ ያስፈልጋል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፓርቲዎች አደረጃጀት እና በየሚዲያው የሚሰጡትን ትንታኔ ያየን እንደሆነ ብዙዎቹ ብሶት የወለዳቸው እና በብሶት የተዋጡ ሃሳቦች ብቻ ነው ይዘው እየቀረቡ ያሉት። ለነገሩ በብሶት ለተዋጠ ሕዝብ በአደባባይ ብሶቱን የሚያወራለት ማግኘት ትልቅ ነገር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የብሶት ፖለቲካ የበለጠ ሆድን ያሻክር እና አዕምሮንም በቂም ይሞላ እንደሆን እንጂ ለፖለቲካ እድገት ጠብ የሚል ነገር የለውም።
የአንድ አገር ፖለቲካ ሊያድግ እና ሊሰለጥን የሚችለው በእውቀት ላይ በተመረኮዙ ውይይቶችም ክርክሮች እና በጥናት እና ምርምር ነው። በቡጢ ወይም የሰፈር አጥር በማጠር ፖለቲካ አይደለም ልጅ ማሳደግ አይቻልም። በደልን በመተንተን እና አሳምሮ በመግለጽ ብቻ የአገሪቱን የፖለቲካ እንቆቅልሽ መፍታት አይቻልም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የሚፈታው ጥልቅ በሆኑ የሃሳብ ውይይቶች እና በባለ ሙያ በተደገፉ ምርምሮች ነው። ፓርቲዎች የደጋፊዎቻቸውን ሰልፍ ማርዘም የህልውና ጉዳይ ነው። ይችን ሰልፍ በዘር እና በብሶት አጀናዎች ላይ በማተኮር ማርዘም ቀላል ቢሆንም ዘላቂ ግን አይደለም። ብሶቶቹ አንድ ቀን ምላሽ ያገኛሉ። ያኔ ሰልፉም ይመናመናል። ስለዚህ የሕዝብ ብሶት ብቻ የመታገያ አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀስ ለፓርቲዎች ህልውና አደጋ ነው። በጎሳ የሚደራጁ ድርጅቶች ሁሌም በሌላው አለምም የሚገጥማቸው አንዱ ፈተና ይሄ ነው። ብሶት ሲጠፋ ብሶቱን እራሳቸውም ሊፈጥሩት የሚችሉበት አጋጣሚም እንዳለ በብዙ አገሮች ታይቷል። እሩቅ ሳንሄድ ህውሃት እያደረገ ያለውን ማየት በቂ ነው። የትግራይን ሕዝብ ሁሌም ብሶተኛ ለማድረግ እና እልውናው ከህውሃት ቃር የተቆራኘ ለማድረጅ የሚሰራው ደባ ዛሬም ብሶበታል።
ለማንኛውም ከብሶት ፖለቲካ ወደ ሃሳብ ፖለቲካ እስክንሸጋገር ድረስ ብዙ መላላጥና መጋጋጦች ይኖራሉ። ብሶት ብቻ ሳይሆን ነፍትጥም የታጠቁ የጎሳ ድርጅቶች ያሉበት አገር ስለሆነ ይህን ማጥራት ምናልባትም ከምናስበው በላይ የተራዘመ ጊዜ እና እልህ አስጨራሽ ትግል ይጠይቅ ይሆናል። ግን የማይቀርበት ጉዞ ነው። አሁን በአገራችን ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ገዢውንም ጨምሮ በሃሳብ ልዩነት እንፈርጃቸው ቢባል ከሁለት እና ሦስት ጎራ የዘለሉ አይሆኑም። ከሰማኒያ ልጥ ፓርቲ ወደ ሁለት እና ሦስት በሃሳብ ልዩነት ወደተዋቀሩ ድርጅቶች ለመድረስ ግን ብዙ ፈተናዎች ከፊታችን ይጠብቁናል።
ለረዥሙ የተሳካ ጉዞ ግን ወሳኙ መወያየት እንጂ ጡጢ ሊሆን አይችልም።
በቸር እንሰንብት!